መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 36

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንዲህም ሆነ፣ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፣ እንዲህም አለው፣
2"ለራስህ አንድ የመጽሐፍ ጥቅልል ውሰድና በእስራኤልና በይሁዳ ላይ፣ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት። ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለአንተ የተናገርሁትን ጻፍበት።
3ምናልባት የይሁዳ ሕዝብ እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል። ከክፋ መንገዳቸው ይመለሱ፣ እኔም በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ።
4ኤርምያስም የኔርያን ልጅ ባሮክን ጠራ፣ ባሮክም ከኤርምያስ አፍ እግዚአብሔር ለእርሱ የተናገረውን ቃል ሁሉ በመጽሐፉ ጥቅልል ላይ ጻፈ።
5ቀጥሎም ኤርምያስ ለባሮክ እንዲህ ሲል አዘዘው። "እኔ በእስር ላይ ስለሆንኩ ወደ እግዚአብሔር ቤት መሄድ አልችልም።
6ስለዚህ አንተ መሄድና ከአፌም የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል ልታነብብ ይገባል። በጾም ቀን፣ በእግዚአብሔር ቤት ሕዝቡ እየሰሙ አንብብ፣ ደግሞም ከከተሞቻቸው የሚወጡ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እየሰሙ አንብበው። እነዚህን ቃሎች አውጅላቸው።
7ምናልባት የምሕረት ልመናቸው በእግዚአብሔር ፊት ትመጣ ይሆናል። እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና፣ ሁሉም ከክፉ መንገዱ ይመለስ ይሆናል።"
8ስለዚህ የኔርያም ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። በእግዚአብሔርም ቤት የእግዚአብሔርን ቃል በመጽሐፉ አነበበ።
9በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም አዋጅ ነገሩ።
10ባሮክም የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሔር ቤት በላይኛው አደባባይ በእግዚአብሔር ቤት በአዲሱ በር መግቢያ ባለው በጸሐፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ጓዳ ሕዝቡ ሁሉ እየሰሙ መጽሐፉን አነበበ።
11የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመጽሐፉ ጥቅልል ሰማ።
12ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ጸሐፊው ክፍል ወረደ። በዚያም፣ አለቆች ሁሉ፦ ጸሐፊው ኤሊሳማ፣ የሸማያ ልጅ ድላያ፣ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፣ የሳፋን ልጅ ገማርያ፣ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ፣ እንዲሁም አለቆቹ ሁሉ በዚያ ተቀምጠው ነበር።
13ሚክያስም ሕዝቡ እየሰሙ ባሮክ ከመጽሐፉ ባነበበ ጊዜ የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው።
14አለቆቹም ሁሉ፣ "በሕዝቡ ጆሮ ያነበብኸውን ጥቅልል በእጅህ ይዘህ ና" የሚል መልእክት በኵሲ ልጅ፣ በሰሌምያ ልጅ፣ በናታንያ ልጅ፣ በይሁዲ እጅ፣ ወደ ባሮክ ላኩ። ስለዚህ የኔርያ ልጅ ባሮክ ጥቅልሉን በእጁ ይዞ ወደ እነርሱ ሄደ።
15ከዚያም፣ "ተቀመጥና እየሰማንህም ይህንን አንብብልን፤" አሉት። ባሮክም በጆሮአቸው አነበበው።
16እነዚህን ቃሎች ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈሩና እርስ በእርሳቸው ተመካከሩ፣ ባሮክንም፣ "ይህን ቃል ሁሉ በእርግጥ ለንጉሡ ልንናገር ይገባል" አሉት።
17ከዚያም ባሮክን፣ "ይህን ሁሉ ቃላት ከኤርምያስ አፍ እንዴት እንደ ጻፍኸው ንገረን" ብለው ጠየቁት።
18ባሮክም፣ "ይህን ቃል ከአፉ ይነግረኝ ነበር፣ እኔም በመጽሐፍ ጥቅልል ላይ በቀለም እጽፍ ነበር" ብሎ መለሰላቸው።
19አለቆቹም ለባሮክ፣ "አንተና ኤርምያስ ሄዳችሁ ተሸሸጉ። የት እንደሆናችሁ ማንም አይወቅ" አሉት።
20ወደ ንጉሡም ሸንጎ ገቡና ቃሉን ሁሉ ንጉሡ እየሰማ ተናገሩ። ነገር ግን አስቀድመው ጥቅልሉን በጸሐፊው በኤሊሳማ ክፍል አኑረውት ነበር።
21ከዚያም ንጉሡ ጥቅልሉን ያመጣ ዘንድ ይሁዲን ላከ። እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ክፍል ወሰደው። ከዚያም ይሁዲ ንጉሡና በንጉሡ አጠገብ የቆሙት አለቆች ሁሉ እየሰሙ አነበበው።
22ያኔ፣ ንጉሡ በዘጠነኛው ወር በክረምት ቤት ተቀምጦ ነበር፣ በፊቱም በምድጃ ውስጥ እሳት ይነድድ ነበር።
23ይሁዲ ሦስት ወይም አራት ዓምድ ያህል ባነበበ ቍጥር፣ ንጉሡ በካራ እየቀደደ ጥቅልሉ በምድጃ ውስጥ ባለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወዳለው እሳት ጣለው።
24ነገር ግን ንጉሡ ወይም ይህንን ቃል ሁሉ የሰሙ ባሪያዎቹ ሁሉ አልፈሩም፣ ልብሳቸውንም አልቀደዱም።
25ነገር ግን ኤልናታን፣ ድላያና፣ ገማርያ ጥቅልሉን እንዳያቃጥል ንጉሡን ለመኑት፣ እርሱ ግን አልሰማቸውም።
26ንጉሡም ጸሐፊውን ባሮክንና ነብዩን ኤርምያስን ይይዙ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረሕምኤልን፣ የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያን፣ የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፣ እግዚአብሔር ግን ሰውሯቸው ነበር።
27ከዚያም ንጉሡ ጥቅልሉንና ባሮክ ከኤርምያስ አፍ እየቀዳ የጻፈውን ቃል ካቃጠለ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
28"ዳግመኛ ሌላ ጥቅልል ውሰድ፣ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው ጥቅልል ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃል ሁሉ ጻፍበት።
29ከዚያም፣ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን እንዲህ በለው፦ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ አንተ፣ "የባቢሎን ንጉሥ በእርግጥ ይመጣል ይህችንም አገር ያፈርሳታል ከሰውና ከእንስሳም ባዶ ያደርጋታል" ብለህ ለምን ጻፍህበት? ብለህ ይህን ጥቅልል አቃጥለሃል።"
30ስለዚህ፣ ስለ አንተ፣ የይሁዳ ንጉሥ፣ ስለ ኢዮአቄም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ "በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀማጭ አይኖርለትም። ሬሳውም በቀን ለትኩሳት፣ በሌሊትም ለውርጭ ይጣላል።
31ስለ ኃጢአታቸውም እርሱንና ዘሩን፣ ባሪያዎቹንም እቀጣለሁ። እነርሱም አልሰሙምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይና፣ በኢየሩሳሌም በሚቀመጡ፣ በይሁዳም ሰዎች ላይ አመጣለሁ።
32ሰለዚህ ኤርምያስ ሌላ ጥቅልል ወሰደ ለኔርያም ልጅ ለጸሐፊው ለባሮክ ሰጠው። እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፉን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ እየቀዳ ጻፈበት። በተጨማሪም፣ ከቀድሞው ቃል ጋር የሚመሳሰል ብዙ ቃል ተጨመረበት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።