መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 20

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በእግዚአብሔርም ቤት የተሾመው አለቃ የካህኑ የኢሜር ልጅ ጳስኮር ኤርምያስ በዚህ ነገር ትንቢት ሲናገር ሰማ።
2ስለዚህ ጳስኮር ነቢዩን ኤርምያስን መታው፣ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ ባለው በላይኛው የብንያም በር በእግር ግንድ አሰረው።
3በቀጣዩ ቀን ጳስኮር ኤርምያስን ከግንድ እስር አወጣው። ከዚያም ኤርምያስ እንዲህ አለው፣ "እግዚአብሔር ስምህን፣ ማጎርሚሳቢብ እንጂ ጳስኮር ብሎ አይጠራህም።
4እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ 'ተመልከት፣ ለራስህና ለወዳጆችህ ሁሉ ፍርሃት አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉና ዓይኖችህም ያንን ያያሉ። ይሁዳንም ሁሉ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ። እርሱም በባቢሎን ምርኮኛ ያደርጋቸዋል ወይም በሰይፍ ይገድላቸዋል።
5የዚህችንም ከተማ ባለጠግነት ሁሉ ጥሪትዋንም ሁሉ ክብርዋንም ሁሉ የይሁዳንም ነገሥታት መዝገብ ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ። እነዚህን ነገሮች በጠላቶቻችሁ እጅ አኖራለሁ፣ እነርሱም ይይዟቸዋል። እነርሱም ይወስዷቸዋል ደግሞም ወደ ባቢሎን ያመጧቸዋል።
6አንተ ግን፣ ጳስኮር ሆይ፣ በቤትህም የሚኖሩት ሁሉ ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ። ወደ ባቢሎን ትሄዳለህ ደግሞም በዚያ ትሞታለህ። አንተና የሚያታልሉ ነገሮችን የተነበይክላቸው ወዳጆችህ ሁሉ በዚያ ትቀበራላችሁ።"
7እግዚአብሔር ሆይ፣ አሳመንኸኝ፣ እኔም አምኛለሁ። ያዝኸኝ ደግሞም አሸነፍኸኝ። መላገጫ ሆኛለሁ። ሕዝቡ በየቀኑ፣ ቀኑን ሁሉ ይሳለቊብኛል።
8በተናገርሁ ቍጥር፣ 'ግፍና ጥፋት' ብዬ እጮኻለሁ። የእግዚአብሔርም ቃል ቀኑን ሁሉ ነቀፌታና ዋዛ ሆኖብኛልና።
9እኔም፣ 'ከእንግዲህ ወዲህ የእግዚአብሔርን ስም አላስብም። ከእንግዲህ ወዲህም ስሙን አላውጅም' ብል፣ ያን ጊዜ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደሚነድድ፣ በልቤ ውስጥ እንዳለ እሳት ሆነብኝ። ስለዚህ ልሸከመው ታገልሁ፣ ነገር ግን አልቻልሁም።
10በዙሪያዬ ካሉ ብዙ ሰዎች የሚያሽብር አሉባልታን ሰምቻለሁ። የቅርቤ ሰዎች የሆኑት ውድቀቴን ለማየት ጠበቊ፣ 'ምናልባት እንበረታበት እንደ ሆነ፣ ከዚያም እንበቀለው እንደ ሆነ 'ክሰሱት፣ እኛም እንከስሰዋለን' ይላሉ።
11እግዚአብሔር ግን እንደ ኃያል ጦረኛ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ። አያሸንፉኝም። አይከናወንላቸውምና፣ በእጅጉ ያፍራሉ። መቼም የማይረሳ በሚሆን እፍረት የማያበቃ እፍረት ያፍራሉ።
12ጻድቅን የምትመረምር፣ አእምሮንና ልብን የምትመለከት የሠራዊት ጌታ ሆይ፣ ክርክሬን አሳይቼሃለሁና በላያቸው በቀልህን ልይ።
13ለእግዚአብሔር ዘምሩ! እግዚአብሔርን አመስግኑ! የተጨቆኑትን ሰዎች ሕይወት ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና።
14የተወለድሁባት ቀን የተረገመች ትሁን። እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን የተባረከች አትሁን።
15'ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል' ብሎ ለአባቴ የነገረው ሰው የተረገመ ይሁን።
16ያም ሰው እግዚአብሔር ያለምሕረት እንደ ገለበጣቸው ከተሞች ይሁን። በማለዳም እርዳታ የሚለምን ጩኸትን በቀትርም የጦርነት እሪታን ይስማ።
17እግዚአብሔር በማኅፀን ውስጥ አልገደለኝምና ወይም እናቴን መቃብሬ አላደረገኝምና፣ ይህ ይከሰት።
18ችግርንና ጣርን አይ ዘንድ፣ ዘመኔም በእፍረት ይሞላ ዘንድ ለምን ከማኅፀን ወጣሁ?
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።