መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 28

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያም ዓመት በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ነቢዩ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ።
2"የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይናገራል፣ የባቢሎን ንጉሥ ያኖረውን ቀንበር ሰብሬአለሁ።
3የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህች ስፍራ ወደ ባቢሎን ያጋዛትን የእግዚአብሔርን ቤት የሆኑትን ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳታለሁ።
4ከዚያም ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚህች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና።"
5ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለነቢዩ ሐናንያ ተናገረ።
6ነብዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ፣ "እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግ! የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ምርኮውንም ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ እግዚአብሔር የተናገረውን ትንቢት ይፈጽም።
7ይሁን እንጂ፣ በጆሮህና በሕዝብህ ጆሮ ሁሉ የምናገረውን ይህን ቃል ስማ።
8ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነብያት በብዙ አገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ሰልፍና ስለ ክፉ ነገር፣ ስለ መቅሰፍትም ትንቢት ተናገሩ።
9ስለዚህም ሰላም እንደሚኖር የተናገረ ነቢይ፣ የነቢዩ ቃል በተፈጸመ ጊዜ፣ ያኔ እግዚአብሔር በእውነት የሰደደው ነቢይ እንደ ሆነ ይታወቃል።"
10ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው።
11ከዚያም ሐናንያ በሕዝብ ሁሉ ፊት፣ "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልክ እንደዚሁ፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ" አለ። ከዚያም ነብዩ ኤርምያስ መንገዱን ሄደ።
12ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፣
13"ሂድና ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፣ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ የእንጨት ቀንበርን ሰብረሃል፣ እኔ ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር እሠራለሁ።'
14የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እንዲያገለግሉ የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ። እነርሱም ያገለግሉታል። እንዲገዛቸውም የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ።"
15ቀጥሎ፣ ነብዩ ኤርምያስ ነብዩን ሐናንያን፣ "ሐናንያ ሆይ፣ አድምጥ! ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል እንጂ እግዚአብሔር አልላከህም።
16ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከት ከምድር ላይ እሰድድሃለሁ። በእግዚአብሔር ላይ ዐመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ።" አለው።
17ነብዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።