መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 18

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል እንዲህ አለው፣
2"ተነሥተህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፣ በዚያም ቃሌን አሰማሃለሁና።
3ስለዚህም ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ወረድሁ፣ ሸክላ ሠሪውም ሥራውን በመንኵራኩር ላይ ይሠራ ነበር።
4ከጭቃም ይሠራው የነበረ ዕቃ በሸክላ ሠሪው እጅ ተበላሸ፣ ሸክላ ሠሪውም እንደ ወደደ መልሶ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው።
5የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፣
6"የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ዘንድ መሥራት አይቻለኝምን? ይላል እግዚአብሔር። ተመልከቱ! ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ፣ እንዲሁ እናንተ በእኔ እጅ ውስጥ አላችሁ።
7በአንድ ወቅት፣ አባርር፣ አፈርስ፣ ወይም አጠፋ ዘንድ ስለ ሕዝብ ወይም ስለ መንግሥት አንዳች ነገር እናገር ይሆናል።
8ነገር ግን ያንን የተናገርኩበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፣ ያኔ እኔ ላደርግበት ያሰብሁትን ክፉ ነገር እተወዋለሁ።
9በሌላ ጊዜ፣ ስለ ሕዝብ ወይም ስለ መንግሥት እንደምሠራው ወይም እንደምተክለው እናገራለሁ።
10ነገር ግን ድምፄን ባለመስማት በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ፣ ያኔ እኔ ላደርግለት የተናገርሁትን መልካም ነገር አቆማለሁ።
11አሁን እንግዲህ፣ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ተናገርና እንዲህ በላቸው፣ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከቱ፣ ክፉ ነገር ልፈጥርባችሁ ነው። እቅድንም ላወጣባችሁ ነው። መንገዶቻችሁ እና ልምምዶቻችሁ መልካምን እንዲያመጡላችሁ፣ እያንዳንዱ ሰው ከክፉ መንገዱ ንስሃ ይግባ'
12እነርሱ ግን፣ 'ይህ ጥቅም የለውም። እንደ እቅዶቻችን እናደርጋለን። እያንዳንዳችን ክፉ የሆነው ልባችን እንደተመኘው እልከኝነትን እናደርጋለን' አሉ።
13ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'እንዲህ ያለውን ነገር ማን ሰምቷል ብላችሁ አሕዛብን ጠይቊ። የእስራኤል ድንግል አስደንጋጭ ነገርን አድርጋለች።
14በውኑ የሊባኖስ በረዶ በሜዳ ያሉትን ድንጋያማ ኮረብቶች ይተዋልን? ወይስ ከሩቅ የምትመጣው ቀዝቃዛይቱ ፈሳሽ ውኃ ትደርቃለችን?
15ሕዝቤ ግን ረስተውኛል። ጥቅም ለሌላቸው ጣዖታት ሠውተዋል፤ ከመንገዳቸውም ተሰናክለዋል፤ በአነስተኞቹ መንገዶች ለመሄድ ሲሉ የቀደሙትን መንገዶች ትተዋል።
16ምድራቸው ለመደንገጪያና ለዘላለም ማፍዋጫ ይሆናል። የሚያልፍባት ሁሉ ይደነቃል፣ ራሱንም ይነቀንቃል።
17እንደ ምሥራቅ ነፋስ በጠላቶቻቸው ፊት እበትናቸዋለሁ። በጥፋታቸውም ቀን ፊቴን ሳይሆን ጀርባዬን አሳያቸዋለሁ።"
18እነርሱም፣ "ሕግ ከካህናት፣ ወይም ምክር ከጠቢባን፣ ወይም ቃልም ከነቢያት አይጠፋምና ኑ፣ በኤርምያስ ላይ እናሲር። ኑ፣ በቃላችን እናጥቃው፣ የሚናገረውንም ሁሉ ትኩረት አንስጠው" አሉ።
19እግዚአብሔር ሆይ፣ አድምጠኝ! የጠላቴንም ድንፋታ ስማ።
20ጕድጓድ ቈፍረውልኛልና መልካም ስለሆንኩላቸው ከእነርሱ የሚሆን ጥፋት ክፍያዬ ይሆናልን? ለደህንነታቸው ለመናገር፣ ከእነርሱ ቊጣህን ለመመለስ በፊት እንደቆምኩ አስታውስ።
21ስለዚህ ልጆቻቸውን ለራብ ስጥ፣ ለሰይፍም ኃይል አሳልፈህ ስጣቸው። ሚስቶቻቸውም የወላድ መካንና መበለቶች ይሁኑ፣ ወንዶቻቸውም ይገደሉ፣ ወጣቶቻቸውም በጦርነት ጊዜ በሰይፍ ይመቱ።
22ሊይዙኝ ጕድጓድ ቆፍረዋልና፣ ለእግሮቼም ድብቅ ወጥመድ አኑረዋልና በላያቸው ጭፍራን በድንገት ባመጣህ ጊዜ፣ ከቤታቸው ጩኸት ይሰማ።
23አንተ ግን፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ይገድሉኝ ዘንድ በላዬ ያቀዱትን ዕቅድ ሁሉ ታውቃለህ። በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር አትበል። ኃጢአታቸውንም ከአንተ ዘንድ አትደምስስ። ይልቅ፣ በፊትህ ይውደቁ። በቍጣህ ጊዜ እንዲሁ አድርግባቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።