1ኢየሩሳሌምም በተያዘች ጊዜ፣ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት።
2በሴዴቅያስም በዐሥራ አንደኛው ዓመትና በአራተኛው ወር ከወሩም በዘጠነኛው ቀን ከተማይቱ ተሰበረች።
3ከዚያም የባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ፣ ኤርጌል ሳራስር፣ ሳምጋርናቦና፣ ዋና አለቃው ሠርሰኪም፤ ኤርጌል ሳራስር በከፍተኛ ደረጃ ያለ አለቃ ነበርና ከቀሩት የባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ ጋር ገብተው በመካከለኛው በር ውስጥ ተቀመጡ።
4የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ፣ ሰልፈኞቹም ሁሉ፣ ባዩአቸው ጊዜ ሸሹ። በሌሊትም በንጉሡ አትክልት መንገድ በሁለቱ ቅጥር መካከል ከነበረው ደጅ ከከተማይቱ ወጡ። ንጉሡ በዓረባ መንገድ ወጣ።
5ነገር ግን የከለዳውያን ሠራዊት ተከታተላቸውና ሴዴቅያስን በኢያሪኮ ሜዳ አቅራቢያ ባሉት የዮርዳኖስ ሸለቆ ሜዳዎች ላይ አገኙት። ከዚያም ይዘውት በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፣ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ።
6የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች በገዛ ዐይኑ ፊት በሪብላ አረዳቸው። እርሱም የይሁዳን ከበርቴዎች ሁሉ ገደለ።
7ከዚያም የሴዴቅያስን ዐይን አወጣና ወደ ባቢሎን ሊወስደው በመዳብ ሰንሰለት አሰረው።
8ከዚያም ከለዳውያን የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ። የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ።
9የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ የቀሩትን ሕዝብ፣ ወደ እርሱም የኰበለሉትን ሰዎች፣ የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማረካቸው።
10አንዳች የሌላቸውን የሕዝቡን ድሆች ግን የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን በይሁዳ አገር ተዋቸው። የወይኑን ቦታና እርሻውን በዚያው ቀን ሰጣቸው።
11የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ ኤርምያስ፣
12"ውሰደውና በመልካም ተንከባከበው። አትጉዳው። የሚነግርህንም የትኛውንም ነገር አድርግለት።" ብሎ የዘበኞቹን አለቃ ናቡዘረዳንን አዘዘ።
13ስለዚህ የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ላከ፣ የጃንደረቦች አለቃ ናቡሽዝባን፣ ዋናው አለቃ ራፋስቂስም ኤርጌል ሳራስርም፣ ራብማግም የባቢሎንም ንጉሥ ዋና ዋና አለቆች ሁሉ ሰዎችን ላኩ።
14ሰዎቻቸውም ኤርምያስን ከግዞት ቤት አደባባይ አወጡት፣ ወደ ቤቱም ይወስደው ዘንድ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፤ ስለዚህ ኤርምያስ በሕዝብ መካከል ተቀመጠ።
15በግዞትም ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፣
16"ለኩሻዊው ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው፣ 'የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፦ ተመልከት፣ ለበጎነት ሳይሆን ለጥፋት ቃሌን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ። በዚያም ቀን በፊትህ እውነት ሆኖ ይፈጸማል።
17ነገር ግን በዚያ ቀን እታደግሃለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም።
18በእርግ አድንሃለሁ ነፍስህም እንደ ምርኮ ትሆንልሃለች እንጂ በሰይፍ አትወድቅም። በእኔ ታምነሃልና፣ ይላል እግዚአብሔር።"