1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ መጣና እንዲህ አለ፣
2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በቤቴ አደባባይ ቁም፣ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ ይሰግዱ ዘንድ ለሚመጡት ለይሁዳ ከተሞች ሁሉ ንገራቸው። እንድትነግራቸው ያዘዝሁህን ቃል ሁሉ ንገራቸው። አንዲትም ቃል አትጉደል!
3ምናልባት ይሰሙ፣ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ።
4ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በፊታችሁ በሰጠኋት ሕጌ ትሄዱ ዘንድ ባትሰሙኝ፣
5በጽናት ወደ እናንተ የላክኋቸውን የባሪያዎቼን የነቢያትን ቃል ባትሰሙ፣ ነገር ግን አላደመጣችኋቸውም!
6ያኔ ይህንን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፤ ይህችንም ከተማ ለምድር አሕዛብ ሁሉ እርግማን አደርጋታለሁ።"
7ኤርምያስ በእግዚአብሔር ቤት ይህንን ቃል ሲናገር ካህናቱ፣ ነቢያቱ፣ ሕዝቡም ሁሉ ሰሙ።
8ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ነገር ሁሉ በፈጸመ ጊዜ፣ ካህናት፣ ነቢያትና ሕዝቡም ሁሉ፣ ያዙትና "በእርግጥ ትሞታለህ!
9በእግዚአብሔር ስም ተንብየህ ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፣ ይህችም ከተማ ነዋሪ የማይገኝባት ወና ትሆናለች ብለህ ለምን ትንቢት ተናገርህ?" አሉት። ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በኤርምያስ ላይ በዐመጽ ተሰብስበው ነበር።
10ከዚያም የይሁዳ አለቆች ይህን ሰሙና ከንጉሥ ቤት ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄዱ። በአዲሱም በእግዚአብሔር ቤት ደጅ መግቢያ ተቀመጡ።
11ካህናቱና ነብያቱም ለአለቆቹና ለሕዝቡ ሁሉ ተናገሩ። እንዲህም አሉ፣ "በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁ በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግአልና ይህ ሰው ሞት የሚገባው ነው!" አሉ።
12ስለዚህ ኤርምያስ ለአለቆችና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፣ "በሰማችሁት ቃል ሁሉ፣ በዚህች ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እናገር ዘንድ እግዚአብሔር ልኮኛል።
13አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፣ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ጥፋት እንዲተው፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ድምፅ ስሙ።
14ተመልከቱኝ! እኔ ራሴ በእጃችሁ ነኝ። በዐይናችሁ ፊት መልካምና ቅን የመሰላችሁን አድርጉብኝ።
15ነገር ግን ይህን ቃል ሁሉ በጆሮአችሁ እናገር ዘንድ በእውነት እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛልና ብትገድሉኝ ንጹሕ ደምን በራሳችሁና በዚህች ከተማ በሚኖሩባትም ላይ እንድታመጡ በእርግጥ እወቁ።"
16አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፣ "ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮናልና ሊሞት አይገባውም" አሉ።
17ከዚያም ከምድሪቱ ሽማግሌዎች ሰዎች ተነሥተው ለመላው የሕዝቡ ጉባኤ ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ።
18እነርሱም፣ "ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ይተነብይ ነበረ። ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ ተንብዮ 'የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፣ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፣ የቤተመቅደሱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል' ብሎ ተናገረ።
19በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ እግዚአብሔርን አልፈራምን? ወደ እግዚአብሔርስ አልተማለሉምን? እግዚአብሔርስ የተናገረባቸውን ክፉ ነገር አይተውምን? እኛም በገዛ ሕይወታችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለንን?"
20ደግሞም በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገረ አንድ ሰው ነበረ፣ እርሱም የቂርያትይዓሪም ሰው የሸማያ ልጅ ኦርዮ ይባል ነበር፤ በዚህችም ከተማ በዚህችም ምድር ላይ ከኤርምያስ ቃል ጋር የተስማማ ትንቢት ተናገረ።
21ነገር ግን ንጉሡ ኢዮአቄም እና ወታደሮቹ ሁሉ እንዲሁም አለቆቹም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ንጉሡ ሊገድለው ሞከረ፤ ነገር ግን ኦርዮም ይህን ሲሰማ ፈርቶ ሸሸ ወደ ግብጽም ገባ።
22ንጉሡም ኢዮአቄም የዓክቦርን ልጅ ኤልናታንን ከእርሱም ጋር ሌሎችን ሰዎች ወደ ግብጽ ላካቸው፤
23ኦርዮንን ከግብጽ አውጥተው ወደ ንጉሡ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ። ከዚያም ኢዮአቄም በሰይፍ ገደለውና ሬሳውን ተራ በሆኑ ሰዎች መቃብር ውስጥ ጣለው።
24ነገር ግን በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች።