መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 27

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ።
2እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፣ "እስራትና ቀንበር ለራስህ ሥራ። በአንገትህም ላይ አድርግ።
3ከዚያም ወደ ይሁዳ ንጉሥም ወደ ሴዴቅያስ፣ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት መልእክተኞች እጅ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ፣ ወደ ሞዓብም ንጉሥ፣ ወደ አሞንም ልጆች ንጉሥ፣ ወደ ጢሮስም ንጉሥ፣ ወደ ሲዶናም ንጉሥ ላካቸው።
4ለጌቶቻቸውም እንዲነግሩ እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፣ 'የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለጌቶቻችሁ ልትነግሯቸው የሚገባው ይህንን ነው፣
5እኔ ራሴ ምድሪቱን በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ ፈጥሬአለሁ። በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን ጭምር ፈጥሬያለሁ። በዐይኔም ዘንድ ትክክል ለሆነው ለማንኛውም ሰው እሰጣታለሁ።
6አሁንም፣ እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለባርያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣታለሁ። እንዲሁም ያገለግሉት ዘንድ በሜዳዎች ያሉትን ሕያዋን ነገሮችን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ።
7የገዛ ራሱም ምድር ፍጻሜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጅ ልጅ ልጁም ይገዛሉ። ከዚያም ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እርሱን ያስገዙታል።
8ለባቢሎን ንጉሥም ለናቡከደነፆር የማያገለግለውን፣ ከባቢሎንም ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የማያደርገውን ሕዝብና መንግሥት፣ ያን ሕዝብ በእጁ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ፣ በመቅሰፍትም እቀጣለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።
9እናንተ ደግሞ! 'ለባቢሎን ንጉሥ አታገልግሉ' የሚሉአችሁን ነቢያቶቻችሁን፣ ሟርተኞቻችሁን፣ ሕልም አላሚዎቻችሁንና ቃላተኞቻችሁን፣ መተተኞቻችሁንም መስማት አቊሙ።
10ከምድራቸሁ አርቀው ሊልኳችሁ፣ እኔም እንዳሳድዳችሁ፣ እናንተም እንድትሞቱ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና።
11ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚያገለግለውን ሕዝብ በአገሩ ላይ እተዋቸዋለሁ፤ እነርሱም ያርሱአታል ቤቶችንም ይሠሩባታል።"
12ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም በዚህ ቃል ተናገርሁ ይህንንም መልእክት ሰጠሁት፣ "ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገታችሁን ዝቅ አድርጉና ለእርሱና ለሕዝቡ አገልግሉ፣ በሕይወትም ትኖራላችሁ።
13ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛ ዘንድ እንቢ ስላለ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፣ አንተና ሕዝብህ በሰይፍና በራብ በመቅሰፍትም ለምን ትሞታላችሁ?
14ሐሰተኛን ትንቢት ይናገሩላችኋልና፣ 'ለባቢሎን ንጉሥ አታገልግሉ' የሚሉአችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ።
15'እኔ አልላክኋቸውምና፤ ነገር ግን እኔ እንዳሳድዳችሁ፣ እናንተና ትንቢት የሚናገሩላችሁ ነቢያትም እንድትጠፉ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገራሉ፣' ይላል እግዚአብሔር።"
16ይህንን ለካህናትና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ፣ "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተንብየውላችሁ 'ተመልከቱ! የእግዚአብሔር ቤት ዕቃ አሁን ከባቢሎን ይመለሳል!' የሚሉአችሁን የነቢያቶቻችሁን ቃል አትስሙ። እነርሱ ውሸትን ይተነብዩላችኋል።
17እነርሱንም አትስሟቸው። የባቢሎንን ንጉሥ ልታገለግሉና በሕይወት ልትኖሩ ይገባችኋል። ይህችስ ከተማ ስለ ምን ባድማ ትሆናለች?
18እነርሱ ግን ነቢያት ከሆኑ፣ የእግዚአብሔርም ቃል በእውነት ወደእነርሱ ቢመጣ፣ በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም የቀረችው ዕቃ ወደ ባቢሎን እንዳትሄድ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ እግዚአብሔር ይለምኑ።
19የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ከበርቴዎች ሁሉ ማርኮ
20ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባፈለሳቸው ጊዜ ስላልወሰዳቸው ዓምዶች ስለ ኵሬውም፣ ስለ መቀመጫዎቹም በዚህችም ከተማ ስለ ቀረች ዕቃ ሁሉ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
21በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም ስለ ቀረችው ዕቃ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣
22'እነርሱ ወደ ባቢሎን ትወሰዳለች እስከምጐበኛትም ቀን ድረስ በዚያ ትኖራለች፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ከዚያም አወጣታለሁ ወደዚህም ስፍራ እመልሳታለሁ።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።