1"የማሰማርያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው! ይላል እግዚአብሔር።"
2ስለዚህ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል፣ "በጎቼን በትናችኋል ደግሞም አባርራችኋቸዋል። በጭራሽ አልተንከባከባችኋቸውም። ይህንን እወቊ! ለሥራችሁ ክፋት መልሼ እከፍላችኋለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር
3እኔ ራሴ የመንጋዬን ቅሬታ ካባረርኋቸው ምድር ሁሉ እሰበስባለሁ፣ ፍሬያማ ወደሚሆኑበትና ወደሚበዙበት ወደ መሠማሪያቸው እመልሳቸዋለሁ።
4ከዚያም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይፈሩና እንዳይደነግጡ የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ። ከእነርሱ አንዳቸውም አይጐድሉም፣ ይላል እግዚአብሔር።
5ተመልከቱ፣ ለዳዊት ጻድቅ ቅርንጫፍን የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር። እርሱም እንደ ንጉሥ ይገዛል፤ ብልፅግናን ያመጣል፣ በምድሪቱም ላይ ፍትህንና ጽድቅን ይፈጽማል።
6በዘመኑም ይሁዳ ይድናል፣ እስራኤልም በአስተማማኝ ደህንነት ይቀመጣል። የሚጠራበትም ስም፦ እግዚአብሔር ጽድቃችን ነው ተብሎ ነው።
7ስለዚህ፣ ተመልከቱ፣ ከእንግዲህ 'የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!' የማይባልበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር።
8ይልቊን፣ 'የእስራኤልን ቤት የዘር-ሐረግ ከሰሜን ምድርና ከተሰደዱባቸው ምድሮች ሁሉ ያወጣና የመራ ሕያው እግዚአብሔርን!' ይባላል፤ እነርሱም በገዛ ራሳቸው ምድር ይቀመጣሉ።"
9ስለ ነቢያት፣ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል፣ አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል። ከእግዚአብሔር እና ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ እንደ ሰካራም ሰው፣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈውም ሆኛለሁ።
10ምድር በአመንዝሮች ተሞልታለችና። ከዚህ መርገም የተነሣ ምድር አለቀሰች። የምድረ በዳ ማሰማርያዎች ደርቀዋል። የእነዚህ ነብያት አካሄድ ክፉ ነው፤ ኃይላቸውም በትክክለኛው መንገድ ጥቅም ላይ አልዋለም።
11"ነብያትና ካህናትም ረክሰዋል። እንደውም፣ በቤቴ ውስጥ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ! ይላል እግዚአብሔር።
12ስለዚህ መንገዳቸው በጨለማ እንዳለች ድጥ ስፍራ ትሆንባቸዋለች። እነርሱም ይገፈተሩበታል። በውስጧም ይወድቁባታል። እኔም በምቀጣቸው ዓመት ክፉ ነገርን እልክባቸዋለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።
13በሰማርያ ነቢያት ላይ የሚያስቀይም ነገርን አይቻለሁ። በበኣል ትንቢት ይናገራሉ፣ ደግሞም ሕዝቤንም እስራኤልን ያስታሉ።
14በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥ ነገሮችን አይቻለሁ፦ ያመነዝራሉ ደግሞም በሐሰት ይመላለሳሉ። የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ማንም ከክፋቱ አልተመለሰም። ሁሉም እንደ ሰዶም ነዋሪዎቿም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ!"
15ስለዚህ ነብያትን በተመለከተ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ተመልከቱ፣ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኵሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና እሬትን አበላቸዋለሁ የተመረዘንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ።"
16የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ። ሐሰተኝነትን ያስተምሩአችኋል! ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ አሳባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ።
17ያለማቋረጥ ለሚንቁኝ እንዲህ ይላሉ፣ 'እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሎአል።' በገዛ ራሱ የልብ እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ፣ 'ክፉ ነገር አያገኛችሁም።' ይላሉ።
18ይሁን እንጂ ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነው? ለቃሉ አትኩሮት ሰጥቶ የሰማ ያደመጠስ ማን ነው?
19ተመልከቱ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ እየመጣ ያለ ዐውሎ ነፋስ አለ! የእርሱም ቍጣና የሚገለባብጥ ዐውሎ ነፍስ ወጥቶአል። በዓመፀኞች ራስ ላይ ይገለባበጣል።
20የእግዚአብሔር ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም። በመጨረሻው ዘመን፣ ትገነዘቡታላችሁ።
21እነዚህን ነብያት እኔ አልላክኋቸውም። በድንገት ተገኙ። ምንም አልነገርኳቸውም፣ ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ ትንቢትን ተናገሩ።
22በምክሬ ግን ቆመው ቢሆን ኖሮ፣ ለሕዝቤ ቃሌን ባሰሙ ነበር፤ ከክፉም ቃሎቻቸው እንዲሁም ከብልሹ ሥራቸው በመለሱአቸው ነበር።
23እኔ የቅርብ አምላክ ብቻ ነኝ ደግሞም የራቀ አምላክ አይደለሁም? ይላል እግዚአብሔር።
24ሰው ላየው እንዳልችል በስውር ሊሸሸግ ይችላልን? ሰማይንና ምድርንስ አልሞላምን? ይላል እግዚአብሔር።
25በስሜ ሐሰትን የሚናገሩት የነብያት ያሉትን ነገር ሰምቻለሁ። እነርሱም 'ህልም አልሜ ነበር! ህልም አልሜ ነበር!' ብለዋል።
26ሐሰትን ከአሳባቸው በሚተነብዩ፣ የልባቸውንም ማታለል በሚተነብዩ ነቢያት ይህ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው?
27በሚናገሯቸው ሕልሞች ሕዝቤ ስሜን እንዲረሳ ለማድረግ ያቅዳሉ፣ እያንዳንዱ ለጎረቤቱ ልክ አባቶቻቸው ለበኣል ሲሉ ስሜን እንደ ረሱ ያደርጋሉ።
28የሚያልም ነቢይ ሕልሙን ይናገር። ነገር ግን ቃሌን የነገርኩት፣ ቃሌን በእውነተኝነት ይናገር። ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? ይላል እግዚአብሔር።
29ቃሌ እንደ እሳት፣ ድንጋዩም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል እግዚአብሔር።
30ስለዚህ፣ ተመልከቱ፣ እኔ ቃልን ከሌላኛው ሰው ሰርቆ ቃሉ ከእኔ ዘንድ መጥቷል በሚሉት ነብያት ላይ ነኝ፣ ይላል እግዚአብሔር።
31ተመልከቱ፣ ትንቢትን ለማወጅ ምላሳቸውን በሚጠቀሙት ነብያት ላይ ነኝ፣ ይላል እግዚአብሔር።
32ተመልከቱ፣ በሐሰት በሚያልሙ፣ ከዚያም በሚናገሩትና በዚህም መልኩ በሐሰታቸውና በትምክህታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፣ ይላል እግዚአብሔር። እኔም አልላክኋቸውምና ትእዛዛትንም አልሰጠኋቸውምና በእነርሱ ላይ ነኝ። ስለዚህም ለዚህ ሕዝብ በእርግጥም አይጠቅሟቸውም ይላል እግዚአብሔር።
33ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፣ 'የእግዚአብሔር ዐዋጅ ምንድር ነው?' ብለው ቢጠይቊህ፣ 'እናንተን ትቻችኋለሁና የምን ዐዋጅ ነው?' ይላል እግዚአብሔር ልትላቸው ይገባል።
34'የእግዚአብሔር ዐዋጅ ይህ ነው፣' የሚሉትን ነብያትን፣ ካህናትን እና ሕዝቡን በተመለከተ፣ ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ።
35እያንዳንዱ ሰው ለጎረቤቱ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ለወንድሙ፣ 'እግዚአብሔር የመለሰው ምንድር ነው?' ደግሞስ 'እግዚአብሔር ምን ዐወጀ?' ማለትህን ቀጥል።
36ከእያንዳንዱ ሰው የሆነው እያንዳንዱ ዐዋጅ የገዛ ራሱ መልእክት ይሆንበታልና፣ እንዲሁም የሕያው እግዚአብሔርን ቃል ለውጣችኋልና፣ ስለ እግዚአብሔር ዐዋጅ ከእንግዲህ ልትናገሩ አይገባችሁም።
37ለነቢዩ የምትጠይቀው ይህንን ነው፣ 'እግዚአብሔር ምን መለሰልህ? እግዚአብሔር ምን ዐወጀ?'
38ከዚያም፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ዐዋጅ ትናገራለህ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን ይላል፣ "ይህ የእግዚአብሔር ዐዋጅ ነው አትበሉ።" ብዬ ትእዛዝን የላክሁባችሁ ቢሆንም፣ እናንተ ግን "የእግዚአብሔር ዐዋጅ ይኸውላችሁ፣" አላችሁ።
39ስለዚህም፣ ተመልከቱ፣ አንሥቻችሁ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ከሰጠሁት ከተማ ጋር ከእኔ ዘንድ ልወረውራችሁ ነው።
40ከዚያም የማይረሳ ዘላለማዊ እፍረትን እና ስድብን አኖርባችኋለሁ።"