መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 48

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለ ሞዓብ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ናባው ጠፍታለችና ወዮላት። ቂርያታይም ተይዛለች አፍራለችም። ምሽጓ ተደምስሷል፣ ተዋርዷልም።
2ከእንግዲህ ወዲህ ሞዓብ ትምክሕት የላትም። በሐሴቦን ያሉ ጠላቶቿ በእርሷ ላይ ጥፋትን አሲረዋል። 'ኑ ሕዝብ እንዳትሆን እናጥፋት። ማድሜንም እንዲሁ ትጠፋለች፣ ሰይፍም ይከታተልሻል።' ብለዋል።
3አድምጡ! መፍረስና ታላቅ ጥፋት ያለበት የጩኸት ቃል ከሖሮናይም ተሰማ።
4ሞዓብ ጠፍታለች። ልጆችዋም ጩኸታቸውን አሰምተዋል።
5በሉሒት ኮረብታ ለቅሶ እያለቀሱ ይወጣሉ፣ ከጥፋቱም የተነሣ፣ በሖሮናይምም ቍልቍለት ጩኸትን ሰምተዋል።
6ሸሹ! ሕይወታችሁን አድኑና በምድረ በዳ እንዳለ ቊጥቋጦ ሁኑ።
7በሥራሽና በኃብትሽ ታምነሻልና፣ አንቺ ደግሞ ትያዢያለሽ። ከዚያም፣ ካሞሽ ከካህናቱና ከመሪዎቹ ጋር በአንድነት ወደ ምርኮ ይሄዳል።
8አጥፊው ወደየከተማው ሁሉ ይመጣል፣ አንዲትም ከተማ አታመልጥም። ስለዚህ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሸለቆው ይጠፋል፣ ሜዳውም ይበላሻል።
9በእርግጥም በርራ እንድትጠፋ ለሞዓብ ክንፍ ስጡአት። ከተሞችዋ በውስጣቸው አንድም የማይኖርባቸው ወና ይሆናሉ።
10የእግዚአብሔርን ሥራ በስንፍና የሚሠራ ርጉም ይሁን! ሰይፉን ደም ከማፍሰስ የሚከለክል ርጉም ይሁን!
11ሞዓብ ከወጣትነቱ ጀምሮ ደህንነት ይሰማው ነበር። እርሱ ከዕቃ ወደ ዕቃ ተገላብጦ እንደማያውቀው ወይኑ ነው። ወደ ምርኮም ሄዶ አያውቅም። ስለዚህ ጣዕሙ ከመቼውም ጊዜ በላይ መልካም ነው፣ መዓዛውም አልተለወጠም።
12ስለዚህ ተመልከቱ፣ የሚያገላብጡትን ሰዎች የምልክበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም እያፈሰሱ ጋኖቹን ባዶ ያደርጋሉ፣ መስቴዎቹንም ይሰብራሉ።
13የእስራኤል ቤት ከታመነበት ቤተል እንዳፈረ ሁሉ፣ እንዲሁ ሞዓብ ከታመነበት ካሞሽ ያፍራል።
14እናንተ፣ 'እኛ ወታደሮች ነን፣ ጽኑዓን ተዋጊዎች ነን' እንዴት ትላላችሁ?
15ሞዓብ ይፈርሳል፣ ከተሞቹም ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። የተመረጡትም ጕልማሶች ወደ መታረድ ወርደዋል። ይህ የንጉሡ አዋጅ ነው! ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
16የሞዓብ ጥፋት ሊመጣ ቀርቦአል፤ መከራውም እጅግ ይፈጥናል።
17በሞዓብ ዙሪያ ያላችሁ ሁሉ፣ አልቅሱ። ዝናውንም የምታውቁ ሁሉ፣ 'ብርቱው በትር፣ የከበረው ሽመል ተሰብሯልና ወዮለት' ብላችሁ አልቅሱለት።
18በዲቦን የምትኖሪ ሴት ልጅ ከክብር ስፍራሽ ውረጂና በደረቅ መሬት ላይ ተቀመጪ። ሞዓብን የሚያጠፋው፣ ምሽግሽንም የሚሰብረው ወጥቶብሻልና።
19በአሮዔር የምትኖሩ ሕዝቦች በመንገድ አጠገብ ቆማችሁ ተመልከቱ። እየሸሹ ያሉትንና የሚያመልጡትን ጠይቊ። 'ምን ተፈጠረ?' በሉ።
20ሞዓብም ፈራርሷልና አፈረ። አልቅሱ፣ ጩኹ፣ ለእርዳታም ተጣሩ። ሞዓብ እንደ ተዘረፈ በአርኖን አጠገብ ለሰዎች አውሩ።
21አሁን በኮረብታማው ገጠር ላይ ባሉት በሖሎን፣ በያሳ፣ በሜፍዓት ላይ፣
22በዲቦን፣ በናባው፣ በቤት ዲብላታይም ላይ፣
23በቂርያታይም፣ በቤትጋሙል፣
24በቤትምዖን ላይ፣ በቂርዮት፣ በባሶራ፣ እና በሞዓብ ምድር ባሉ የቅርብና ሩቅ ከተሞች ሁሉ ላይ ቅጣት መጥቶአል።
25የሞዓብ ቀንድ ተቈረጠ፤ ክንዱም ተሰበረ፣ ይላል እግዚአብሔር።
26በእኔ በእግዚአብሔር ላይ ኰርቷልና አስክሩት። እንግዲህ ሞዓብ በገዛ ራሱ ትውከቱ ላይ በጥላቻ እጆቹን ያጨበጭባል፣ ደግሞም መሳለቂያ ይሆናል።
27እስራኤል ለአንተ መሳለቂያህ አልሆነምን? ወይስ ስለ እርሱ በተናገርህ ጊዜ ሁሉ ራስህን እንድትነቀንቅ በሌቦች መካከል ተገኝቶአልን?
28እናንተ በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ፣ ከተሞችን ትታችሁ በቋጥኝ ውስጥ ተቀመጡ። በዐለታማ ገደል አፋፍ ቤትዋን እንደምትሠራ ርግብ ሁኑ።
29እጅግ እንደ ታበየ ስለ ሞዓብ ትዕቢት፣ ስለ ትምክህቱም፣ ስለ ኩራቱም፣ ራሱን ስለማክበሩም፣ ስለ ልቡም ትዕቢት ሰምተናል።
30ምንም ሆኖ የማይቆጠረውን የድንፋታ ንግግሩን እኔ ራሴ አውቃለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ፉከራው ምንም አልሠራም።
31ስለዚህ ለሞዓብ አለቅሳለሁ፣ በኃዘኔታ ለመላዋ ሞዓብ እጮኻለሁ። ለቂርሔሬስ ሰዎች አለቅሳለሁ።
32አንቺ የሴባማ ወይን ሆይ፣ ከኢያዜር ልቅሶ ይልቅ ለአንቺ አለቅሳለሁ! ቅርንጫፎችሽ የጨው ባሕርን ተሻግረው ወደ ኢያዜር ባሕር ደርሰዋል። አጥፊዎች በሰብልሽና በወይንሽ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
33ክብረ-በዓላዊ ሐሤትና ፍንደቃ ከፍሬያማው እርሻና ከሞዓብ ምድር ጠፍተዋል። የወይን ጠጁን ከመጥመቂያው አጥፍቻለሁ። ጠማቂውም በደስታ እልልታ አይጠምቅም። እልልታቸውም የደስታ እልልታ አይሆንም።
34ከሐሴቦን ጩኸት እስከ ኤልያሊና፣ እስከ ያሀጽ ድረስ ድምፃቸውን ሰጥተዋል፤ ከዞዓር እስከ ሖሮናይምና እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ ይደርሳል፤ የኔምሬም ውኃዎች ደርቀዋልና።
35በኮረብታው መስገጃ ላይ የሚሠዋውን ለአማልክቱም የሚያጥነውን ከሞዓብ ፍጻሜያቸውን አደርጋለሁ ይላል እግዚአብሔር።
36ልቤ ለሞዓብ እንደ እንቢልታ ይጮኻል። ልቤም ለቂርሔሬስ ሰዎች እንደ እንቢልታ ይጮኻል። ያገኙት ትርፋቸው ጠፍቶባቸዋልና።
37ራስ ሁሉ መላጣ፣ ጢምም ሁሉ የተላጨ ነውና። በእጅም ሁሉ ላይ ክትፋት በወገብም ላይ ማቅ አለና።
38በሞዓብ ሰገነት ሁሉ ላይ፣ በእያንዳንዱም የተደላደለ ጣራ እና በሁሉም የሞዓብ አደባባዮች ላይ ለቅሶ አለ። ሞዓብን ማንም እንደማይፈልጋቸው የሸክላ ዕቃዎች ሰብሬአለሁና፣ ይላል እግዚአብሔር።
39እንዴት ተገለበጠ! ከለቅሶም የተነሣ ሞዓብ እያፈረ ጀርባውን እንዴት መለሰ! ብላችሁ አልቅሱ። ስለዚህ ሞዓብ በዙሪያው ላሉት ሁሉ መሳቂያና ድንጋጤ ይሆናል።"
40እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ተመልከቱ፣ ጠላት እንደ ንስር እየበረረ፣ ክንፉንም በሞዓብ ላይ እየዘረጋ ይመጣል።
41ከተሞቹ ተይዘዋል፣ ምሽጎቹም ተይዘዋል። በዚያም ቀን የሞዓብ ወታደሮች ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል።
42ስለዚህ ሞዓብ በእኔ በእግዚአብሔር ላይ እብሪተኛ ሆኗልና ሕዝብ ከመሆን ይጠፋል።
43በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ፣ ፍርሃትና ጉድጓድ፣ ወጥመድም በእናንተ ላይ አለ፣ ይላል እግዚአብሔር።
44በፍርሃት የሸሸ በጕድጓድ ውስጥ ይወድቃል፥ ከጉድጓድም የወጣ በወጥመድ ይያዛል፤ በሞዓብ ላይ የምበቀልበትን ዓመት አመጣበታለሁና፣ ይላል እግዚአብሔር።
45የሸሹ ያለ ምንም ብርታት ከሐሴቦን ጥላ በታች ቆመዋል፤ እሳት ከሐሴቦን፣ ነበልባልም ከሴዎን ወጥቶአልና፣ የሞዓብንም ማዕዘን የሤትንም ልጆች አናት በልቶአልና።
46ሞዓብ ሆይ፣ ወዮልህ! የካሞሽ ሕዝብ ተደምስሰዋል፣ ወንዶች ልጆችህ ተማርከዋልና፣ ሴቶች ልጆችህም ወደ ምርኮ ሄደዋልና።
47ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።" የሞዓብ ፍርድ እዚህ ላይ ያበቃል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።