1በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዐሥረኛው ዓመት፣ በናቡክደነፆር በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።
2በዚያን ጊዜ፣ የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩም ኤርምያስ በይሁዳ ንጉሥ ቤት በነበረው በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ነበር።
3የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በእስር አቆይቶት እንዲህ አለው፣ "ለምን እንዲህ ብለህ ትንቢት ትናገራለህ፣ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከት፣ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፣ እርሱም ይይዛታል።
4የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፣ በእውነት በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፣ አፉ ለአፉ ይናገረዋል፣ ዐይኑም የንጉሡን ዐይን ያያል።
5ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ይሄዳል፣ እኔም እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይሆናል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ከከለዳውያን ጋር ብትዋጉ አይሳካላችሁም።"
6ኤርምያስም እንዲህ አለ፣ "የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፣
7'ተመልከቱ፣ የአጐትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፣ "ትገዛው ዘንድ መቤዠቱ የአንተ ነውና በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ ይልሃል።"
8ከዚያም፣ እግዚአብሔር እንደተናገረው ቃል፣ የአጐቴ ልጅ አናምኤል እኔ ወዳለሁበት ወደ ግዞቱ ቤት አደባባይ መጥቶ እንዲህ አለኝ፣ 'በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን፣ እባክህ ግዛ፤ የርስት መብቱ የአንተ ነውና፣ የመቤዠቱ መብትም የአንተ ነውና ለአንተ ግዛው።' ያን ጊዜ ይህ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ አወቅሁ።
9ስለዚህ፣ በዓናቶት ያለውን እርሻ ከአጐቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፣ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት።
10በውሉም ወረቀት ላይ ፈረምሁ አተምሁትም፣ ምስክሮችም እንዲመሰክሩ አስደረግሁ። ከዚያም ብሩን በሚዛን መዘንሁለት።
11ቀጥሎ፣ የታተመውንና የተከፈተውን የግዢ ውል ወረቀት ወሰድሁ፤
12የአጐቴም ልጅ አናምኤል፣ የውሉንም ወረቀት የፈረሙ ምስክሮች፣ በግዞትም ቤት አደባባይ የተቀመጡ አይሁድ ሁሉ እያዩ የውሉን ወረቀት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።
13በፊታቸውም እንዲህ ብዬ ባሮክን አዘዝሁት።
14'የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፡- የታተመውንና የተከፈተውን ይህን የውል ወረቀት ውሰድ። ብዙ ቀን እንደተጠበቊ እንዲቆዩ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው።
15የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰዎች በዚህች ምድር ቤትን፣ እርሻን፣ የወይን ቦታንም እንደ ገና ይገዛሉ።'
16ለኔርያ ልጅ ለባሮክም የውሉን ወረቀት ከሰጠሁት በኋላ፣ እንዲህ ብዬ ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፣
17'ወዮ፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ተመልከቱ! አንተ ብቻህን ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል። ለአንተም እንደሚያቅትህ የተናገርከው ነገር የለም።
18ለብዙ ሺህ ምሕረት ታደርጋለህ፣ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ጭን ላይ ትመልሳለህ። ስምህ ታላቅና ኃያል አምላክ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
19በጥበብ ታላቅ በአደራረግም ብርቱ ነህ፣ ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ትሰጥ ዘንድ ዐይኖችህ በሰዎች መንገድ ሁሉ ላይ ተገልጠዋል።
20እስከ ዛሬም ድረስ ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብጽ ምድር አድርገሃል። እስከዛሬ ድረስ፣ በዚህ በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች ሁሉ መካከል ስምህን አግንነሃል።
21በምልክትና በድንቅ ነገር፣ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አውጥተሃልና።
22ከዚያም ትሰጣቸውም ዘንድ ለአባቶቻቸው የማልህላቸውን፣ ወተትና ማርን የምታፈስሰውን ምድር፣ ሰጠሃቸው።
23እነርሱም ገብተው ወረሱአት። ነገር ግን ቃልህን አልሰሙም ለሕግህም በመታዘዝ አልሄዱም። ይደረግ ዘንድ ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፣ ስለዚህ ይህን ጥፋት ሁሉ አመጣህባቸው።
24ተመልከቱ! የአፈር ድልድል ሊይዙአት እስከ ከተማይቱ ድረስ ቀርበዋል። ከሰይፍ፣ ከራብና፣ ከመቅሠፍት የተነሣ፣ ከተማይቱ ለሚዋጓት ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች። እንደሚሆን የተናገርኸው ሆኖአልና፣ ደግሞም ተመልከቱ፣ አንተ ታየዋለህ።
25ከዚያም አንተ ራስህ፣ "ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ምንም እንኳን ይህች ከተማ ለከለዳውያን እጅ ተላልፋ የምትሰጥ ቢሆንም፣ እርሻውን በብር ግዛ ምስክሮችንም ጥራ" አልኸኝ።
26ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፣ እንዲህም አለ፣
27"ተመልከቱ! የሰው ዘር ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። እፈጽመው ዘንድ የሚያቅተኝ ነገር አለን?
28ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ተመልከቱ፣ ይህችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ። እርሱም ይይዛታል።
29ይህችን ከተማ የሚወጉ ከለዳውያን መጥተው በእሳት ያነድዱአታል፣ ያስቈጡኝም ዘንድ በሰገነታቸው ላይ ለበኣል ካጠኑባቸው፣ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቊርባን ካፈሰሱባቸው ቤቶች ጋር ያቃጥሉአታል።
30የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች ከወጣትነታቸው ጀምሮ በዐይኔ ፊት ክፉ ነገርን ብቻ አድርገዋል። የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደረጉምና፣ ይላል እግዚአብሔር።
31ከፊቴ አስወግዳት ዘንድ ይህች ከተማ ከገነቧት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቍጣዬንና መዓቴን ለማነሣሣት ሆናለችና። ስለዚህም ከፊቴ አስወግዳታለሁ።
32ምክንያቱም እኔን ያስቈጡኝ ዘንድ፣ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው፣ አለቆቻቸውም፣ ካህናቶቻቸውም፣ ነቢያቶቻቸውም፣ የይሁዳም ሰዎች፣ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ፣ ስላደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው።
33ምንም እንኳን በጉጉት ያስተማርኳቸው ቢሆንም፣ ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ። ላስተምራቸው ሞከርኩ፣ ነገር ግን ተግሣጽን ይቀበሉ ዘንድ አንዳቸውም እንኳን አልሰሙም።
34ከዚያም፣ ያረክሱት ዘንድ፣ ስሜ በተጠራበት ቤት ውስጥ ርኩሰታቸውን አኖሩ።
35ቀጥሎም ይሁዳን ኃጢአት እንዲሠራ ለማድረግ፣ ይህንን ርኩሰት ያደርጉ ዘንድ፣ እኔ ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን ነገር፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ በእሳት ያሳልፉ ዘንድ፣ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን የበኣልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠሩ።
36አሁን እንግዲህ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፣ አንተ ስለ እርስዋ፣ 'በሰይፍና በራብ በመቅሰፍትም ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ተሰጥታለች' ስለምትላት ከተማ እንዲህ ይላል።
37ተመልከቱ፣ በቍጣዬ፣ በመዓቴና በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት አገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ። ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፣ ተዘልለውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ።
38ከዚያም እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፣ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
39ለእነርሱም፣ ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘላለም እንዲፈሩኝ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ።
40ለእነርሱም ከማደርገው በጎነት አልመለስም ስል፣ ከእነርሱ ጋር የዘላለምን ቃል ኪዳን እገባለሁ። መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ። ከዚህ የተነሣ እኔን ከመከተል አይመለሱም።
41ከዚያም ለእነርሱ መልካምን በማድረግ ደስ ይለኛል። በታማኝነት በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።
42እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ 'ይህን እጅግ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፣ እንዲሁ እንደማደርግላቸው የተናገርሁላቸውን በጎነት ሁሉ አመጣላቸዋለሁ።
43ከዚያም፣ እናንተ፣ "ይህች ያለ ሰውና ያለ እንሰሳ ያለች ባድማ ምድር ናት። ለከለዳውያንም እጅ ተሰጥታለች።" በምትሉአት ምድር እርሻን ይገዛሉ።
44ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና፣ በብንያም አገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፣ በይሁዳም ከተሞች በደጋውም ባሉ ከተሞች በቈላውም ባሉ ከተሞች፣ በደቡብም ባሉ ከተሞች፣ ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ በውሉም ወረቀት ፈርመው ያትማሉ ምስክሮችንም ይጠራሉ።"