1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ መጣ፣ እንዲህም አለኝ፣
2"ሂድና በኢየሩሳሌም ጆሮ ጩኽ። እንዲህም በል 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በወጣትነትሽ የነበረሽን የኪዳን ታማኝነት፣ በታጨሽበት ጊዜ የነበረሽን ፍቅር፣ ዘር ባልተዘራበት ምድረ በዳ እንደ ተከተልሽኝ ስለአንቺ አስታውሳለሁ።
3እስራኤል ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነበረ፣ የእርሻው መከር በኩራትም ነበረ! ከበኩራቱ የበሉት ሁሉ ኃጢአት አድርገዋል! ክፉም ነገር ይመጣባቸዋል ይላል እግዚአብሔር።'"
4የያዕቆብ ቤትና የእስራኤልም ቤት ቤተሰቦች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "አባቶቻችሁ ምን ክፋት አግኝተውብኝ ነው እኔን ከመከተል የራቁት፣ ከንቱ ጣዖታትንም የተከተሉት፣ እና ራሳቸውም ከንቱ የሆኑት?
6እነርሱም 'ከግብጽ ምድር ያወጣን እግዚአብሔር፣ በምድረ በዳ ጉድጓድ ወዳለበት የአረባህ ምድር፣ በውኃ ጥምና በሞት ጥላ ምድር፥ ማንም በማያልፍበትና ማንም በማይቀመጥበት ምድር የመራን እግዚአብሔር ወዴት አለ?' አላሉም።
7ነገር ግን ፍሬዋንና ሌሎች መልካም ነገሮቿን እንድትበሉ ወደ ቀርሜሎስ ምድር አገባኋችሁ! ይሁን እንጂ በመጣችሁ ጊዜ፣ ምድሬን አረከሳችሁ፣ ርስቴንም አጐሳቈላችሁ!
8ካህናቱም 'እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም፥ ባለ የኦሪቶች ሊቅ የሆኑትም ስለ እኔ ግድ አላላቸውም! እረኞችም በደሉኝ፥ ነቢያትም ለበኣል ትንቢት ተናገሩ፣ ትርፍ የሌለውንም ነገር ተከተሉ።
9ስለዚህ እከስሳችኋለሁ - የልጆቻችሁንም ልጆች እከስሳለሁ።
10ወደ ኪቲም ደሴቶች እለፉና ተመልከቱ። ወደ ቄዳርም መልእክተኞችን ላኩና እንደዚህ ያለ ነገር ህኖ እንደ ሆነ መርምራችሁ እዩ።
11አማልክት ባይሆኑ እንኳን አማልክት ያልሆኑትን አማልክቱን የለወጣቸው አንድ ሕዝብ አለን? ነገር ግን ሕዝቤ ሊረዳቸው ለማይችለው ነገር ክብሩን ለወጠ።
12ሰማያት ከዚህ የተነሣ ተደነቁ! ተንቀጥቀጡ እና ደንግጡ ይላል እግዚአብሔር።
13ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች በእኔ ላይ አድርገዋልና፦ ውሃ ለመያዝ የማይችሉትን የተቀደዱ ጉድጓዶች ለራሳቸው በመቆፈር እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል!
14እስራኤል ባርያ ነውን? ወይስ በቤት የተወለደ አይደለምን? እናስ ብዝበዛ የሆነው ለምንድነው?
15የአንበሳ ደቦሎች በእርሱ ላይ አገሡ። ብዙ ድምጽ በማሰማት ምድሩን አስፈሪ አደረጉት! ከተሞቹም የሚኖርባቸው እንዳይኖር ሆኖ ተደመሰሰ።
16የሜምፎስና የጣፍናስ ልጆች የራስ ቅልሽን ላጭተው ባርያዎችን ከአንቺ ወሰዱ!
17ይህን ሁሉ በራስሽ ላይ ያደረግሽው በመንገድ ላይ ሲመራሽ አምላክሽን እግዚአብሔርን ስለተውሽ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር አምላክሽ።
18አሁንስ በግብጽ መንገድ ሄደሽ የሺሖርን ውኃ የምትጠጪው ለምንድነው? በአሦርስ መንገድ ሄደሽ የኤፍራጥስንም ውኃ የምትጠጪው ለምንድነው?
19ክፋትሽ ይገሥጽሻል፣ ክዳትሽም ይቀጣሻል፤ አምላክሽንም እግዚአብሔርን መተውሽ እኔንም መፍራት ማቆምሽ ክፉና መራራ ነገር እንደ ሆነ እወቂ፥ ተመልከቺ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
20ከጥንት ጀምሮ የነበረብሽን ቀንበር ሰብሬአለሁና፣ እስራትሽንም ቈርጫለሁ። እንዲህም ሆኖ አንቺ 'አላገለግልም!' አልሽ፥ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ተጋደምሽ፣ አንቺ አመንዝራ።
21እኔ ራሴ ግን የተመረጠች ወይን፣ ፈጽሞ እውነተኛ የሆነ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር። አንቺ ግን ክፉ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆነሽ እንዴት ተለወጥሽብኝ?
22በወንዝ ብትታጠቢ ወይም በብርቱ ሳሙና ብትታጠቢ፣ በእኔ ፊት በኃጢአትሽ ረክሰሻል ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
23'አልረከስሁም! በአሊምንም አልተከተልሁም' እንዴት ትያለሽ? በሸለቆዎች ያለውን ባህርይሽን ተመልከቺ! ያደረግሽውንም ተገንዘቢ፣ በመንገዷ ላይ እንደ ተለቀቀች ፈጣን ግመል ሆነሻል፤
24በምኞትዋ ከንቱ ነፋስን እንደምታሸትት፣ ምድረ በዳ እንደ ለመደች እንደ ሜዳ አህያ ነሽ! ከምኞትዋ የሚመልሳት ማን ነው? የሚፈልጋት ሁሉ ራሱን አያደክምም። ወደ እርሷ ሄደው በትኩሳቷ ወራት ያገኟታል።
25እግርሽን ባዶ ከመሆን፣ ጉሮሮሽንም ከውኃ ጥም ከልክዪ! አንቺ ግን 'ተስፋ-ቢስ ነው! አይሆንም፣ እንግዶችን ወድጄአለሁና እከተላቸዋለሁ!' አልሽ።
26ሌባ ሲያዝ እንደሚያፍረው ሁሉ፣ እንዲሁ የእስራኤል ቤት፣ እነርሱ፣ ንጉሦቻቸው፣ አለቆቻቸው፣ ካህናቶቻቸውና ነብያቶቻቸውም ያፍራሉ።
27ለዛፉ፣ 'አንተ አባቴ ነህ፣' ድንጋዮንም 'አንተ ወለድከኝ' ይላሉ። ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ። በመከራቸው ጊዜ ግን 'ተነሥና አድነን!' ይላሉ።
28ለአንተ የሠራሃቸው አማልክትህ ወዴት ናቸው? ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቊጥር እንዲሁ ናቸውና ይነሡ በመከራህም ጊዜ ያድኑህ!
29ስለዚህ እኔ እንዳጠፋሁ አድርጋችሁ የምትከስሱኝ ለምንድር ነው? ሁላችሁ በእኔ ላይ ኃጢአት ሠርታችሁብኛል ይላል እግዚአብሔር።
30ሕዝባችሁን በከንቱ ቀጥቼአቸዋለሁ፤ ተግሣጽን አልተቀበሉም፤ እንደሚሰብር አንበሳ ሰይፋችሁ ነቢያቶቻችሁን በልቶአል!
31ከዚህ ትውልድ የሆናችሁ እናንተ! የእግዚአብሔር ቃል ለሆነው ለቃሌ ትኩረት ስጡ! በውኑ ለእስራኤል ምድረ በዳ፣ ወይስ የጥልቅ ጨለማ ምድር ሆንሁባትን? ሕዝቤስ ስለ ምን 'እኛ እንቅበዝበዝ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ አንመለስም' ይላል?
32ደናግሏ ጌጥዋን፣ ወይስ ሙሽራ ዝርግፍ ጌጥዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን ለማይቈጠሩ ቀናት ረስቶኛል።
33ፍቅርን ለመሻት መንገድሽን እንዴት በደህና ታቀኛለሽ። እንደውም መንገድሽን ለክፉዎች ሴቶች እንኳ አስተምረሻል።
34የንፁሐን ሕይወት የሆነው ደም፣ የድሆችም ደም በልብሶችሽ ላይ ተገኝቷል። እነዚህ ሰዎች በስርቆሽ ተግባር የተያዙ አልነበሩም።
35ይልቊን፣ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ፣ 'ወቀሳ የለብኝም፤ በእውነት የእግዚአብሔር ቊጣ ከእኔ ተመልሶአል' አልሽ። ነገር ግን ተመልከቺ! 'ኃጢአት አልሠራሁም' ብለሻልና ይፈረድብሻል።
36መንገድሽን ትለዋውጪ ዘንድ ነገሩን ለምን ታቀልያለሽ? አሦር እንዳሳፈረሽ ግብጽ ያሳፍርሻል።
37እግዚአብሔር የታመንሽባቸውን ጥሎአልና፥ በእነርሱም አይከናወንልሽምና እጅሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ ከዚያ ደግሞ ትወጫለሽ።