መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 42

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚያም የጭፍራ አለቆች ሁሉ፣ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ የሆሻያም ልጅ ያእዛንያ፣ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ያሉት ሕዝብ ወደ ነብዩ ኤርምያስ ቀረቡ።
2እንዲህም አሉት፣ "ልመናችን በፊትህ ይድረስ። እንዳየኸው ከብዙዎቹ መካከል የቀረነው ጥቂቶች ነንና፣
3የምንሄድበትን መንገድና፣ የምናደርገውን ነገር እንዲያሳየን ስለ እኛና ስለዚህ ቅሬታ ሕዝብ ወደ አምላክህ እግዚአብሔር ጸልይ" አሉት።
4ስለዚህ ነቢዩ ኤርምያስ፣ "ሰምቻችኋለሁ። ተመልከቱ፣እንደጠየቃችሁት ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ። እግዚአብሔርም የሚመልስላችሁን ሁሉ እነግራችኋለሁ። ከእናንተ ምንም አልሸሽግም፤" አላቸው።
5እነርሱም ለኤርምያስ፣ "አምላክህ እግዚአብሔር ወደ እኛ የላከውን ነገር ሁሉ ባናደርግ፣ እግዚአብሔር በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን።
6የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል በመስማታችን መልካም እንዲሆንልን፣ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፣ አንተን ወደ እርሱ የምንልክህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ድምፅ እንሰማለን አሉት።"
7ከዚያም ከዐሥር ቀን በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።
8ስለዚህ ኤርምያስ የቃሬያንም ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የሠራዊቱን አለቆች ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ።
9እንዲህ አላቸው፣ "ጸሎታችሁን በፊቱ አቀርብ ዘንድ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣
10'በእናንተ ላይ ያመጣሁባችሁን ጥፋት እመልሳለሁና ተመልሳችሁ በዚህች ምድር ብትኖሩ፣እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፣ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም።
11የምትፈሩትን የባቢሎን ንጉሥ አትፍሩ። አድናችሁ ዘንድ፣ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ፣ ይላል እግዚአብሔር።
12ምሕረትን እሰጣችኋለሁና። እርሱ እንዲምራችሁ ወደ ምድራችሁም እንዲመልሳችሁ እኔ እራራላችኋለሁ።
13እናንተ ግን፣"በዚህች ምድር አንቀመጥም" ብትሉ፣ የእኔን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፣
14እናንተም፣ "አይሆንም! የትኛውንም ጦርነት ወደማናይባት፣ የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማባት፣ ወደማንራብባት ወደ ግብጽ ምድር እንሄዳለን። በዚያ እንኖራለን" ብትሉ፣
15አሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፣ እናንተ የይሁዳ ቅሬታ የሆናችሁ። የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ወደ ግብጽ እንድትገቡ፣ በዚያም እንድትኖሩ በእርግጥ ፊታችሁን ብታቀኑ፣
16ያኔ የምትፈሩት ሰይፍ በዚያ በግብጽ ምድር ያገኛችኋል። የምትደነግጡበት ረሃብ በዚያ በግብጽ ይደርስባቸኋል። በዚያም ትሞታላችሁ።
17ስለዚህ ወደ ግብጽ እንዲገቡ፣ በዚያም እንዲኖሩ ፊታቸውን የሚያቀኑ ሰዎች ሁሉ በሰይፍ፣ በረሃብ፣ ወይም በመቅሠፍት፣ ይሞታሉ። እኔም ከማመጣባቸው ክፉ ነገር ማንም አይተርፍም፣ ማንም አያመልጥም።
18የእስራኤል አምላክ፣የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላልና፦ ቊጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ፈሰሰ፣ እንዲሁ ወደ ግብጽ የምትገቡ ከሆነ መዓቴ ይፈስስባችኋል። እናንተም ለእርግማንና ለመደንገገጪያ፣ ለመረገሚያና ለመዋረጂያ ትሆናላችሁ። ደግሞም ይህንን ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩትም።"
19ከዚያም ኤርምያስ እንዲህ አለ፣ "እናንተ የይሁዳ ቅሬታዎች፣ እግዚአብሔር፣ ወደ ግብጽ አትሂዱ ብሎ ተናግሯችኋልና ዛሬ ምስክር እንደሆንኩባችሁ በእርግጥ እወቁ።
20'ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ። አምላካችንም እግዚአብሔር የሚናገርህን ሁሉ ንገረን፣ እኛም እንፈጽመዋለን' ብላችሁ ወደ እግዚአብሔር ወደ አምላካችሁ ስትልኩኝ የሕይወት ዋጋ የሚያስከፍላችሁን ነገር አድርጋችኋልና።
21እኔም ዛሬ ነግሬአችኋለሁ፣ ወደ እናንተም በላከኝ ነገር ሁሉ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁም።
22ስለዚህ፣ አሁንም ሄዳችሁ እንድትኖሩበት በወደዳችሁበት ስፍራ በሰይፍ፣ በራብ፣ በቸነፈር እንድትሞቱ በእርግጥ እወቁ።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።