1እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፣ "ሂድና ከሸክላ ሠሪ ገምቦ ግዛ፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎችና ከካህናት ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ።
2የገል በር በሚከፈትበት ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ሂድ፣ በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር።
3እንዲህም በል፣ 'ይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ! የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ተመልከቱ! የሰማውን ሰው ጆሮ የሚያስጨንቅ ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ አመጣለሁ።
4ይህንን የማደርገው ስለተዉኝና ይህንን ስፍራ የባዕድ አማልክት አድርገውታልና ነው። እነርሱና አባቶቻቸው ለማያውቋቸው ለሌሎች አማልክት አጥነዋል፣ የይሁዳም ነገሥታት ይህንን ስፍራ በንጹህ ደም ሞልተዋል።
5እኔም ያላዘዝሁትን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ወንዶች ልጆቻቸውን ለበኣል በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ የበኣልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠርተዋል። ይህንን እንዲያደርጉ አልተናገርኳቸውም፣ በልቤም አላሰብሁትም።
6ስለዚህም፣ ተመልከቱ፣ ይህ ስፍራ የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ የማይባልበት ዘመን ይመጣል ይላል እግዚአብሔር።
7በዚህ ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን እቅድ ከንቱ አደርጋለሁ። በጠላቶቻቸው ፊት በሰይፍና ነፍሳቸውን ደግሞ በሚሹት እጅ እጥላቸዋለሁ። ከዚያም ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ።
8ከዚያም ይህችን ከተማ አጠፋና መደነቂያ አደርጋታለሁ፣ ስለ ተደረገባት መቅሠፍት ሁሉ የሚያልፍባት ሁሉ ይደነቃል፣ ከንፈሩንም ይመጥጣል።
9የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውንም ሥጋ አበላቸዋለሁ፣ ሁሉም ጠላቶቻቸውንና ነፍሳቸውን የሚሹት በሚያስጨንቋቸው ጭንቀትና መከበብ የጎረቤቶቻቸውን ሥጋ ይበላሉ።
10ከዚያም ገምቦውን ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ።
11እንዲህም ትላቸዋለህ፣ 'የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሸክላ ሠሪውን ዕቃ ኤርምያስ እንደሰባበረው፣ ደግሞም በድጋሚ ይጠገን ዘንድ እንደማይቻል፣ እንዲሁ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እሰብራለሁ፤ የሚቀብሩበትም ስፍራ እስከማይኖር ድረስ በቶፌት ይቀበራሉ።
12ይህችንም ከተማ እንደ ቶፌት ሳደርግ ለዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማደርገው ይህንኑ ነው ይላል እግዚአብሔር።
13የረከሱትም የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች፣ እነዚያ በሰገነታቸው ላይ ለሰማይ ከዋክብት ሁሉ ያጠኑባቸው ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን ያፈሰሱባቸው ቤቶች ሁሉ፣ እንደ ቶፌት ስፍራ ይሆናሉ።"
14ከዚያም ትንቢት እንዲናገር እግዚአብሔር ልኮት ከበረው ስፍራ፣ ከቶፌት ኤርምያስ መጣ። በእግዚአብሔርም ቤት አደባባይ ቆሞ ለሕዝብ ሁሉ እንዲህ አለ፣
15"የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ቃሌን እንዳይሰሙ አንገታቸውን አደንድነዋልና፣ በዚህች ከተማና በመንደሮችዋ ሁሉ ላይ የተናገርሁባትን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣለሁ።"