መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 41

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በሰባተኛውም ወር ከመንግሥት ወገንና፣ ከንጉሡ ዋና ዋና አለቆች አንዱ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ወደ ምጽጳ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ። በዚያም በምጽጳ በአንድ ላይ እንጀራ በሉ።
2የናታንያም ልጅ እስማኤል፣ ከእርሱም ጋር የነበሩት ዐሥሩ ሰዎች ተነሥተው የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱ። የባቢሎን ንጉሥ በአገሩ ላይ የሾመውን እስማኤል ገደለው።
3ከዚያም እስማኤል ከጎዶልያስ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፣ በዚያም የተገኙትን የከለዳውያንን ሰልፈኞች ሁሉ ገደላቸው።
4ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ ሁለት ቀን ሆነ፣ ነገር ግን ማንም አላወቀም ነበር።
5ጢማቸውን ላጭተው፣ ልብሳቸውንም ቀድደው፣ ገላቸውንም ነጭተው፣ ወደ እግዚአብሔር ቤት ያቀርቡ ዘንድ የእህል ቍርባንና ዕጣን በእጃቸው እየያዙ፣ ሰማንያ ሰዎች ከሴኬም፣ ከሴሎና፣ ከሰማርያ መጡ።
6የናታንያም ልጅ እስማኤል ከምጽጳ ወጥቶ እያለቀሰ ሊገናኛቸው ሄደ። ባገኛቸውም ጊዜ፣ "ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ!" አላቸው።
7ወደ ከተማም መካከል በመጡ ጊዜ፣ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች አረዷቸውና በጉድጓድ ውስጥ ጣሉአቸው።
8ነገር ግን በመካከላቸው እስማኤልን፣ "የምንሰጥህ በሜዳ የተሸሸገ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዘይትና፣ ማር ስላለን አትግደለን" የሚሉት ዐሥር ሰዎች ነበሩ። እርሱም ከሌሎች ወዳጆቻቸው ጋር አልገደላቸውም።
9ጉድጓዱ እስማኤል ከጎዶልያስ ጋር የገደላቸውን የሰዎች ሬሳ ሁሉ የጣለበት ጕድጓድ ነበር። ይህ ጥልቅ ጉድጓድ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ የሠራው ጉድጓድ ነበረ። የናታንያም ልጅ እስማኤል የገደላቸውን ሞላበት።
10ቀጥሎ እስማኤል በምጽጳ የነበረውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፣ የንጉሡን ሴቶች ልጆች፣ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ የሰጠውን በምጽጳ የቀሩትን ሕዝብ ሁሉ ማረካቸው። ስለዚህ የናታንያም ልጅ እስማኤል ማርኮ ወደ አሞን ልጆች ይሄድ ዘንድ ተነሣ።
11የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ ከእርሱም ጋር የነበሩት የጭፍራ አለቆች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል ያደረገውን ክፋት ሁሉ ሰሙ።
12ስለዚህ ሰዎቻቸውን ሁሉ ይዘው ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ጋር ሊዋጉ ሄዱ። በገባዖንም ባለው በታላቁ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አገኙት።
13ከዚያም ከእስማኤል ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን፣ ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆችን ሁሉ ሲያዩ እጅግ ደስ አላቸው።
14ስለዚህ እስማኤል ከምጽጳ የማረካቸው ሕዝብ ሁሉ ዞረው ወደ ቃሬያም ልጅ ወደ ዮሐናን ሄዱ።
15ነገር ግን የናታንያ ልጅ እስማኤል ከስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ። ወደ አሞንም ሕዝቦች ሄደ።
16የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ ከእርሱም ጋር የነበሩት የጭፍራ አለቆች ሁሉ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምጽጳ ከገደለው በኋላ ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ያስመለሱአቸውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፣ ከገባዖን ያስመለሱአቸውን ሰልፈኞች፣ ሴቶችንም፣ ልጆችንም፣ ጃንደረቦችንም፣ ወሰዱ።
17ከዚያም ሄደው ለተወሰነ ጊዜ በቤተልሔም አቅራቢያ ባለው በጌሮት ከመዓም ተቀመጡ። ሊሄዱ የነበረው ወደ ግብጽ ነበር።
18ይህም ከከለዳውያን ፍርሃት የተነሣ ነበር። የባቢሎን ንጉሥ በአገሩ ላይ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን እስማኤል ስለ ገደለው ፈሯቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።