መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 46

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለ አሕዛብ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2ስለ ግብጽ፦ "ይህ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በከርከሚሽ ስለ ነበረው ሠራዊት ነው። በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታው ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ኒካዑ ሠራዊት፦
3ትንንሾቹን እና ትልልቆቹን ጋሻዎች አዘጋጁና ወደ ውጊያ ሂዱ።
4ፈረሰኞች ሆይ፣ ፈረሶችን ለጉሙና ውጡ፣ ራስ ቍርንም ደፍታችሁ ቁሙ። ጦርንም ሰንግሉ፣ የጦር ዕቃንም ልበሱ።
5በዚህ የማየው ምንድነው? ወታደሮቻቸው ተሸንፈዋልና፣ በፍርሃት ተሞልተው ወደ ኋላ ተመለሱ። ወደ ኋላቸውም ሳይመለከቱ ፈጥነው ሸሹ። ድንጋጤ በሁሉ ቦታ አለ፣ ይላል እግዚአብሔር።
6ፈጣኑ ሊሸሽ አይችልም፣ ወታደሮችም ሊያመልጡ አይችሉም። በሰሜን ተሰናከሉ፣ በኤፍራጥስ ወንዝ በኩል ደግሞ ወደቁ።
7ይህ እንደ አባይ ወንዝ የሚነሣ፣ ውኃውም እንደ ወንዝ የሚናወጥለት ማን ነው?
8ግብጽ እንደ አባይ ወንዝ ይነሣል፣ ውኃውም እንደ ወንዙ ይናወጣል። እርሱም፣' እነሣለሁ ምድርንም ሁሉ እከድናለሁ። ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን አጠፋለሁ ብሎአል።
9ፈረሶች ሆይ፣ ውጡ። ሠረገሎችም ሆይ፣ ንጐዱ፤ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የፋጥ ኃያላን፣ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኃያላን ይውጡ።'
10ያ ቀን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የበቀል ቀን ነው፣ ደግሞም ጠላቶቹን እርሱ ራሱ ይበቀላቸዋል። ሰይፍ በልቶ ይጠግባል። ደማቸውንም ተሞልቶ ይጠጣል። ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መሥዋዕት አለውና።
11ድንግሊቱ የግብጽ ሴት ልጅ ሆይ፣ ወደ ገለዓድ ውጪና መድኃኒት ውሰጂ። መድኃኒትን በራስሽ ላይ ማብዛትሽ ጥቅም የለሽ ነገር ነው። ለአንቺ የሚሆን ፈውስ የለም።
12ወታደሩ በወታደሩ ላይ ተሰናክሎ፣ ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ እፍረትሽን ሰምተዋል። ምድር በለቅሶሽ ተሞልታለች።"
13የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መጥቶ የግብጽን ምድር ሲያጠቃ እግዚአብሔር ለነብዩ ኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
14"ለግብጽ ተናገሩ፣ በሚግዶልና በሜምፎስ ይሰማ። በጣፍናስ 'ሰይፍ በዙሪያህ ያለውን በልቶአልና፣ ተነሥተህ ተዘጋጅ' ብለዋል።
15የከፍታ አምላክሽ ለምን ሸሸ? በበሬ የተመሰለው ጣዖትሽስ ለምን አይቆምም? እግዚአብሔር ገፍትሮ ጥሎታል።
16እርሱ የሚሰናከሉትን ቊጥር ያበዛል። እያንዳንዳቸው ወታደሮች አንዱ በሌላው ላይ ይወድቃል። እነርሱም፣ "ተነሡ። ወደቤት እንጂድ። ወደገዛ ሕዝባችን፣ ወደ ተወለድንባት ምድር እንሂድ። ይህንን እየቀጠቀጠን ያለውን ሰይፍ ትተን እንሂድ።" ይላሉ።
17በዚያም፣ 'የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ያገኘውን ዕድል የሚያሳልፍ ኁከተኛ ብቻ ነው" ብለው ይናገራሉ።
18"እኔ ሕያው ነኝና በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር፣ በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፣ እንዲሁ በእውነት ይመጣል፣ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ።
19አንቺ በግብጽ የምትቀመጪ ልጅ ሆይ፣ ለምርኮ የምትሄጂበትን ዕቃ አዘጋጂ። ሜምፎስ የምትሸበር ትሆናለችና፣ ማንም በዚያ የማይኖርባት እንድትሆን ትፈራርሳለችና።
20ግብጽ እጅግ የተዋበች ጊደር ናት፣ ነገር ግን ከሰሜን በኩል የሚያሰቃይ መዥገር ይመጣባታል።
21በመካከሏም ያሉ ቅጥረኛ ወታደሮች እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፣ ነገር ግን እነርሱም እንዲሁ ይመለሱና ይሸሻሉ። የጥፋታቸው ቀን እየመጣባቸው ነውና፣ የቅጣታቸው ጊዜ መጥቶባቸዋልና በአንድነት አይቆሙም።
22ጠላቶቿ በእርሷ ላይ ይሰለፉባታልና ግብጽ እንደ እባብ ድምፅ ትጮኻለች፣ በደረቷም ተስባ ትሸሻለች። በመጥረቢያ እንደሚቆርጡ እንደ እንጨት ቈራጮች ሆነው ይመጡባታል።
23በጣም ጥቅጥቅ ያሉ ቢሆኑም እንኳን ጫካዎቿን ይቈርጣሉ፣ ይላል እግዚአብሔር። ጠላቶቿ ሊቆጠሩ እስከማይችሉ ድረስ ከአንበጣ ይልቅ ብዙ ይሆናሉና።
24የግብጽ ሴት ልጅ እንድታፍር ትደረጋለች። ከሰሜን ለሚሆኑ ሕዝቦች እጅ ተላልፋ ትሰጣለች።"
25የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፣ 'ተመልከቱ፣ የኖእ አሞንን፣ ፈርዖንንም፣ ግብጽንና አማልክቶችዋን፣ ፈርዖን ነገሥታቶችዋንና በእነርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ።
26ነፍሳቸውንም በሚፈልጉ ሰዎች እጅ፣ በባቢሎን ንጉሥ በናቡክደነፆር እንዲሁም በባርያዎቹም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። ከዚያም በኋላ አንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች፣" ይላል እግዚአብሔር።
27"ነገር ግን፣ አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ፣ አትፍራ። አንተም እስራኤል ሆይ፣ አትደንግጥ። እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረከባት ምድር አድናለሁ። ከዚያም፣ ያዕቆብ ይመለሳል፣ ሰላም ያገኛል፣ በዋስትናም ይቀመጣል፣ የሚያስፈራራው ማንም አይገኝም።
28አንተ፣ ባርያዬ ያዕቆብ፣ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተን ያሰደድሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና አትፍራ ይላል እግዚአብሔር። ነገር ግን አንተን ፈጽሜ አላጠፋህም። በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም አልተውህም።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።