1ይህ የኬልቅያስ ልጅ የሆነው የኤርምያስ ቃል ነው፤ እርሱ በብንያም ምድር ከነበሩት ካህናት አንደኛው ነበር።
2የአሞጽ ልጅ በሆነው በይሁዳ ንጉሥ ዐሥራ ሦስተኛ ዓመት አገዛዝ ዘመን ላይ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ።
3ቃሉ የመጣው በይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ በሆነው ኢዮአቄም ዘመን፣ የኢዮስያስ ልጅ በሆነው የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ የዐሥራ አንደኛው አመት አገዛዝ አምስተኛ ወር ድረስ፣ የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ምርኮኛ ሆነው ሲወሰዱ ነበር።
4የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፣
5"በማኅፀን ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብ ነቢይ አድርጌሃለሁ።"
6እኔም፣ "ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ ገና ብላቴና በመሆኔ እንዴት እንደምናገር አላውቅም" አልሁ።
7ነገር ግን እግዚአብሔር "'ገና ብላቴና ነኝ' አትበል። ወደምልክህ ሁሉ ልትሄድ ይገባል፣ የማዝዝህንም ሁሉ ልትናገር ይገባል!
8ላድንህ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ አትፍራ - ይህ የእግዚአብሔር ንግግር ነው።" አለኝ።
9እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፣ እንዲህም አለኝ "ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤
10ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾሜሃለሁ" አለኝ።
11የእግዚአብሔር ቃል "ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ?" እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም "የለውዝ በትር አያለሁ" አልሁት።
12እግዚአብሔርም "መልካም አይተሃል፣ እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና" አለኝ።
13የእግዚአብሔር ቃል ለሁለተኛ ጊዜ "ምን ታያለህ?" እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም "ፊቱ ከሰሜን አቅጣጫ የሆነ የሚፈላ ማሰሮ አያለሁ" አልሁ።
14እግዚአብሔርም "በዚህች ምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ከሰሜን አቅጣጫ ክፉ ነገር ይገለጣል" አለኝ።
15በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁና ይላል እግዚአብሔር። እነርሱም ይመጣሉ፣ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም መግቢያ በራፍ ላይ፣ በዙሪያዋ ባሉት በአጥሮቿ ሁሉ ላይ፣ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያኖራሉ።
16እኔን ስለተዉበት ክፋታቸው ሁሉ፣ ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ፣ በገዛ እጃቸው ለሠሯቸውም ስለሰገዱላቸው፣ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ።
17አንተ ራስህን አዘጋጅ! ተነሥና ያዘዝሁህን ሁሉ ንገራቸው። በእነርሱ ፊት አትፍራ፣ አሊያ እኔ በእነርሱ ፊት አስፈራሃለሁ!
18ተመልከት! ዛሬ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በይሁዳም ነገሥታት -በአለቆችዋና በካህናትዋ ላይ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ እንደ ተመሸገ ከተማ እንደ ብረትም ዓምድ እንደ ናስም ቅጥር አድርጌሃለሁ።
19ይዋጉሃል፣ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም" ይላል እግዚአብሔር።