1በግብጽ ምድር በሚግዶልና በጣፍናስ በሜምፎስም በጳትሮስም አገር ስለ ተቀመጡ አይሁድ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።
2"የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ያመጣሁትን ክፉ ነገር ሁሉ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል። ተመልከቱ፣ ዛሬ ጠፍተዋል። የሚኖርባቸው የለም።
3ይህም የሆነው ለሌሎች አማልክት በማጠንና በማምለክ ያስቀይሙኝ ዘንድ ስላደረጉት ክፋት ነው። እነዚህም አማልክት እነርሱ ራሳቸው፣ አንተም ራስህ፣ እንዲሁም አባቶቻቸው የማያውቋቸው ናቸው።
4ስለዚህ በተደጋጋሚ ባርያዎቼን ነብያትን ሁሉ ሰደድሁባችሁ። 'እንደነዚህ ያሉ የጠላኋቸውን ርኩስ ነገሮች ማድረጋችሁን አቊሙ' ልላቸው ላክኋቸው።
5ነገር ግን አልሰሙም። ከክፋታቸው ተመልሰው ለሌሎች አማልክት እንዳያጥኑ አትኩሮታቸውን ለመስጠት አልፈለጉም።
6ስለዚህ መዓቴና ቍጣዬ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ ፈሰሱ፣ ደግሞም እንደ እሳት ተቀጣጠሉ። ዛሬም እንደ ሆነው ፈረሱ፣ ባድማም ሆኑ።"
7አሁንም ቢሆን፣ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ወንድንና ሴትን፣ ብላቴናንና ሕፃንን ከይሁዳ እንድታጠፉ ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? ከመካከላችሁ የአንዳችሁም ቅሬታ አይተርፍም።
8ሰውነታችሁንም ታጠፉ ዘንድ፣ በምድርም አሕዛብ ሁሉ መካከል መረገሚያና መሰደቢያ ትሆኑ ዘንድ፣ ለመቀመጥ በገባችሁባት በግብጽ ምድር ለሌሎች አማልክት በማጠናችሁ በእጃችሁ ሥራ ለምን ታስቈጡኛላችሁ?
9በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያደረጉትን የአባቶቻችሁን ክፋት፣ የይሁዳንም ነገሥታት ክፋት፣ የሚስቶቻቸውንም ክፋት፣ የእናንተንም ክፋት፣ የሚስቶቻችሁንም ክፋት ረስታችሁታልን?
10እስከ ዛሬ ድረስ ትሑታን አልሆኑም። በእነርሱና በአባቶቻቸውም ፊት ያኖርሁትን ሕጌን ወይም ሥርዓቴን አላከበሩም፣ አልሄዱበትም።"
11ስለዚህም የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፦ "ተመልከቱ፣ በእናንተ ላይ ጥፋትን ለማድረግ እና ይሁዳን ሁሉ ላጠፋ ፊቴን በላያችሁ ላይ አደርጋለሁ።
12ወደ ግብጽ ሄደው በዚያ እንዲኖሩ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ቅሬታ እወስዳለሁና። ይህን የማደርገው ሁሉም በግብጽ ምድር እንዲጠፉ ነው። እነርሱ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ። ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለመደነቂያ፣ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ።
13ኢየሩሳሌምን በሰይፍ፣ በረሃብ እና በመቅሠፍት እንደ ቀጣሁ፣ እንዲሁ በግብጽ ምድር የሚኖሩትን እቀጣለሁ።
14በዚያ ለመኖር ወደ ግብጽ ምድር ከሄዱ እንኳን ወደ ይሁዳ አገር ተመልሰው በዚያ ይኖሩ ዘንድ ከሚወድዱ ከይሁዳ ቅሬታ ወገን የሚያመልጥና የሚቀር፣ ወደዚያም የሚመለስ የለም። ከዚህ ከሚያመልጥ በቀር ማንም አይመለስም።"
15ከዚያም ሚስቶቻቸው ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ሰዎች ሁሉ፣ በዚያም የቆሙ ሴቶች ሁሉ፣ በግብጽ ምድር በጳጥሮስ የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፣ ታላቅ ጉባኤ ሆነው እንዲህ ሲሉ ለኤርምያስ መለሱለት።
16እነርሱም እንዲህ አሉ፣ "በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን ቃል አንሰማህም።
17እኛና አባቶቻችን፣ ነገሥታቶቻችን፣ አለቆቻችንም በይሁዳ ከተሞች በኢየሩሳሌም አደባባይ እናደርገው እንደ ነበረ፣ ለሰማይ ንግሥት እናጥን ዘንድ የመጠጥንም ቊርባን እንድናፈስስላት ከአፋችን የወጣውን ቃል ሁሉ በእርግጥ እናደርጋለን። ያን ጊዜ እንጀራ እንጠግባለን፣ ደግሞም የትኛውም ጥፋት ሳይደርስብን እንበለጽጋለን።
18ለሰማይ ንግሥት ማጠንን ለእርስዋም የመጠጥን ቍርባን ማፍሰስን ከተውን ወዲህ ግን፣በድህነት ተሰቃይተናል፣ ደግሞም በሰይፍና በረሃብ አልቀናል።"
19ሴቶቹም እንዲህ አሉ፣ "እኛስ ለሰማይ ንግሥት ባጠንንላት፣ የመጠጥንም ቍርባን ባፈሰስንላት ጊዜ፣ ባሎቻችን ሳያውቊ ምስልዋን ለማበጀት እንጐቻ አድርገንላት ኖሮአልን? የመጠጥንም ቍርባን አፍስሰንላት ኖሮአልን?"
20ኤርምያስም ይህን ቃል ለመለሱለት ሕዝብ ሁሉ፣ ለወንዶቹና ለሴቶቹ፣ ለሕዝቡም ሁሉ፣ መለሰላቸው እንዲህም አለ፣
21"እናንተና አባቶቻችሁ፣ ነገሥታቶቻችሁና አለቆቻችሁም፣ የምድርም ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያጠናችሁትን ዕጣን እግዚአብሔር ያሰበው በልቡም ያኖረው አይደለምን?
22ከክፉ ልምምዳችሁ የተነሣ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የሥራችሁን ክፋትና ያደረጋችሁትን ርኵሰት እግዚአብሔር ይታገሥ ዘንድ አልቻለም። ስለዚህ ምድራችሁ ባድማ፣ መደነቂያ፣ መረገሚያም ሆናለች ዛሬም እንደሆነው የሚኖርባት የለም።
23እጣን ስላጠናችሁና በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ስለሠራችሁ፣ ድምፁንም ስላልሰማችሁ፣ በሕጉ፣ በሥርዓቱና በምስክሩም ስላልሄዳችሁ፣ ዛሬ እንደሆነው ይህች ክፉ ነገር አግኝታችኋለች።"
24ከዚያም ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ፣ ለሴቶቹም ሁሉ እንዲህ አለ፣ "በግብጽ ምድር የምትኖሩ ይሁዳ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
25የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'እናንተና ሚስቶቻችሁ በአፋችሁ፣ "ለሰማይ ንግሥት እንድናጥን፣ የመጠጥንም ቍርባን እንድናፈስስላት የተሳልነውን ስእለታችንን በእርግጥ እንፈጽማለን።" ብላችሁ በእጃችሁ አደረጋችሁት፤ እንግዲህ ስእለታችሁን አጽኑ፣ ፈጽሙትም።'
26ስለዚህ፣ እናንተ በግብጽ ምድር የምትኖሩ ይሁዳ ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፣ 'ተመልከቱ፣ በግብጽ ምድር ሁሉ በሚኖር በይሁዳ ሰው ሁሉ አፍ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ፣ "ሕያው እግዚአብሔርን!" ተብሎ እንዳይጠራ በታላቅ ስሜ ምያለሁ፤" ይላል እግዚአብሔር።
27ተመልከቱ፣ ለመልካም ሳይሆን ለጥፋት እተጋባቸዋለሁ። በግብጽ ምድር ያሉት የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ያልቃሉ።
28ከዚያም ከሰይፍ የሚያመልጡ ጥቂት ሰዎች ብቻ ሆነው ከግብጽ ምድር ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሳሉ። ሊቀመጡም ወደ ግብጽ ምድር የገቡት የይሁዳ ቅሬታ ሁሉ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማናችን ቃል እንዲጸና ያውቃሉ።
29ቃሌም በላያችሁ ለክፋት እንዲጸና ታውቁ ዘንድ በዚህች ስፍራ እንድቀጣችሁ ምልክታችሁ ይህ ነው፣' ይላል እግዚአብሔር።
30እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ተመልከቱ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ጠላቱ ለሆነው፣ ነፍሱንም ለሚፈልገው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ። ሁኔታው የግብጹን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራንን ለጠላቶቹ ነፍሱንም ለሚፈልጉ እጅ አሳልፌ እንደሰጠሁት ይሆናል።"