መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 31

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1"በዚያን ዘመን፣ ይላል እግዚአብሔር፣ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።"
2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "እስራኤልን ለማረድ ከመጣው ሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ።"
3እግዚአብሔር በኃላፊው ጊዜ ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፣ "እስራኤል ሆይ፣ በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ። ስለዚህ በኪዳን ታማኝነት ወደራሴ ሳብሁሽ።
4የእስራኤል ድንግል ሆይ፣ እንደ ገና እገነባሻለሁ አንቺም ትገነቢያለሽ። እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ደስታ ጭፈራሽ ትወጫለሽ።
5እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ቦታዎችን ትተክያለሽ፤ ገበሬዎች ይተክላሉ፣ ፍሬውንም በመልካም ይጠቀሙበታል።
6በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ተመልካቾች፣ 'ተነሡ፣ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ.' ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣልና።"
7እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ "ስለ ያዕቆብ በደስታ ጩኹ! ስለ አሕዛብም አለቆች በደስታ ጩኹ! ምስጋና ይሰማ። 'እግዚአብሔር ሕዝቡን፣ የእስራኤልን ቅሬታ አድኖአል' በሉ።
8ተመልከቱ፣ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ። ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ። በመካከላቸውም ዕውሩና አንካሳው፣ ያረገዙ ሴቶችና ሊወልዱ ያሉ ሴቶች በአንድነት ይሆናሉ። ታላቅ ጉባኤ ሆነው ወደዚህ ይመለሳሉ።
9በልቅሶ መጡ፤ ልመናቸውን ሲያደርጉ እመራቸዋልሁ። በወንዝ ዳር በቀጥተኛ መንገድ አስኬዳቸዋለሁ። በእርሱም አይሰናከሉም፣ እኔ ለእስራኤል አባት እሆናለሁና፣ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና።"
10"አሕዛብ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፣ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩ። እናንተ አህዛብ፣ "እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስባታል፣ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቃታል" በሉ።
11እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶታል፣ ከበረታበትም እጅ አድኖታል።
12ከዚያም ይመጡና በጽዮን ተራራ ይፈነድቃሉ። ወደ እግዚአብሔርም መልካምነት፣ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ፣ ወደ ዘይትም፣ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ይሰበሰባሉ። ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፣ ከእንግዲህም ወዲህ ኃዘን አይሰማቸውም።
13በዚያን ጊዜ ደናግሉ በዘፈን ደስ ይላቸዋል፣ ወጣቶቹና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ይሆናሉ። ለቅሷቸውን ወደ ክብረ-በዓል እለውጣለሁና። እራራላቸዋለሁ፣ ከኅዘናቸውም ይልቅ እንዲፈነድቁ አደርጋቸዋለሁ።
14ከዚያም የካህናቱን ነፍስ በብዛት አረካታለሁ። ሕዝቤም መልካምነቴን ይጠግባል ይላል እግዚአብሔር።"
15እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "የዋይታና የመራራ ለቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ። ስለ ልጆችዋ የምታለቅሰው ራሔል ናት። ከእንግዲህ አይኖሩምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች።"
16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ድምፅሽን ከለቅሶ፣ ዐይንሽንም ከእንባ ከልክዪ፤ ምክንያቱም ለመከራሽ ካሳ አለ፤ ልጆችሽ ከጠላት ምድር ይመለሳሉ።
17ለፍጻሜሽ ተስፋ አለ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ልጆችሽም ወደ ዳርቻቸው ይመለሳሉ።"
18"ኤፍሬም፣ 'ቀጣኸኝ፣ እኔም ተቀጣሁ። እንዳልተገራ ወይፈን መልሰህ አምጣኝ፣ አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና እኔም እመለሳለሁ።
19ወደ አንተ ከተመለስሁ በኋላ፣ ተጸጸትሁ፤ ከሠለጠንሁም በኋላ፣ በኃዘን ጭኔን መታሁ፤ በወጣትነቴ በደልን ተሸክሜአለሁና አፈርሁ፣ ተዋረድሁ።'
20ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ አይደለምን? ወይስ የምደሰትበት ሕጻን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር፣ እንደዚያም ሆኖ በፍቅር አስበዋለሁ። በዚህ መልኩ ልቤ ትናፍቀዋለች። በእርግጥም እራራለታለሁ ይላል እግዚአብሔር።"
21ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ። ለራስሽም መንገድን የሚመሩ ዓምዶችን ትከዪ። አሳብሽንም ልትሄጂበት ወደሚገባው ትክክለኛ መንገድ አድርጊ። የእስራኤል ድንግል ሆይ፣ ተመለሺ! ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ ተመለሺ።
22አንቺ እምነት የለሽ ልጅ ሆይ፣ እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና፤ ብርቱ ወንዶችን ለመጠበቅ ሴቶች ይከብባሉ።
23የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ሕዝቡን ወደ ምድራቸው ባመጣኋቸው ጊዜ፣ በይሁዳ ምድርና በከተሞችዋ እንዲህ ይላሉ፣ 'እርሱ የሚኖርብሽ የጽድቅ ማደሪያ፣ የቅድስና ተራራ ሆይ፣ እግዚአብሔር ይባርክሽ።'
24ይሁዳና ከተሞቹ ሁሉ በአንድነት በእርስዋ ይኖራሉ። ገበሬዎችና እረኞች ከመንጎቻቸው ጋር በዚያ ይገኛሉ።
25ለደከሙት የሚጠጡትን ውሃ እሰጣለሁና፣ በጥማት የሚሰቃዩትን ሁሉ በእርካታ እሞላለሁ።
26ከዚህም በኋላ ነቃሁ፣ እንቅልፌ የሚያነቃ እንደሆነ አስተዋልኩኝ።
27"ተመልከቱ፣ የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት በሰውና በእንስሳ ዘር የምዘራበት ዘመን፣ እንደሚመጣ ተመልከቱ ይላል እግዚአብሔር።
28እንዲህም ይሆናል፣ አፈርሳቸውና፣ ክፉ አድርግባቸው ዘንድ እንደ ተጋሁባቸው፣ ነገር ግን በሚመጡት ዘመናት፣ እንዲሁ እሠራቸውና፣ እተክላቸው ዘንድ እተጋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።
29በዚያ ዘመን ሰው ዳግመኛ እንዲህ አይልም፣ 'አባቶች መራራ የወይን ፍሬ በሉ፣ ነገር ግን የልጆች ጥርሶች ጠረሱ።'
30ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ መራራውን የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ ጥርሶቹ ይጠርሳሉ።
31ተመልከቱ፣ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር።
32ከግብጽ ምድር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም። ምንም እንኳን እኔ ባላቸው ብሆንም፣ እነርሱ ኪዳኔ ላይ ዐምጸዋልና፣ ይላል እግዚአብሔር።
33ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ግን ይህ ነውና፣ ይላል እግዚአብሔር፦ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፣ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።
34ከዚያም እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፣ ወይም እያንዳንዱ ሰው ወንድሙን፣ 'እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፣ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።"
35እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ እርሱ ነው። ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። እርሱ እንዲህ ይላል፣
36"እነዚህ ቋሚ ነገሮች ከእይታዬ ቢወገዱ፣ ይላል እግዚአብሔር፣ በዚያን ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ዘር በፊቴ ሕዝብ እንዳይሆን ለዘላለም ይቀራል።"
37እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ከፍ ያሉት ሰማያት ሊለኩ ቢችሉ፣ የምድርም መሠረት ከታች ቢመረመር፣ በዚያን ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ የእስራኤልን ዘር ሁሉ እጥላለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።"
38"ተመልከቱ፣ ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ከተማ ለእግዚአብሔር የሚሠራበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር።
39የተለካበትም ገመድ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፣ ወደ ጎዓም ይዞራል።
40የሬሳም ሸለቆ ሁሉ የአመድም እርሻ ሁሉ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል እስካለው እስከ ፈረሰ በር ማዕዘን ድረስ ለእኔ፣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል። ከእንግዲህም ወዲህ ለዘላለም አይነቀልም አይፈርስምም።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።