መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 35

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በይሁዳ ንጉስ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፣ እንዲህም አለ፣
2"ወደ ሬካባውያን ወገን ሄደህ አነጋግራቸው። ወደ ቤቴ፣ ከክፍሎቹ ወደ አንዲቱ፣ አግባቸው የወይን ጠጅም አጠጣቸው።"
3የከባስንን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያን፣ እንዲሁም ወንድሞቹን፣ ልጆቹንም ሁሉ፣ ብሎም የሬካባውያንን ወገን ሁሉ ወሰድኋቸው።
4ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ጌዴልያ ልጅ ወደ ሐናን ልጆች ጓዳ ወሰድኳቸው። እነዚህ ክፍሎች የእግዚአብሔር ቤት በበረኛው በሰሎም ልጅ በመዕሤያ ጓዳ በላይ ባለው የአለቆች ክፍል አጠገብ ነበሩ።
5በሬካባውያንም ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አኑሬ፣ "ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጡ፤" አልኳቸው።
6እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፣ "የትኛውንም የወይን ጠጅ አንጠጣም፣ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ 'እናንተና ልጆቻችሁ ለዘላለም የወይን ጠጅ አትጠጡ' ብሎ አዝዞናልና።
7እንደ እንግዶች በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፣ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፣ የትኛውንም ዘር አትዝሩ፣ የትኛውንም ወይን አትትከሉ፣ ይህ ለእናንተ አይደለም።'
8እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል፤ እኛም፣ ሚስቶቻችንም፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም፣ ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም።
9የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም፣ የወይን ቦታና እርሻ ዘርም የለንም።
10በድንኳንም ውስጥ ኖረናል፣ አድምጠናል፣ አባታችንም ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ አድርገናል።
11ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ምድሪቱን ባጠቃ ጊዜ፣ 'ኑ ከከለዳውያን ሠራዊትና ከሦርያ ሠራዊት ፊት የተነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ' አልን። ስለዚህ በኢየሩሳሌም እየኖርን ነን።"
12ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፣
13"የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፣ 'ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ተናገር እንዲህም በላቸው፣ "ቃሌን ትሰሙ ዘንድ ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል እግዚአብሔር።
14ልጆቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ያዘዛቸው ቃል እስከ ዛሬ ድረስ ተፈጸመ። ለአባታቸውም ትእዛዝ ታዝዘዋል። እኔ ግን በተደጋጋሚ ተናግሬአችኋለሁ፣ ሆኖም አልሰማችሁኝም።
15'እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፣ ሥራችሁንም አሳምሩ፤ ታመልኩአቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፣ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ እያልሁ በተደጋጋሚ ባርያዎቼን፣ ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። እናንተ ግን ጆሯችሁን አላዘነበላችሁም፣ ወይም እኔንም አልሰማችሁኝም።
16የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ልጆች አባታቸው ያዘዛቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋልና፣ ይህ ሕዝብ ግን ሊሰማኝ አልፈለገም።"
17ስለዚህ፣ የእስራኤል አምላክና የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ተመልከቱ፣ በተናገርኋቸው ጊዜ አልሰሙምና፣ በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ፣ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ።"
18ኤርምያስም ለሬካባውያን ቤተሰብ እንዲህ አላቸው፣ "የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለአባታችሁ ለኢዮናዳብ ትእዛዝ ታዝዛችኋልና፣ ትእዛዙንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፣ ያዘዛችሁንም ፈጽማችኋልና፤
19ስለዚህ፣ 'በፊቴ የሚቆም ሰው፣ ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘላለም አይታጣም።" ይላል የሠራዊት አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።