1የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ያነገሠው የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፋንታ ነገሠ።
2ነገር ግን ሴዴቅያስም ሆነ ባርያዎቹ፣ የአገሩም ሕዝብ በነቢዩ በኤርምያስ እጅ የተናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
3ስለዚህ፣ ንጉሡ ሴዴቅያስ፣ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ። እነርሱም "ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ" አሉት።
4በግዞት ቤት ገና አላገቡትም ነበርና ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይወጣና ይገባ ነበር።
5የፈርዖንም ሠራዊት ከግብጽ ወጣ፣ ኢየሩሳሌምንም ከብበዋት የነበሩ ከለዳውያን ይህን ወሬ በሰሙ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ተመለሱ።
6ከዚያም፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፣
7"የእስራኤል አምላክ፣ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፦ ከእኔ ትጠይቁ ዘንድ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ 'ተመልከቱ፣ ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደገዛ ምድሩ ወደ ግብጽ ይመለሳል።
8ከለዳውያንም ይመለሳሉ። ይህችን ከተማ ይዋጉአታል፣ ይይዟትማል፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።'
9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለማይሄዱ 'ከለዳውያን በእርግጥ ከእኛ ዘንድ ይሄዳሉ' ብላችሁ ራሳችሁን አታታልሉ።
10እናንተም የሚዋጉትን የከለዳውያንን ሠራዊት ሁሉ አሸንፋችሁ ቢሆን እንኳን፣ ከእነርሱም የቆሰሉት ብቻ በድንኳኖቻቸው ቀርተው ቢሆን ኖሮ፣ይህችን ከተማ በእሳት ባቃጠሉአት ነበር።
11ስለዚህ የከለዳውያን ሠራዊት ከፈርዖን ሠራዊት ፊት የተነሣ ከኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ፣
12ያኔ ኤርምያስ ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ከኢየሩሳሌም ወጣ። እርሱ የርስቱን እድል ፈንታ በዚያ ከሕዝቡ መካከል ይቀበል ዘንድ ፈለገ።
13በብንያምም በር በነበረ ጊዜ፣ የዘበኞች አለቃ በዚያ ነበር። ስሙም የሐናንያ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የሪያ ነበረ። እርሱም "ወደ ከለዳውያን መኰብለልህ ነው" ብሎ ነቢዩን ኤርምያስን ያዘው።
14ኤርምያስ ግን፣ "ይህ እውነት አይደለም። ወደ ከለዳውያን መኰብለሌ አይደለም" አለ። ነገር ግን የሪያ አልሰማውም። ኤርምያስንም ይዞ ወደ አለቆች አመጣው።
15አለቆችም በኤርምያስ ላይ ተቈጡ። መቱትና የጸሐፊውንም የዮናታንን ቤት እስር ቤት አድርገውት ነበርና በዚያ አኖሩት።
16ስለዚህ ኤርምያስ ብዙ ቀናት በተቀመጠበት ከምድር በታች ባለ ክፍል ተጣለ፤
17ከዚያም ንጉሡ ሴዴቅያስ አንድ ሰው ልኮ ወደ ቤተመንግሥት አስመጣው። ንጉሡም በቤቱ፣ "በውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ቃል አለን?" ብሎ በድብቅ ጠየቀው። ኤርምያስም፣ "አዎን አለ፦ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፈህ ትሰጣለህ" አለ።
18ከዚያም ኤርምያስ ንጉሡን ሴዴቅያስን፣"በእስር ቤት የጣላችሁኝ አንተን፣ ወይስ ባርያዎችህን፣ ወይስ ሕዝብህን ምን በድያችሁ ነው?
19የባቢሎን ንጉሥ በእናንተና በዚህች ምድር አይመጣባችሁም ብለው ትንቢት ይናገሩላችሁ የነበሩ ነቢያቶቻችሁ ወዴት አሉ?
20ንጉሡ ጌታዬ ሆይ፣ እንድትሰማኝ እለምንሃለሁ! ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ። በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ።"
21ስለዚህ ንጉሡ ሴዴቅያስ አዘዘ። አገልጋዮቹም ኤርምያስን በግዞት ቤት አደባባይ አኖሩት። እንጀራም ሁሉ ከከተማ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ ይሰጡት ነበር። ስለዚህ ኤርምያስ በእስር ቤት አደባባይ ተቀምጦ ነበር።