1ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፣
2"በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይኑርህ።
3እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ስለ ተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፣ ስለወለዱአቸውም ስለ እናቶቻቸው፣ በዚህችም ምድር እንዲወለዱ ስላደረጉ አባቶቻቸው እንዲህ ይላል፣
4በበሽታ ሞት ይሞታሉ። አይለቀስላቸውም ወይም አይቀበሩም። በመሬትም ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ። በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፣ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናሉ።'
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ልቅሶ ወዳለበት የትኛውም ቤት አትግባ። ታለቅስም፣ ታዝንም ዘንድ አትሂድ። ሰላሜን፣ ቸርነትና ምሕረትን፣ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና!
6ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ። አይቀበሩም፣ ሰዎችም አያለቅሱላቸውም። ስለ እነርሱም ገላን አይነጩላቸውም ራስንም አይላጩላቸውም።
7ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የእዝን እንጀራን ሊካፈሉ አይገባም፣ ለአባታቸውና ለእናታቸውም ማንም የመጽናናት ጽዋ ሊሰጧቸው አይገባም።
8ትበላና ትጠጣ ዘንድ ከእነርሱ ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ።'
9የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ 'ተመልከት፣ በዐይናችሁ ፊት በዘመናችሁም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፣ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቆማለሁ።'
10ከዚያም ለዚህ ሕዝብ ይህን ቃል ሁሉ በተናገርህ ጊዜ፣ 'እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ታላቅ የሆነ ክፉ ነገር ለምን ተናገረብን? በደላችንስ ምንድር ነው? በአምላካችንስ በእግዚአብሔር ላይ የሠራነው ኃጢአታችን ምንድር ነው? ሲሉህ፣
11እንዲህ በላቸው፣ 'አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተው ነው፣ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ሌሎችን አማልክት ተከተሉ አመለኩአቸውም ሰገዱላቸውም። እነርሱም ትተውኛል፣ ሕጌንም አልጠበቁም።
12ነገር ግን፣ እናንተ ራሳችሁ ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፤ ተመልከቱ፣ እያንዳንዱ ሰው በክፉ ልብ እልከኝነት ሄዷል፣ እኔንም የሚሰማ የለም።
13ስለዚህ ከዚህች ምድር እናንተና አባቶቻችሁ ወዳላወቃችኋት ምድር እጥላችኋለሁ፣ ሞገስን አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታመልካላችሁ።
14ስለዚህ ተመልከቱ! ከእንግዲህ 'የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!' የማይባልበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል እግዚአብሔር።
15ነገር ግን፣ የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር፣ ካሳደዳቸውም ምድር ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
16ተመልከቱ! ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እሰድዳለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ሕዝቡን ሊያወጡ ያጠምዱአቸዋል። ከዚህም በኋላ ብዙ አጥማጆችን እሰድዳለሁ፣ እነርሱም ከየተራራውና ከየኮረብታው ሁሉ ከየድንጋዩም ስንጣቂ ውስጥ ያጠምዷቸዋል።
17ዓይኔ በመንገዳቸው ሁሉ ላይ ነውና፤ ከፊቴም ሊሰወሩ አይችሉም። በደላቸውም ከዓይኔ ሊሰወር አይችልም።
18በተጠሉ ጣዖቶቻቸው ሬሳዎች ምድሬን አርክሰዋልና፣ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና፣ አስቀድሜ የበደላቸውንና የኃጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ።"
19እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ምሽጌ፣ አምባዬ፣ በመከራም ቀን መጠጊያዬ ነህ። አሕዛብ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ ሄደው፣ "በእርግጥ አባቶቻችን ውሸትን ወርሰዋል። ባዶ ናቸው፤ በእነርሱ ዘንድ ትርፍ የለም ይላሉ።
20በውኑ ሕዝቦች አማልክት ያልሆኑትን ለራሳቸው አማልክትን አድርገው ይሠራሉን?
21ስለዚህ ተመልከቱ! በዚህ ጊዜ አስታውቃቸዋለሁ፣ እጄንና ኃይሌን አስታውቃቸዋለሁ፤ ከዚህም የተነሣ ስሜ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቃሉ።"