1"እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ተመልከቱ፣ በባቢሎን ላይና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ አጥፊውን ነፋስ አስነሣለሁ።
2በባቢሎንም ላይ የውጪ ሰዎች እልካለሁ። እነርሱም ይበትኗታል፣ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፤ በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል።
3በወርዋሪው ላይ በጥሩርም በሚነሣው ላይ ቀስተኛው ቀስቱን ይገትር፤ ለጐበዛዝትዋ አትዘኑ፣ መላውን ሠራዊትዋንም አጥፉ።
4የቆሰሉት ሰዎች በከለዳውያንም ምድር ተገድለው፣ በሜዳዋም ላይ ተወግተው ይወድቃሉና።
5ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል ምንም እንኳ የተሞላች ብትሆን፣ እስራኤልም ሆነ ይሁዳ በአምላኩ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ዘንድ አልተጣለም።
6ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ፤ እያንዳንዳችሁም ራሳችሁን አድኑ። በበደልዋ አትጥፉ። የእግዚአብሔር የበቀል ጊዜ ነውና። እርሱም ብድራትዋን ይከፍላታል።
7ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ ነበረች፣ አሕዛብም ከጠጅዋ ጠጥተዋል፤ ስለዚህ አሕዛብ እብድ ሆነዋል።
8ባቢሎን በድንገት ወድቃ ጠፍታለች። ለእርሷ አልቅሱላት! ትፈወስም እንደ ሆነ ለቊስልዋ መድኃኒት ውሰዱላት።
9'ባቢሎንን ለመፈወስ ተመኘን፣ እርስዋ ግን አልተፈወሰችም። ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፣ እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ከፍ ብሎአልና ትታችኋት እያንዳንዳችን ወደ ምድራችን እንሂድ።'
10እግዚአብሔር ጽድቃችንን አውጥቶአል። ኑ፣ በጽዮን የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ሥራ እንናገር።'
11ፍላጾችን ሳሉ ጋሻዎችንም አዘጋጁ። እግዚአብሔር ያጠፋት ዘንድ አሳቡ በባቢሎን ላይ ነውና የሜዶንን ነገሥታት መንፈስ አስነሥቶአል፤ የእግዚብሔር በቀል፣ የመቅደሱ መጥፊያ በቀል ነውና።
12በባቢሎን ቅጥር ዓላማውን አንሡበት፣ ጥበቃን አጽኑ። ተመልካቾችን አቁሙ፣ ከከተማዋ የሚወጡትን ለመያዝ ድብቅ ጦር አዘጋጁ። እግዚአብሔር በባቢሎን በሚኖሩት ላይ የተናገረውን አስቦአልና፣ አድርጎአልምና።
13አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፣ በመዝገብም የበለጠግሽ፣ እንደ ስስትሽ መጠን ፍጻሜሽ ደርሶአል።
14የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሏል፣ 'በእውነት ሰዎችን እንደ አንበጣ እሞላብሻለሁ፣ እነርሱም የጦርነት ጩኸት ያነሡብሻል።'
15ምድርን በኃይሉ ፈጠረ፤ ዓለሙን በጥበቡ መሠረተ። ሰማያትንም በማስተዋሉ ዘረጋ።
16ድምጹን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፣ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል። ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፣ ነፍስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል።
17ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ እንደ እንስሳ ሆኗል፤ እያንዳንዱ አንጥረኛ ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል። ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፤ እስትንፋስም የላቸውምና።
18እነርሱም ምናምንቴና፣ የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በሚቀጡበት ጊዜ ይጠፋሉ።
19የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፣ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና። እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
20አንቺ መዶሻዬና የጦር መሣሪያዬ ነሽ። በአንቺ አሕዛብን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም መንግሥታትን አጠፋለሁ።
21በአንቺ ፈረሱንና ሠረገላውን እሰባብራለሁ፤
22በአንቺም በላዩ የሚቀመጡትን ወንድ እና ሴት እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እሰባብራለሁ። በአንቺም ጐልማሳውንና ልጃገረዲቱን እሰባብራለሁ።
23በአንቺም እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም አራሹንና ጥማጁን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም አለቆችንና ሹማምቶችን አሰባብራለሁ።
24በጽዮን በዓይናችሁ ፊት ስለሠሩት ክፋታቸው ሁሉ በባቢሎንና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ፍዳቸውን እከፍላለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።
25"ተመልከት፣ አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊ ተራራ ሆይ፣ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፣ ይላል እግዚአብሔር። እጄንም እዘረጋብሃለሁ፣ ከድንጋዮችም ላይ አንከባልልሃለሁ። የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ።
26ከአንተም ለማዕዘንና ለመሠረት የሚሆን ድንጋይ አይወስዱም፣ ለዘላለምም ባድማ ትሆናለህ፣ ይላል እግዚአብሔር።
27"በምድር ላይ ዓላማን አንሡ። በአሕዛብም መካከል መለከት ንፉ። እንዲያጠቋት አሕዛብን አዘጋጁባት፤ የአራራትንና የሚኒን የአስከናዝንም መንግሥታት ሰብስቡባት፣ አለቃንም በላይዋ አቁሙ። እንደ ጠጉራም አንበጣ ኩብኩባ ፈረሶችን በላይዋ አውጡ።
28አሕዛብን የሚዶንንም ነገሥታት አለቆችንም ሹማምቶችንም ሁሉ የግዛታቸውንም ምድር ሁሉ አዘጋጁባት።
29ማንም እንዳይቀመጥባት የባቢሎንን ምድር ባድማ ያደርጋት ዘንድ የእግዚአብሔር አሳብ በባቢሎን ላይ ጸንቶአልና ምድር ተናወጣለች ታመመችም።
30የባቢሎን ወታደሮች መዋጋትን ትተዋል፤ በምሽጎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል። ኃይላቸውም ጠፍቶአል እንደ ሴቶችም ሆነዋል። ማደሪያዎችዋም ነድደዋል፣ መወርወሪያዎችዋም ተሰብረዋል።
31ከዳር እስከ ዳር ድረስ ከተማው እንደ ተያዘች መልካምዎችዋም እንደ ተያዙ፣ ቅጥርዋም በእሳት እንደ ተቃጠለ፣ ሰልፈኞችም እንደ ደነገጡ
32ለባቢሎን ንጉሥ ይነግር ዘንድ ወሬኛው ወሬኛውን፣ መልእክተኛውም መልእክተኛውን ሊገናኝ ይሮጣል።"
33የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ አውድማ እንደ ተረገጠ ጊዜ፣ እንዲሁ የባቢሎን ልጅ ናት። ጥቂት ቈይታ የመከር ጊዜ ይደርስላታል።
34ኢየሩሳሌም፣ 'የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላኝ። አድርቆ አሟጠጠኝ፣ እንደ ባዶ የሸክላ ዕቃም አደረገኝ። እንደ ዘንዶም ዋጠኝ። ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ። እኔንም ወደ ውጪ ጣለኝ።' አለች።
35የጽዮን ነዋሪዎች እንዲህ ይላሉ፣ 'በእኔና በሥጋዬ የተደረገ ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን።' ኢየሩሳሌምም፣ 'የሚፈስሰው ደሜ ጥፋት በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን" ትላለች።
36ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከቺ፣ እምዋገትልሻለሁ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ። ባሕርዋንም ድርቅ አደርገዋለሁ፣ ምንጭዋንም አደርቀዋለሁ።
37ባቢሎንም የድንጋይ ቊልልና የቀበሮ ማደሪያ፣ መደነቂያም ማፍዋጫም ትሆናለች፤ የሚቀመጥባትም ሰው አይገኝም።
38በአንድነትም እንደ አንበሶች ያገሣሉ። እንደ አንበሳም ደቦሎች ያጕረመርማሉ።
39በስስት በሞቃቸው ጊዜ ደስ እንዲላቸው፣ ለዘላለምም አንቀላፍተው እንዳይነቁ፣ የመጠጥ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ፣ አሰክራቸውማለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።
40እንደ ጠቦቶችና እንደ አውራ በጎች እንደ አውራ ፍየሎችም ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።"
41"ባቢሎን እንዴት ተያዘች! የምድርም ሁሉ ምስጋና እንዴት ተወሰደች። ባቢሎንም በአሕዛብ መካከል መደነቂያ እንዴት ሆነች።
42ባሕር በባቢሎን ላይ ወጣ! በሞገዱም ብዛት ተከደነች።
43ከተሞችዋ ባድማና ደረቅ ምድር ምድረ በዳም፣ ሰውም የማይኖርበት፣ የሰውም ልጅ የማያልፍበት ምድር ሆኑ።
44በባቢሎንም ውስጥ ቤልን እቀጣለሁ፤ የዋጠውንም ከአፉ አስተፋዋለሁ፣ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርሱ አይሰበሰቡም። የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል።"
45"ሕዝቤ ሆይ፣ ከመካከልዋ ውጡ። እያንዳንዳችሁም ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ራሳችሁን አድኑ።
46በምድርም ከሚሰማ ወሬ የተነሣ አትፍሩ፣ ልባችሁም የዛለ አይሁን፤ በአንድ ዓመት ወሬ ይመጣል፣ ከዚያም በኋላ በሌላው ዓመት ወሬ፣ በምድርም ላይ ግፍ ይመጣል፣ አለቃም በአለቃ ላይ ይነሣል።
47ስለዚህ፣ ተመልከቱ፣ የተቀረጹትን የባቢሎን ምስሎች የምቀጣበት ዘመን ይመጣል። ምድርዋም ሁሉ ታፍራለች፣ ተወግተውም የሞቱት ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ።
48አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር በእነርሱም ያለው ሁሉ ስለ ባቢሎን እልል ይላሉ፣ ይላል እግዚአብሔር።
49ባቢሎንም ከእስራኤል ተወግተው የሞቱት እንዲወድቁ እንዳደረገች፣ እንዲሁ በባቢሎን ከምድሩ ሁሉ ተወግተው የሞቱት ይወድቃሉ።"
50"ከሰይፍ ያመለጣችሁ፣ ሂዱ! ተረጋግታችሁ አትቁሙ። እግዚአብሔርን ከሩቅ ጥሩት፤ ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡ።
51ስድብን ስለ ሰማን አፍረናል፤ ባዕዳን ሰዎችም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገብተዋልና ነውር ፊታችንን ከድኖታል።"
52"ስለዚህ፣ ተመልከቱ፣ የተቀረጹትን ምስሎችዋ የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር፤ በምድርዋም ላይ ሁሉ የተወጉት ያንቋርራሉ።
53ባቢሎን ምንም ወደ ሰማይ ብትወጣ፣ የኃይልዋንም ምሽጎች ብታጸና፣ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል፣ ይላል እግዚአብሔር።"
54ከባቢሎን ጩኸት፣ ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰምቶአል።
55እግዚአብሔር ባቢሎንን አጥፍቶአታልና፣ ከእርስዋም ታላቁን ድምፅ ዝም አሰኝቶአልና፤ ሞገዳቸውም እንደ ብዙ ውኆች ይተምማል፣ የድምፃቸውም ጩኸት በብርቱ ተሰምቶአል።
56አጥፊው በባቢሎን ላይ መጥቶባታልና፣ ኃያላኖችዋ ተያዙ፣ ቀስታቸውም ተሰባበረ፤ እግዚአብሔር ፍዳን የሚከፍል አምላክ ነውና፣ ፍዳንም በእርግጥ ይከፍላል።
57"መሳፍንቶችዋንና ጥበበኞችዋን፣ አለቆችዋንና ሹማምቶችዋን፣ ወታደሮችዋንም አሰክራለሁ፥ ለዘላለምም አንቀላፍተው አይነቁም፣ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ።"
58"የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰፊው የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል፤ ረጃጅሞችም በሮችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፤ የወገኖችም ድካም ከንቱ ትሆናለች፣ የአሕዛብም ሥራ ሁሉ ለእሳት ትሆናለች፤ እነርሱም ይደክማሉ።"
59የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ከእርሱ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘው ቃል ይህ ነው፣ ያን ጊዜ ሠራያ የቤት አዛዥ ነበረ።
60በባቢሎንም ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ፣ ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ፣ ኤርምያስ በመጽሐፍ ላይ ጻፈው።
61ኤርምያስም ሠራያን እንዲህ አለው፣ "ወደ ባቢሎን በገባህ ጊዜ ይህ ቃል ሁሉ መነበቡን እርግጠኛ ሁን።
62አንተም ደግሞ፣ 'ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት፣ ለዘላለምም ባድማ እንድትሆን ታጠፋት ዘንድ በዚህች ስፍራ ላይ ተናግረሃል' በል።
63ከዚያም ይህንን ጥቅልል መጽሐፍ ማንበብ ከፈጸምህ በኋላ፣ ድንጋይን እሰርበትና በኤፍራጥስ ወንዝ መሃከል ጣለው።
64አንተ፣ 'እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች፣ አትነሣምም" በል። የኤርምያስ ቃል እዚህ ላይ ያበቃል።