1ስለ አሞን ልጆች፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "እስራኤል ልጆች የሏትምን? ወይስ የትኛውንም ነገር ከእስራኤል የሚወርስ የላትምን? ሚልኮም ጋድን ለምን ወረሰ? ሕዝቡስ በከተሞቿ ላይ ስለ ምን ተቀመጠ?
2ስለዚህ ተመልከቱ፣ በአሞን ልጆች ከተማ በረባት ላይ የጦርነት ውካታን የማሰማበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር፤ የፍርስራሽ ክምርም ትሆናለች፣ ሴቶች ልጆችዋም በእሳት ይቃጠላሉ። እስራኤልም የወረሷትን ትወርሳለች፣" ይላል እግዚአብሔር።
3"ሐሴቦን ሆይ፣ ጋይ ፈርሳለችና አልቅሺላት! እናንተም የረባት ሴቶች ልጆች ጩኹ! ማቅ ልበሱ። ሚልኮም ካህናቱና አለቆቹም በአንድነት ይማረካሉና ጩኹ፣ ማቅም ታጠቁ፣ አልቅሱም፣ በቅጥሮችም መካከል ተሯሯጡ።
4ማን ይመጣብኛል ብለሽ በብርታትሽ የታመንሽ አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፣ በሸለቆችሽ፣ ውኃ በሚያረካቸው ሸለቆችሽ፣ ስለ ምን በብርታትሽ ትመኪያለሽ?
5ተመልከቺ፣ ሽብርን አመጣብሻለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ይህ ሽብር በዙሪያሽ ከከበቡሽ ሁሉ ዘንድ ይሆናል። እያንዳንዳችሁም በፊታችሁ ወዳለው ስፍራ ትበተናላችሁ። የሚሸሹትንም የሚሰበስብ አይኖርም።
6ነገር ግን ከዚያ በኋላ የአሞንን ልጆችን ምርኮ እመልሳለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።"
7ስለ ኤዶምያስ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "በውኑ በቴማን ከእንግዲህ ጥበብ አይገኝምን? ማስተዋል ካላቸውስ መልካም ምክር ጠፍቶአልን? ጥበባቸው ተበላሽቷልን?
8ሽሹ! ተመለሹ! እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ፣ በጥልቅ ውስጥ ተቀመጡ። የዔሳውን ጥፋት እርሱን በምቀጣበት ጊዜ አመጣበታለሁና
9የወይን አዝመራ ለቃሚዎች ወደ አንተ ቢመጡ፣ቃርሚያውን አይተውልህምን? ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፣ የሚሠርቁት እስኪበቃቸው ድረስ አይደለምን?
10እኔ ግን ዔሳውን ዐራቈትሁት። የተሸሸገበትንም ስፍራዎች ገለጥሁ። ስለዚህ ይሸሸግ ዘንድ አይችልም። ልጆቹ፣ ወንድሞቹ፣ እንዲሁም ጎረቤቶቹ ጠፍተዋል፤ እርሱም የለም።
11ድሀ አደጎችህን ተዋቸው። እኔም ለሕይወታቸው እንክብካቤ አደርጋለሁ፤ መበለቶችህም በእኔ ሊታመኑ ይችላሉ።"
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ "ተመልከቱ ያልተገባቸው ሰዎች ጽዋውን በእርግጥም ሊጠጡት ይገባቸዋል። አንተም ሳትቀጣ የምትቀር ይመስልሃልን? በእርግጥ ትጠጣለህ እንጂ ያለ ቅጣት አትቀርም።
13ባሶራ መደነቂያና መሰደቢያ፣ መረገሚያም እንድትሆን በራሴ ምያለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር። ከተሞችዋም ሁሉ ለዘላለም ባድማ ይሆናሉ።
14ከእግዚአብሔር ዘንድ ወሬ ሰምቻለሁ፣ መልእክተኛም በአሕዛብም መካከል ተልኳል፣ 'ተሰብሰቡ፣ እርስዋንም አጥቊ። ለጦርነትም ተነሡ' ይላል።
15"ተመልከቱ፣ በንጽጽር ስትታይ በአሕዛብ ዘንድ የተጠቃህ፣ በሰዎችም ዘንድ የተናቅህ አድርጌሃለሁ።
16በዓለት ንቃቃት ውስጥ የምትኖር፣ የተራራውን ከፍታ የምትይዝ ሆይ፣ ድፍረትህና የልብህ ኵራት አታልለውሃል። ቤትህን ምንም እንደ ንስር ከፍ ብታደርግ፣ ከዚያ አወርድሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።
17ኤዶምያስም የሚያልፉባት ሁሉ እስኪደነቁ ድረስ መሸበሪያ ትሆናለች። ስለ መጣባትም መቅሠፍት ሁሉ እንዲህ ያሉ ሰዎች ሁሉ ተደናግጠው ያፍዋጩባታል።
18"ሰዶምና ገሞራ፣ በእነርሱም አጠገብ የነበሩት ከተሞች እንደ ተገለበጡ፣" ይላል እግዚአብሔር፣ "እንዲሁ በዚያ ሰው አይቀመጥም የሰው ልጅም አይኖርባትም።
19ተመልከቱ፣ ከእርስዋ ዘንድ በቶሎ አባርራቸዋለሁና በጠነከረው አምባ ላይ ከዮርዳኖስ ትዕቢት እንደ አንበሳ ይወጣል፤ የተመረጠውንም በእርስዋ ላይ እሾመዋለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ ለእኔ ጊዜ የሚወስን ማን ነው? ወይስ ፊቴን የሚቃወም እረኛ ማን ነው?
20"ስለዚህ እግዚአብሔር በኤዶምያስ ላይ የመከረባትን ምክር፣ በቴማንም በሚኖሩ ሰዎች ላይ ያሰባትን አሳብ አድም። በእውነት ትንንሽ መንጎች ሳይቀሩ ይጐተታሉ። በእውነት ማደሪያቸውን ባድማ ያደርግባቸዋል።
21ከመውደቃቸው ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች። የጩኸታቸውም ድምፅ በቀይ ባሕር ተሰማ።
22ተመልከቱ፣ አንዱ መጥቶ እንደ ንስር ወጥቶ ያጠቃል፣ እያንዣበበ ክንፉን በባሶራ ላይ ይዘረጋል። ያን ጊዜ በዚያ ቀን፣ የኤዶምያስ ወታደሮች ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል።"
23ስለ ደማስቆ፣ "ክፉ ወሬ ሰምተዋልና ሐማትና አርፋድ አፈሩ። ቀለጡ! ሊረጋጋ በማይችል ባሕር ላይ ኅዘን አለ።
24ደማስቆ እጅግ ደከመች። ትሸሽም ዘንድ ዘወር አለች፤ ሽብር ያዛት፣ እንደ ወላድም ሴት ጣርና ምጥ ያዛት።
25ሕዝቦቿም፣ 'የተመሰገነችው ከተማ፣ የደስታዬ ከተማ፣ ስፍራውን ሳትለቅቅ እንዴት ቀረች?' ይላሉ።
26ስለዚህ ጐበዛዝትዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፣ በዚያም ቀን ተዋጊዎቿ ሁሉ ይጠፋሉ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።"
27"በደማስቆም ቅጥር ላይ እሳት አነድዳለሁ፣ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች።"
28የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታ ስለ ቄዳርና ስለ አሶር መንግሥታት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ "ተነሡ ወደ ቄዳርም ውጡ፣ የምሥራቅንም ልጆች አጥፉ።
29ጦር ሠራዊቱ ድንኳናቸውንና መንጋቸውን ይወስዳል፤ መጋረጆቻቸውንና ዕቃቸውን ሁሉ ግመሎቻቸውንም ለራሳቸው ይወስዳሉ። በዙሪያቸውም ሁሉ ጥፋትን ጥሩባቸው፣ 'ሽብር በዙሪያቸው ሁሉ አለ!"
30ሽሹ! በሩቅ ቦታም ተቅበዝበዙ! እናንተ በአሶር የምትኖሩ ሆይ፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ተማክሮባችኋልና፣ አሳብም አስቦባችኋልና በጥልቅ ውስጥ ተቀመጡ፣ ይላል እግዚአብሔር። ሽሹ! ዙሩና ተመለሱ!
31ዕርፊት ወዳለበት በዋስትናም ወደ ተቀመጠው፣ ደጅና መወርወሪያ ወደሌለው ብቻውንም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ውጡ፣ ተነሡ! አጥቊ!።
32ግመሎቻቸው ይበዘበዛሉ፣ የእንስሶቻቸውም ብዛት በጦርነት ይማረካል። ጠጉራቸውንም በዙሪያ የሚላጩትን ሰዎች ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከየዳርቻቸውም ሁሉ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
33አሶርም የቀበሮ መኖሪያና የዘላለም ባድማ ትሆናለች። በዚያም ሰው አይኖርም፣ የሰው ልጅም አይቀመጥባትም።"
34ስለ ኤላም ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። ይህ የሆነው በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ ነው። እንዲህም አለ፣
35"የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዋና የኃይላቸው መሣሪያ የሆነውን የኤላምን ቀስት እሰብራለሁ።
36ከአራቱም ከሰማይ ማዕዘናት አራቱን ነፋሳት በኤላም ላይ አመጣለሁ፣ የኤላምን ሕዝብ ወደ እነዚያ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ። ከኤላም የተሰደዱ ሰዎች የማይበተኑበት ሕዝብ አይገኝም።
37ስለዚህ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውን በሚሹአት ፊት ኤላምን አስደነግጣለሁ። ክፉ ነገርን እርሱም ጽኑ ቍጣዬን አመጣባቸዋለሁና፣ ይላል እግዚአብሔር። እስካጠፋቸውም ድረስ በኋላቸው ሰይፍ እሰድድባቸዋለሁ።
38ከዚያም፣ ዙፋኔንም በኤላም አኖርና ንጉሡን ከእነአለቆቹ አጠፋለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።
39ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የኤላምን ምርኮ እመልሳለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።"