1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፣ እንዲህም አለ፣
2"የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'የነገርኩህን ቃል ሁሉ በጥቅልል ላይ ጻፈው።
3ተመልከት፣ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስባት ዘመን ይመጣልና፣ ይላል እግዚአብሔር። ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፣ እነርሱም ይገዙአታል።
4እግዚአብሔር ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው፣
5"እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'የሚያስፈራ ድምፅ ሰምተናል፤ የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም።
6ጠይቁ፣ ወንድ ይወልድ እንደ ሆነ ተመልከቱ። እያንዳንዱ ወጣት ሰው እጁን በወገቡ ላይ ያደረገው ለምንድነው? እንደ ወላድ ሴት፣ ፊታቸው ሁሉ ወደ ጥቁረት የተለወጠው ለምንድነው?
7ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ይሆናልና፣ እርሱንም የሚመስል የለምና። ያ የያዕቆብ የመከራ ዘመን ነው፣ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል።
8በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፣ እስራትህንም እበጥሳለሁ፣ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ለሌላ አትገዛም።
9ነገር ግን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር፣ በእነርሱ ላይ ንጉሥ ለማደርግላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ያገለግላሉ።
10ስለዚህ፣ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፣ አትፍራ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተም እስራኤል ሆይ፣ አትደንግጥ። ተመልከቱ፣ አንተን ከሩቅ፣ ዘርህንም ከምርኮ አገር አድናለሁና። ያዕቆብም ይመለሳል ሰላምም ይሆናል፤ ደህንነቱም ይጠበቃል፣ ከዚያም በኋላ ማንም አያስፈራውም።
11አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና፣ ይላል እግዚአብሔር። አንተንም የበተንሁባቸውን አሕዛብ ፍጹም ማብቂያቸው እንዲመጣ አደርጋለሁ። አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፣ በፍትህ እቀጣሃለሁ፣ ያለ ቅጣትም ከቶ አልተውህም።'
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ስብራትህ የማይፈወስ፣ ቍስልህም ያመረቀዘ ነው።
13ጉዳይህን የሚሟገትልህ የለም፣ ቍስልህንም የሚፈውስ መድኃኒት የለህም።
14አፍቃሪዎችሽ ሁሉ ረስተውሻል። አይፈልጉሽምም፣ በደልሽ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትሽም ስለ በዛ፣ በጠላት ማቍሰልና በጨካኝ አሠሪ ቅጣት አቍስዬሻለሁና።
15ሕመምሽ የማይፈወስ ሆኖአልና ስለ ስብራትሽ ለምን ትጮያለሽ? በደልሽ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትሽም ስለ በዛ፣ ይህን አድርጌብሻለሁ።
16ስለዚህ የሚበሉሽ ሁሉ ይበላሉ፣ ጠላቶችሽም ሁሉ ወደ ምርኮ ይወሰዳሉ። የዘረፉሽም ይዘረፋሉ፣ የበዘበዙሽንም ሁሉ ለመበዝበዝ አሳልፌ እሰጣለሁ።
17እኔ ጤናሽን እመልስልሻለሁ ቍስልሽንም እፈውሳለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ይህንንም የማደርገው፦ ማንም የማይሻት፤ የተጣለች ጽዮን" ብለው ጠርተውሻልና።
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ተመልከቺ፣ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፣ ለቤቱም እራራለሁ። ከተማይቱም በፍርስራሽ ጉብታዋ ላይ ትሠራለች፣ ምሽጉም እንደ ዱሮው ይሆናል።
19ከዚያም ከእርሱ ዘንድ የምስጋናና የዘፋኞች ድምፅ ይወጣል፣ እኔም አበዛቸዋለሁ አላሳንሳቸውም፤ እንዳይዋረዱ እኔ አከብራቸዋለሁ።
20ከዚያም ሕዝቦቻቸው እንደ ቀድሞ ይሆናሉ፣ ማኅበራቸውም በፊቴ ጸንቶ ይኖራል፤ የሚያስጨንቋቸውንም ሁሉ እቀጣለሁ።
21መሪያቸው ከእነርሱ ውስጥ ይወጣል። እኔ ሳቀርበውና እርሱም ሲቀርበኝ ከመካከላቸው ይወጣል። ይህንን ባላደርግ፣ ወደ እኔ ለመቅረብ የሚደፍር ማን ነው? ይላል እግዚአብሔር።
22እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፣ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።
23ተመልከቱ፣ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፣ ቍጣው ወጥቷል። ሳይቋረጥ የሚያገለባብጥ ዐውሎ ነፋስ ወጥቶአል። የክፉዎችንም ራስ ይገለባብጣል።
24የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም። በመጨረሻው ዘመን ታስተውሉታላችሁ።"