መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 29

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ነቢዩ ኤርምያስ ከምርኮ ሽማግሌዎች መካከል ወደ ተረፉት፣ ወደ ካህናቱም፣ ወደ ነቢያቱም፣ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ወዳፈለሰውም ሕዝብ ሁሉ ከኢየሩሳሌም የላከው የደብዳቤው ቃል ይህ ነው።
2ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን፣ እቴጌይቱ እናቱ፣ ከፍተኛ መኮንኖቹ፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም አለቆች፣ ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም ከኢየሩሳሌም ከወጡ በኋላ ነው።
3ኤርምያስ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር በላካቸው በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ደብዳቤውን እንዲህ ሲል ላከው።
4ጥቅሉ እንዲህ ይላል፣ "የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረክኋቸው ምርኮኞች ሁሉ እንዲህ ይላል፣
5'ቤት ሠርታችሁ ኑሩባቸው፣ አታክልትም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ፤
6ሚስቶችን ውሰዱ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ውለዱ፤ ከዚያም ለወንዶች ልጆቻችሁ ሚስቶችን ውሰዱ፣ ሴቶች ልጆቻችሁንም ለባሎቻቸው ስጡ። እነርሱም ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ይውለዱ፤ ከዚያም ተባዙ ጥቂቶችም አትሁኑ።
7በእርስዋም ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማርክኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ፣ ከእኔ ዘንድ ማልዱ።'
8የእስራኤልም አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ 'በመካከላችሁ ያሉት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፣ እናንተም ራሳችሁ የምታልሙትን ሕልም አትስሙ።
9በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና። እኔም አልላክኋቸውም። ይላል እግዚአብሔር።'
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ባቢሎን ለሰባ ዓመታት በገዛቻችሁ ጊዜ፣ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ እረዳችኋለሁ፣ ደግሞም መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።
11ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ ራሴ አውቃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የጥፋት አይደለም።
12እናንተም ወደ እኔ ትጠራላችሁ፣ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፣ እኔም እሰማችኋለሁ።
13እናንተ ትሹኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ።
14ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፤ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ከበተንሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።'
15እናንተም፣ እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል ብላችኋልና፣
16እግዚአብሔር በዳዊት ዙፋን ስለ ተቀመጠ ንጉሥ፣ በዚያች ከተማ ለቆዩት ሕዝቦች ሁሉ፣ ከእናንተም ጋር ስላልተማረኩት ወንድሞቻችሁ፣ እንዲህ ይላል።
17የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ተመልከቱ፣ ሰይፍንና ራብን፣ በሽታንም እሰድድባቸዋለሁ። ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉ በለስ አደርጋቸዋለሁ።
18በሰይፍም፣ በራብም፣ በመቅሠፍትም አሳዳድዳቸዋለሁ፣ ባሳደድሁባቸውም አሕዛብ ሁሉ ዘንድ ለመጠላት፣ ለመደነቂያ፣ ለማፍዋጫም፣ ለመሰደቢያም እንዲሆኑ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
19ይህም የሆነው ቃሌን ስላልሰሙ ነው፣ ይላል እግዚአብሔር፤ በማለዳ ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ወደ እነርሱ ሰድጃለሁና፤ በተደጋጋሚ ላክኋቸው፣ እናንተ ግን አልሰማችሁም፣ ይላል እግዚአብሔር።'
20ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ ሆይ፣ እናንተ ራሳችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፣
21'የእስራኤል አምላክ፣ እኔ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚናገሩላችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ እላለሁ፦ ተመልከቱ፣ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። በዓይኖቻችሁም ፊት ይገድላቸዋል።
22ከዚያም በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ ስለ እነዚህ ሰዎች እርግማንን ይናገራሉ። እርግማኑም፦ እግዚአብሔር የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ያድርግህ የሚል ነው።
23በእስራኤል ዘንድ ስንፍና አድርገዋልና፣ ከጎረቤቶቻቸውም ሚስቶች ጋር አመንዝረዋልና፣ ያላዘዝኋቸውንም ቃል በስሜ በሐሰት ተናግረዋልና ይህ ይሆናል። እኔም አውቃለሁ ምስክርም ነኝ፣ ይላል እግዚአብሔር።"
24"ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ በል፦
25'የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌም ወዳለው ሕዝብ ሁሉ፣ ወደ ካህኑም ወደ መዕሤያ ልጅ ወደ ሶፎንያስ፣ ወደ ካህናቱም ሁሉ ደብዳቤዎችን በገዛ ስምህ እንዲህ ስትል ልከሃል፣
26"እያበደ ትንቢት የሚናገርን ሰው ሁሉ በእግር ግንድና በሠንሰለት ታኖረው ዘንድ በእግዚአብሔር ቤት አለቃ እንድትሆን እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ፋንታ ካህን አድርጎሃል።
27አሁንስ፣ ትንቢት ተናጋሪውን የዓናቶቱን ሰው ኤርምያስን ስለ ምን አትገሥጸውም?
28እርሱ፣ 'ጊዜው የረዘመ ነው። ቤት ገንቡና በውስጡ ኑሩበት፣ አትክልትንም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ' ብሎ ወደ እኛ ወደ ባቢሎን ልኮአል።"
29ካህኑም ሶፎንያስ ይህን ደብዳቤ ነብዩ ኤርምያስ እየሰማ አነበበው።
30የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፣
31"'እግዚአብሔር ስለ ኔሔላማዊው ስለ ሸማያ እንዲህ ይላል፣ ብለህ ወደ ምርኮኞች ሁሉ ላክ፦ 'እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችኋልና፣ በሐሰትም እንድትታመኑ አድርጎአችኋልና፤
32ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከቱ፣ ኔሔላማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ። እኔም የማደርግላችሁን መልካሙን ነገር የሚያይ አንድም የእርሱ ሰው በመካከላችሁ አይኖርም። ለሕዝቤ የማደርገውን አንዱንም መልካም ነገር አያይም ይላል እግዚአብሔር። እርሱ በእኔ፣ በእግዚአብሔር ላይ በእምነት ያልሆነ ነገርን ተናግሯልና።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።