1ወደ ባቢሎን በተማረኩት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምርኮኞች መካከል የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን፣ከራማ ከለቀቀው በኋላ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጥቶ የነበረው ቃል ይህ ነው። ኤርምያስ ተወስዶ የነበረው ወደዚህ ቦታ የነበረ ሲሆን፣ እርሱም በሠንሰለት ታስሮ ነበር። እርሱ በምርኮ ከተወሰዱት የኢየሩሳሌም እና ይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ መካከል አንዱ ነበር።
2የዘበኞቹም አለቃ ኤርምያስን ወሰደውና እንዲህ አለው፣ "አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ ተናገረ።
3ስለዚህ እግዚአብሔር ነገሩን አመጣው። እናንተ ሕዝቦች በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርታችኋልና፣ እንደ ተናገረው አደረገ። ይህ ነገር እየሆነባችሁ ያለው፣ ቃሉን አልሰማችሁምና ነው።
4አሁን ግን ተመልከት! እጅህ የታሰረችበትን ሰንሰለት ዛሬ ፈታሁልህ። ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት በዐይኖችህ ዘንድ መልካም መስሎ ቢታይህ፣ ና፣ እኔም እንከባከብሃለሁ። ነገር ግን ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣቱ በዐይኖችህ ዘንድ መልካም መስሎ ባይታይህ ግን፣ አትምጣ። በፊትህ ያለችውን ምድር ሁሉ ተመልከት። በዐይኖችህ ዘንድ ልትሄድበት መልካም መስሎ ወደሚታይህና ትክክል ወደሚመስልህ ስፍራ ሂድ።"
5እርሱም ገና መልስ ሳይሰጥ፣ ናቡከደነፆር "የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን ልጅ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ተመለስ። ከእርሱም ጋር በሕዝቡ መካከል ተቀመጥ ወይም ልትሄድበት ደስ ወደሚያሰኝህ ስፍራ ሁሉ ሂድ" አለው። የዘበኞቹም አለቃ የምግብ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶ አሰናበተው።
6ስለዚህ ኤርምያስ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ ሄደ። ከእርሱም ጋር በአገሩ ውስጥ በቀሩት ሕዝብ መካከል ተቀመጠ።
7በየገጠሩ የነበሩት የጭፍራ አለቆችና ሰዎቻቸው ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምድር ላይ እንደ ሾመ ሰሙ። እንዲሁም ወደ ባቢሎን ያልተማረኩ የምድሪቱ ድሆች የሆኑት ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ላይ እንደሾመው ሰሙ።
8ስለዚህ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ። እነዚህም ሰዎች የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያም ልጅ ዮሐናንና ዮናታን፣ የተንሑሜትም ልጅ ሠራያ፣ የነጦፋዊውም የዮፌ ልጆች፣ የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ፣ እነርሱና ሰዎቻቸው ነበሩ።
9የሳፋንም ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው ማለ፣ እንዲህም አላቸው፣ "ለከለዳውያን አለቆች ለማገልገል አትፍሩ። በምድሪቱ ላይ ተቀመጡ ለባቢሎንም ንጉሥ አገልግሉ፣ መልካምም ይሆንላችኋል።
10ተመልከቱ፣ ወደ እኛ ከሚመጡት ከለዳውያን ጋር ለመገናኘት ምጽጳ ውስጥ እኖራለሁ፤ እናንተ ግን ወይንን፣ የበጋ ፍሬንና፣ ዘይትን በየዕቃዎቻችሁ አከማቹ። በያዛችኋቸውም ከተሞቻችሁ ውስጥ ኑሩ።"
11በሞዓብ፣ በአሞንም ልጆች መካከል፣ እንዲሁም በኤዶምያስና በእያንዳንዱ ምድር ሁሉ ላይ የነበሩ አይሁድ ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የይሁዳን ቅሬታ እንዳስቀረ፣ የሳፋንንም ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው እንደ ሾመው ሰሙ።
12ስለዚህ አይሁድ ሁሉ ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ ተመለሱ። ጎዶልያስ ወዳለበት፣ ወደ ይሁዳ ምድር፣ ወደ ምጽጳ መጡ። ወይንና የበጋንም ፍሬ በመሰብሰብ እጅግ ብዙ አከማቹ።
13የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ በየገጠሩም የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ።
14"የአሞን ልጆች ንጉሥ በኣሊስ ይገድልህ ዘንድ የናታንያን ልጅ እስማኤልን እንደ ሰደደ ታውቃለህን?" አሉት። የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን አላመናቸውም።
15ስለዚህ፣ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ምጽጳ ላይ ጎዶሊያስን እንዲህ በማለት በሚስጢር አነጋገረው፣"ሄጄ ማንም ሳያውቅ የናታንያን ልጅ እስማኤልን እንድገድለው ፍቀድልኝ። ማንም አይጠረጥረኝም። ሊገድልህ የሚገባው ለምንድነው? ወደ አንተ የተሰበሰቡ አይሁድ ሁሉ እንዲበተኑ፣ የይሁዳም ቅሬታ እንዲጠፋ ለምን ትፈቅዳለህ?"
16ነገር ግን የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን፣ "በእስማኤል ላይ ሐሰት ተናግረሃልና ይህን ነገር አታድርግ" አለው።