1ንጉሥ ሴዴቅያስ የመልክያን ልጅ ጳስኮርንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስ ወደ ኤርምያስ በላከ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።
2"የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋናልና ስለ እኛ፣ እባክህ፣ እግዚአብሔርን ጠይቅ። ምናልባት ከእኛ ይመለስ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግ ይሆናል።"
3ስለዚህ ኤርምያስ እንዲህ አላቸው፣ "ለሴዴቅያስ እንዲህ በሉት፣
4'የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከት፣ የባቢሎንን ንጉሥ ከቅጥርም ውጭ የከበቡአችሁን ከለዳውያንን የምትወጉበትን በእጃችሁ ያለውን ዕቃ ጦራችሁን እመልሰዋለሁ! እነዚያንም ወደዚህች ከተማ አማከይ እሰበስባቸዋለሁ።
5ያን ጊዜ እኔ ራሴ በተዘረጋች እጅና በብርቱ ክንድ፣ በቍጣና በመዓት በታላቅም መቅሠፍት እወጋችኋለሁ።
6በዚህችም ከተማ የሚኖሩትን፣ ሰዎችንና እንስሶችን እመታለሁ፣ በጽኑም መቅሰፍት ይሞታሉ።
7ከዚህ በኋላ፣ ይላል እግዚአብሔር፣ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስን፣ ከቸነፈርና ከሰይፍ ከራብም በዚህች ከተማ የቀሩትንም ባሪዎቹንና ሕዝቡን፣ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። ከዚያም እርሱ በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል። አያዝንላቸውም፣ አይራራላቸውም፣ ወይም አያዝንላቸውም።'
8ከዚያም ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ልትል ይገባል፣ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከቱ፣ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ በፊታችሁ አደርጋለሁ።
9በዚህች ከተማ ውስጥ የሚቆይ የትኛውም ሰው በሰይፍ፣ በራብ፣ በመቅሠፍትም ይሞታል፤ ነገር ግን ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል። በሕይወትም ያመልጣል።
10መልካምን ሳይሆን ጥፋትን ለማምጣት ፊቴን በዚህች ከተማ ላይ አድርጌአለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር። ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ተሰጥታለች፣ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል።'
11የይሁዳ ንጉሥ ቤትን በተመለከተ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
12የዳዊት ቤት ሆይ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'በማለዳ ፍርድን አድርጉ። የተዘረፈውንም ከአጨቋኙ እጅ አድኑ፣ አሊያ ቍጣዬ እንደ እሳት ይወጣና ያቃጥላል። ከሥራችሁ ክፋት የተነሣ ሊያጠፋው የሚችል ማንም አይኖርም።
13ተመልከቱ፣ የሸለቆው ነዋሪዎች! በሜዳው ላይ ያለው ዓለት ሆይ በእናንተ ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር። "ሊያጠቃን በእኛ ላይ የሚወርድ ማነው?" ወይም "ወደ ቤታችን የሚገባ ማን ነው?" ለምትሉት፣ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ።
14የሥራችሁ ፍሬ በእናንተ ላይ እንዲመጣባችሁ መድቤያለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ በዱርዋም ውስጥ እሳትን አነድዳለሁ፣ በዙሪያዋም ያለውን ሁሉ ይበላል።