1"የይሁዳ ኃጢአት የሾለ አልማዝ ባለው የብረት ብዕር ተጽፎአል። በልባቸው ጽላትና በመሠዊያቸው ቀንዶች ላይ ተቀርጾአል።
2ልጆቻቸውም ከለመለሙ ዛፎች በታችና በከፍተኞቹ ኮረብቶች ላይ ያሉትን መሠዊያቸውንና አሼራ የምትባለውን ጣዖታቸውን ያስባሉ።
3በገጠር ባሉት ተራሮች ላይ ያሉትን መሠዊያዎቻቸውን ያስታውሳሉ። ባለጠግነታችሁንና መዝገባችሁን ሁሉ፣ የኮረብታውን መስገጃዎቻችሁንም በኃጢአታችሁ ምክንያት እንዲበዘበዙ አደርጋለሁ።
4አናንተም የሰጠኋችሁን ርስት ትለቅቃላችሁ። በማታውቋትም ምድር ለጠላቶቻችሁ ባሪያ አደርጋችኋለሁ፤ ለዘላለም የሚነድደውን እሳት በቍጣዬ አንድዳችኋልና።
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "በሰው የሚታመን፣ ሥጋ ለባሹንም ብርታቱ የሚያደርግ፣ ልቡን ግን ከእግዚአብሔር የሚመልስ ሰው ርጉም ነው።
6በአረብ ምድር እንዳለ ትንሽ ቍጥቋጦ ይሆናል፣ የሚመጣውንም መልካም ነገር አያይም። ሰውም በሌለበት ዐለታማ ምድር ውስጥ ደረቅ በሆነ ምድረ በዳ ይቀመጣል።
7ነገር ግን በእግዚአብሔር የታመነ፣ የልበ-ሙሉነቱ ምክንያት እግዚአብሔር ነውና ቡሩክ ነው።
8በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፣ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ተክል ይሆናልና። ሙቀት ሲመጣ አያይም፣ ቅጠሉ ይለመልማልና። ከዚያም፣ በድርቅ ዓመት ላይ አይሠጋም፣ ማፍራቱንም አያቋርጥም።
9ልብ ከየትኛውም ነገር ይልቅ ተንኰለኛ ነው። በሽተኛ ነው፤ ማንስ ያስተውለዋል?
10ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ ልሰጥ ልብን የምመረምር፣ ኵላሊትንም የምፈትን እግዚአብሔር እኔ ነኝ።
11ያልጣለችውን እንቁላል እንደምታቅፍ ቆቅ፣ እንዲሁ አንድ ሰው ያለፍትህ ባለጠጋ ይሆን ይሆናል። ነገር ግን በእኩሌታ ዘመኑ ላይ ብልጥግናው ይተወዋል፣ በፍጻሜውም ሰነፍ ይሆናል።
12የመቅደሳችን ስፍራ ከመጀመሪያም ጀምሮ ክፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው።
13እግዚአብሔር የእስራኤል ተስፋ ነው። አንተን የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ። ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና በምድር ላይ ይቆረጣሉ።
14እግዚአብሔር ሆይ፣ ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ! አድነኝ እኔም እድናለሁ። አንተ የምስጋናዬ ዝማሬ ነህና።
15ተመልከቱ፣ 'የእግዚአብሔር ቃል ወዴት ነው? ይምጣ!' ይሉኛል።
16እኔም አንተን ተከትዬ እረኛ ከመሆን አልሮጥሁም። የመከራንም ቀን አልታገሥሁም። ከከንፈሬ የመጣውን አንተ ታውቃለህ። በህልውናህ ፊት ተነግረዋል።
17መሸበሪያ አትሁንብኝ። በመከራ ቀን አንተ መጠጊያዬ ነህ።
18አሳዳጆቼ ይፈሩ፣ እኔ ግን አልፈር። እነርሱ ይደንግጡ፣ እኔ ግን አልደንግጥ። የጥፋትን ቀን አምጣባቸው፣ በሁለት እጥፍ ጥፋት አጥፋቸው።
19እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ "ሂድና የይሁዳም ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት የሕዝቡ በር፣ ከዚያም በኢየሩሳሌምም በሮች ሁሉ ቁም።
20እንዲህም በላቸው፣ 'በእነዚህ በሮች የምትገቡ እናንተ የይሁዳ ነገሥታት፣ የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ፣ የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ለራሳችሁ ሕይወት ተጠንቀቁ፥ በኢየሩሳሌምም በሮች እንድታገቡ በሰንበት ቀን ሸክምን አትሸከሙ።
22በሰንበት ቀን ከቤቶቻችሁ ሸክምን አታውጡ። የትኛውንም ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፣ ነገር ግን አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁት የሰንበትን ቀን ቀድሱ።"
23እነርሱ ግን ትኩረት ሰጥተው አልሰሙም፣ እንዳይሰሙና ተግሣጽን እንዳይቀበሉ አንገታቸውን አደነደኑ።
24እኔን ፈጽሞ ብትሰሙ ይሆናል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ደግሞም በሰንበት ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም አታምጡ፣ ይልቊንም የሰንበትን ቀን ለእግዚአብሔር ቀድሱ የትኛውንም ሥራ አትሠሩበት፤
25በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መሳፍንት በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ እየተቀመጡ በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፣ እነርሱና መሳፍንቶቻቸው የይሁዳም ነዋሪዎች በኢየሩሳሌምም የሚቀመጡ ይመጣሉ። ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ሆና ትቀራለች።
26የሚቃጠለው መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም የምስጋናውንም መሥዋዕት ይዘው ከይሁዳ ከተሞች ከኢየሩሳሌምም ዙሪያ ከብንያምም አገር ከቈላውም ከደጋውም ከኔጌቭም ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ።
27ነገር ግን የሰንበትን ቀን ልትቀድሱ፣ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች ልትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፣ እሳትን በበሮችዋ ላይ እለኩሳለሁ፣ የኢየሩሳሌምንም ምሽጎች ትበላለች፣ እሳቱም አይጠፋም።