1ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ስፋጥያስ፣ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፣ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፣ የመልክያም ልጅ ጳስኮር ሰሙ። ኤርምያስ እንዲህ ሲል ነበር፣
2"እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህች ከተማ የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው በሰይፍ፣ በራብ፣ በመቅሠፍትም ይሞታል። ወደ ከለዳውያን የሚወጣ ግን በሕይወት ይኖራል። ሕይወቱንም ያስመልጣል፣ በሕይወትም ይኖራል።
3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በእርግጥ ትሰጣለች፣ እርሱም ይይዛታል።"
4ስለዚህ አለቆቹ ለንጉሡ እንዲህ አሉት፣ "ይህን የመሰለውን ቃል ሲነግራቸው በዚህች ከተማ የቀሩትን የሰልፈኞቹን እጅ የሕዝቡንም ሁሉ እጅ ያደክማልና ይህ ሰው ይገደል። ይህ ሰው ጥፋትን እንጂ ለዚህ ሕዝብ ሰላምን አያበጅለትምና እነዚህን ቃሎች እየተናገረ ነው።
5ስለዚህ ንጉሡ ሴዴቅያስ፣ "ተመልከቱ፣ እናንተን የሚቋቋም ንጉሥ የለምና፣ በእጃችሁ ነው" አለ።
6ከዚያም ኤርምያስን ወሰዱትና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጕድጓድ ጣሉት። ጉድጓዱ በእስር ቤቱ አደባባይ ነበረ። ኤርምያስንም በገመድ አወረዱት። በጕድጓድም ውስጥ ውኃ አልነበረበትም፣ ነገር ግን ጭቃማ ነበርና ኤርምያስ ጭቃው ውስጥ ገባ።
7ኩሻዊ የሆነው አቤሜሌክ በንጉሡም ቤት ከነበሩት ጃንደረቦች አንዱ ነበር። ኤርምያስን በጕድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር።
8ስለዚህ አቤሜሌክ ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ከንጉሡ ጋር ተነጋገረ።
9"ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች ነቢዮን ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ በመጣላቸው ክፉ አድርገዋል። በከተማይቱም ውስጥ እንጀራ ስለሌለ በዚያ በራብ እንዲሞት ወደ ጉድጓድ ጥለውታል።"
10ከዚያም ንጉሡ ለኩሻዊው አቤሜሌክ ትእዛዝ ሰጠ። "ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፣ ነብዩ ኤርምያስ ሳይሞት በፊት ከጕድጓድ አውጣው" ብሎ አዘዘው።
11ስለዚህ አቤሜሌክ ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደና ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደ ነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ። ከዚያም አሮጌ ጨርቅና እላቂ ልብስ ወሰደና ወደ ኤርምያስ ወደ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አወረደው።
12ኩሻዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን፣ "ይህን አሮጌ ጨርቅና እላቂውን ልብስ በብብትህ እና ከገመዱ በታች አድርግ" አለው። ስለዚህ ኤርምያስ እንዲሁ አደረገ።
13ከዚያም ኤርምያስን በገመዱ ጐተቱት። በዚህ መልኩ ከጕድጓድ አወጡት። ስለዚህ ኤርምያስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።
14ከዚያም ንጉሡ ሴዴቅያስ ልኮ በእግዚአብሔር ቤት ወደ ነበረው፣ ወደ ሦስተኛው መግቢያ፣ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው። ንጉሡም ኤርምያስን፣ "አንዲት ነገር ልጠይቅህ እፈልጋለሁ። መልሱን አትደብቅብኝ" አለው።
15ኤርምያስም ሴዴቅያስን፣ "ብመልስልህ፣ በእርግጥ አትገድለኝምን? ምክር ብሰጥህም፣ አትሰማኝም" አለው።
16ንጉሡ ሴዴቅያስ ግን "እኛን የፈጠረንን ሕያው እግዚአብሔርን፣ አልገድልህም፣ ወይም ነፍስህን ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም" ብሎ በድብቅ ለኤርምያስ ማለ።
17ስለዚህ ኤርምያስ ሴዴቅያስን፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት አምላክ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ብትወጣ፣ በሕይወት ትኖራለህ፣ ይህችም ከተማ አትቃጠልም። አንተና ቤተሰብህ በሕይወት ትኖራላችሁ።
18ነገር ግን ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፣ ይህች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች። በእሳትም ያቃጥሉአታል፣ አንተም ከእጃቸው አታመልጥም" አለው።
19ንጉሡ ሴዴቅያስም ኤርምያስን፣ "ነገር ግን ወደ ከለዳውያን ክፉኛ እንዲያፌዙብኝ፣ በኰበለሉት በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል ብዬ እፈራለሁ" አለው።
20ኤርምያስም እንዲህ አለው፣ "ለእነርሱ አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ እየነገርኩህ ያለሁትን የእግዚአብሔርን መልእክት ታዘዝ፤ ነገሮችም መልካም ይሆኑልሃል፣ በሕይወትም ትኖራለህ።
21ነገር ግን ትወጣ ዘንድ እንቢ ብትል፣ እግዚአብሔር ያሳየኝ ይህንን ነው፦
22ተመልከት! በይሁዳ ንጉሥ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ። እነዚያም ሴቶች ለአንተ፣ "ወዳጆችህ አታልለውሃል፤ አበላሽተውህማል። እግሮችህ ግን አሁን በጭቃ ውስጥ ሰጥመዋል፣ ወዳጆችህም ይሸሻሉ።'
23ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፣ አንተም ራስህ አታመልጥም። በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።"
24ከዚያም ሴዴቅያስ ኤርምያስን እንዲህ አለው፣ "እንዳትሞት ስለእነዚህ ቃሎች ለማንም አትናገር።
25አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ከሰሙ፣ ወደ አንተ መጥተው፣ 'ለንጉሡ የነገርከውን ንገረን። ከእኛም አትሸሽገን፣ አሊያ እንገድልሃለን። ንጉሡ ደግሞ ያለህን ንገረን' ቢሉህ፣
26ያን ጊዜ 'በዚያ እሞት ዘንድ ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ' ብዬ በንጉሡ ፊት ለመንሁ" በላቸው።
27ከዚያም አለቆቹ ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት፣ ንጉሡም እንዳዘዘው እንደዚህ ቃል ሁሉ ነገራቸው። በኤርምያስና በንጉሡ መካከል የነበረው ውይይት አልተሰማምና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተዉ።
28ስለዚህ፣ ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ ኤርምያስ በእስር ቤት አደባባይ ተቀመጠ።