መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 33

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኤርምያስ ገና በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል ሁለተኛ ጊዜ መጣለትና እንዲህ አለው፣
2"ስሙ እግዚአብሔር የሆነ፣ ያደረገው እግዚአብሔር፣ ያጸናውም ዘንድ የሠራው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
3'ወደ እኔ ጩኽ፣ እኔም እመልስልሃለሁ። አንተም የማታስተውለውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ።'
4የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፣ ለአፈር ድልድልና ለምሽግ ስለ ፈረሱ ስለዚህች ከተማ ቤቶች፣ ስለ ይሁዳም ነገሥታት ቤቶች እንዲህ ይላልና።
5'ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፊቴን ከዚህች ከተማ ስሰውር፣ ከለዳውያን ለመዋጋትና በቊጣዬ፣ እንዲሁም በመዓቴ በምገድላቸው ሰዎች ሬሳዎች ሊሞሏቸው እየመጡ ናቸው።
6ነገር ግን ተመልከቱ፣ ፈውስንና መድኃኒትን አመጣላታለሁ፣ እፈውሳቸውማለሁ፤ መትረፍረፍንም አመጣላቸዋለሁ፣ ሰላምንና የታማኝነትን ብዛት አመጣላቸዋለሁ።
7የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልን ምርኮ መልሼ አመጣለሁ፣ ቀድሞም እንደ ነበሩ አድርጌ እሠራቸዋለሁ።
8እኔንም ከበደሉበት ኃጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ። እኔንም የበደሉበትን ያመፀብኝንም ኃጢአታቸውን ሁሉ ይቅር እላለሁ።
9ይህችም ከተማ እኔ የምሠራላቸውን በጎነት ሁሉ በሚሰሙ እኔም ስላመጣሁላቸው መልካምነትና ሰላም ሁሉ በሚፈሩና በሚደነግጡ አሕዛብ ሁሉ ፊት ለደስታ ስም ለምስጋናም ለክብርም ትሆናለች።
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ እናንተ፣ "ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት በምትሉአት በዚህች ስፍራ፣ የሚቀመጥባቸው በሌላ፣ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባድማ በሆኑ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ጥፋት ሆኗል።"
11የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፣ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ፣ "እግዚአብሔር ቸር ነውና፣ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ" የሚሉ ድምፅ በድጋሚ ይሰማል። ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት አምጡ፣ የምድርን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፣' ይላል እግዚአብሔር።
12የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 'ባድማ ሆኖ፣ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባለው በዚህ ስፍራ፣ በከተሞችም ሁሉ መንጎቻቸውን የሚያሳርፉት የእረኞች መኖሪያ ይሆናል።
13በደጋው ላይ ባሉ ከተሞች፣ በቈላውም ባሉ ከተሞች፣ በደቡብም ባሉ ከተሞች፣ እንዲሁም በብንያምም ምድር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፣ በይሁዳም ከተሞች መንጎቹ በተቈጣጣሪው እጅ እንደ ገና ያልፋሉ፣' ይላል እግዚአብሔር።
14'ተመልከቱ! ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፤ ይላል እግዚአብሔር።
15በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፣ እርሱም ፍትህንና ጽድቅን በምድር ላይ ያደርጋል።
16በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም በአስተማማኝ ሁኔታ ትቀመጣለች፤ የምትጠራበትም ስም፣ "እግዚአብሔር ጽድቃችን" ተብሎ ነው።
17እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ 'በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዳዊት ዘንድ አይታጣም፤
18የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ፣ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል፣ ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም።"
19የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፣
20"እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 'ቀንና ሌሊት በወራቱ እንዳይሆን የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፣
21ያኔ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ ከእንግዲህ እንዳይሆንለት ከባሪዬ ከዳዊት ጋር፣ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል።
22የሰማይ ሠራዊት መቍጠር፣ የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፣ እንዲሁ የባሪያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ።"
23የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፣
24"ይህ ሕዝብ፣ 'እግዚአብሔር መርጧቸው የነበሩትን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል፤' ያለውን ነገር አትመለከትምን? በዚህ መልኩ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ እንዳይሆን ሕዝቤን አቃልለዋል።
25እኔ፣ እግዚአብሔር እንዲህ እላለሁ፣ 'የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔ የማይኖሩ ከሆነ፣ ወይም የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያልጠበቅሁ እንደሆነ፣
26ያን ጊዜ በአብርሃም፣ በይስሐቅና፣ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች ይሆኑ ዘንድ ከዘሩ እንዳልወስድ፣ የያዕቆብንና የባሪያዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ። ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፣ እምራቸውማለሁና።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።