መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 22

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤት ውረድና በዚያም ይህን ቃል ተናገር።
2እንዲህም በል፣ 'በዳዊት ዙፋን የምትቀመጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። አንተና የእርሱ ባርያዎች የሆናችሁ፣ በእነዚህም በሮች የመትገቡት ሕዝቦቹ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ፣ የተዘረፈውንም ከጨቋኙ እጅ አድኑ። በምድራችሁ ያለውን እንግዳ፣ ወይም የትኛውንም ወላጅ አልባ ወይም መበለቲቱን አትበድሉ። አታምፁባቸው፣ ወይም በዚህ ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ።
4እነዚህንም ነገሮች ብታደርጉ፣ ያን ጊዜ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታት በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ ተቀምጠው በዚህ ቤት በሮች ይገባሉ። እርሱም፣ ባርያዎቹም፣ ሕዝቡም እንዲሁ ይገባሉ!
5ነገር ግን ከእኔ የተነገሩትን እነዚህን ቃሎች ባትሰሙ፣ ይህ ንጉሣዊ ቤተመንግሥት እንደሚጠፋ በራሴ ምያለሁ" ይላል እግዚአብሔር።
6እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤት እንዲህ ይላልና፣ 'አንተ በእኔ ዘንድ እንደ ገለዓድ፣ ወይም እንደ ሊባኖስ ራስ ነህ። ነገር ግን፣ በእርግጥ ምድረ በዳ፣ ማንም እንደማይቀመጥባቸው ከተሞች አደርግሃለሁ።
7እንዲመጡባችሁ አጥፊዎችን በእናንተ ላይ አዘጋጅቻለሁ! የተመረጡትንም የዝግባ ዛፎቻችሁን ይቈርጣሉ፣ በእሳትም ውስጥ ይጥሉአቸዋል።
8ከዚያም ብዙ አሕዛብ በዚህች ከተማ አጠገብ ያልፋሉ። ሁሉም ባልንጀሮቻቸውን፣ "እግዚአብሔር በዚህች ታላቅ ከተማ ለምን እንዲህ አደረገ?" ይላሉ።
9ሌላኛውም፣ "የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትተው ለሌሎች አማልክት ስለ ሰገዱ ስላመለኩአቸውም ነው" ብለው ይመልሳሉ።
10ለሞተው አታንቡ። አታልቅሱለትም። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አይመለስምና፣ የተወለደባትንም አገር አያይምና ወደምርኮ ለሚሄደው በእርግጥ አልቅሱ።
11በአባቱ በኢዮአስ ፋንታ ስለ ነገሠው ከዚህም ስፍራ ስለ ወጣው ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
12'በተማረከባት አገር ይሞታል እንጂ ወደዚህ አይመለስም፣ ይህችንም አገር ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።'
13ቤቱን ያለ ጽድቅ ሰገነቱንም በግፍ ለሚሠራ፣ ሌሎችንም አሠርቶ፣ ክፍያ ለማይሰጣቸው።
14'ለራሴ ሰፊ የላይኛ ቤት፣ ትልቅም ሰገነት እሠራለሁ ለሚል፣ መስኮትንም ለሚያወጣ፣ በዝግባም ሥራ ለሚያስጌጥ፣ በቀይ ቀለምም ለሚቀባው ወዮለት።'
15የዝግባ እንጨት እንዲኖርህ ስለፈለግህ መልካም ንጉሥ የሚያደርግህ ይህ ነውን? በውኑ አባትህ አይበላምና አይጠጣም ነበርን፣ ፍርድንና ጽድቅንስ አያደርግም ነበርን? በዚያም ጊዜ ነገሮች መልካም ሆነውለት አልነበረምን።
16ለድሀውና ችግረኛው ፍርድን ይፈርድ ነበር። በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር። እኔን ማወቅ ማለት ይህ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር።
17ዓይንህና ልብህ ግን ለስስት፣ ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ፣ ዓመፅንና ግፍንም ለመሥራት ብቻ ካልሆነ በቀር ሌላ ነገር የለውም።
18ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፦ "ወዮ፣ ወንድሜ ሆይ!" ወይም፣ "ወዮ፣ እኅቴ ሆይ!' እያሉ አያለቅሱለትም፣ ወይም 'ወዮ፣ ጌታዬ!' አሊያም 'ወዮ፣ ግርማዊነትዎ!' እያሉ አያለቅሱለትም።
19በአህያ ቀብር ይቀበራል፣ ከኢየሩሳሌምም በር ወደ ውጭ ተጐትቶ ይጣላል።
20ወደ ሊባኖስ ወጥተሽ ጩኺ። በባሳን ድምፅሽን አንሺ። ውሽሞችሽ ሁሉ ይጠፋሉና ከበዓባሪም ተራሮች ሆነሽ ጩኺ።
21በደኅንነትሽ ጊዜ ተናገርሁሽ፣ አንቺ ግን 'አልሰማም' አልሽ። ከወጣትነትሽ ጀምሮ ቃሌን አለመስማትሽ ልማድሽ ነው።
22በግ ጠባቂዎችሽን ሁሉ ነፋስ ይጠብቃቸዋል፣ ውሽሞችሽም ተማርከው ይሄዳሉ። በዚያን ጊዜም ስለ ክፋትሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ ትዋረጂማለሽ።
23አንቺ በሊባኖስ የምትቀመጪ፣ በዝግባ ዛፍም ውስጥ ጎጆሽን የምትሠሪ ሆይ፣ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሕማም በያዘሽ ጊዜ እንዴት ታጓሪያለሽ።"
24"እኔ ሕያው ነኝና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ ማኅተም ቢሆን ኖሮ እንኳ፣ ከዚያ እነቅልህ ነበር፤ ይላል እግዚአብሔር።
25ነፍስህንም ለሚሹት ለምትፈራቸውም እጅ፣ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ለከለዳውያንም እጅ እሰጥሃለሁ።
26አንተንም የወለደችህንም እናትህን ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ አገር እጥላችኋለሁ፣ በዚያም ትሞታላችሁ።
27ይመለሱባትም ዘንድ ወደሚመኟት ወደዚያች ምድር ተመልሰው አይመጡም።
28በውኑ ይህ ሰው ኢዮአቄም የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ ነውን? ወይስ እርሱ ለአንዳች የማይረባ የሸክላ ዕቃ ነውን? እርሱና ዘሩስ በማያውቋት ምድር ስለ ምን ተጥለው ወደቁ?
29ምድር ሆይ፣ ምድር ሆይ፣ ምድር ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ!
30እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ከዚህ ሰው ዘር የሚከናወን በዳዊትም ዙፋን ላይ የሚቀመጥ በይሁዳም የሚነግሥ እንግዲህ አይገኝምና። መካን በዘመኑም የማይከናወንለት ሰው ብላችሁ ጻፉ።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።