መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 15

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔርም እንደዚህ አለኝ፣ "ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም እንኳን፣ ለዚህ ሕዝብ አላደላም። እንዲወጡ ከፊቴ አባርራቸው።
2እነርሱም፣ 'ወዴት እንሂድ?' ቢሉህ፣ ያኔ አንተ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሞት የተወሰኑት ወደ ሞት፣ ለሰይፍም የተወሰኑት ወደ ሰይፍ፣ ለራብም የተወሰኑት ወደ ራብ፣ ለምርኮም የተወሰኑት ወደ ምርኮ' ትላቸዋለህ።
3አራቱን ዓይነት ጥፋት አዝዝባቸዋለሁ፣ እነርሱም አንዳንዶችን የሚገድል ሰይፍ፣ አንዳንዶችን የሚጎትቱ ውሾችን፣ አንዳንዶችን የሚበሉ የሰማያትን ወፎች፣ የምድርንም አራዊት ናቸው ይላል እግዚአብሔር።
4የይሁዳም ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ስላደረገው ሁሉ ለምድር መንግሥታት ሁሉ መጨነቂያ አደርጋቸዋለሁ።
5ኢየሩሳሌም ሆይ የሚራራልሽ ማን ነው? የሚያዝንልሽስ ማን ነው? ወይስ ስለ ደኅንነትሽ ይጠይቅ ዘንድ ዘወር የሚል ማነ ነው?
6አንቺ እኔን ጥለሻል፣ ይላል እግዚአብሔር፣ ወደ ኋላሽም ተመልሰሻል። ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ እመታሽና አጠፋሻለሁ። ለአንቺ ምሕረት ማድረግ አድክሞኛል።
7በአገርም ደጆች ውስጥ በመንሽ አበጥራቸዋለሁ። ልጆቻቸውንም እነጥቃለሁ። ከመንገዳቸውም አልተመለሱምና ሕዝቤን አጠፋለሁ።
8መበለቶቻቸውን ከባሕር አሸዋ ይልቅ አበዛለሁ። በቀትር ጊዜ ላይ በብላቴኖች እናት ላይ አጥፊውን እልካለሁ። ድንጋጤና ሽብር በድንገት እንዲወድቅባቸው አደርጋለሁ።
9ሰባት የወለደች ትደክማለች። ታለከልካለች። ገና ቀን ሳለ ፀሐይዋ ትገባባታለች። የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁና ታፍራለች፣ ትዋረድማለች።
10እናቴ ሆይ፣ ወዮልኝ! በምድሪቱ ሁሉ የክርክርና የጥል ሰው የሆንሁትን እኔን ወልደሽኛልና። አላበደርሁም፣ ከማንም አልተበደርኩም፣ ነገር ግን ሁሉ ይረግመኛል።
11እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ "በእውነት ለደኅንነትህ አልታደግህምን? በእርግጥ በመከራና በጭንቅ ጊዜ ጠላቶችህ እንዲለምኑህ አደርጋለሁ።
12ሰው ብረትን ይሰብራልን? በተለይ ከሰሜን የሆነውን ከናስ ጋር የተቀየጠውን ብረት የሚሰብር አለን?
13ባለጠግነትህንና መዝገብህን ለመበዝበዝ በነፃ እሰጣለሁ። ይህንንም የማደርገው በድንበሮችህ ሁሉ ስለፈጸምከው ኃጢአትህ ሁሉ ነው።
14ከዚያም፣ ጠላቶችህ ወደማታውቀው ምድር እንዲወስዱህ አደርጋለሁ፣ የምታቃጥላችሁ እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና።
15አንተ ራስህ ታውቃለህ፣ እግዚአብሔር ሆይ! አስበኝ እርዳኝም። የሚያሳድዱኝንም ተበቀላቸው። በትእግሥትህ አታርቀኝ። ስለ አንተ ነቀፌታን እንደ ጠገብሁ እወቅ።
16ቃሎችህ ተገኝተዋል እኔም በልቼያቸዋለሁ። የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃሎችህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆኑልኝ።
17በሚፈነድቁትና በደስተኞች ዙሪያ አልተቀመጥሁም። በቍጣህ ሞልተኸኛልና በኃይለኛው እጅህ ፊት ለብቻዬ ተቀመጥሁ።
18ስለ ምን ሕመሜ አዘወተረኝ፣ ቍስሌስ ስለ ምን ፈውስን የማይቀበልና የማይሽር ሆነ? በውኑ እንደ አታላይ ምንጭ፣ እንደደረቅ ውኃ ትሆናለህን?
19ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ኤርምያስ ሆይ፣ ንስሃ ብትገባ፣ እንደ ቀድሞው እመልስሃለሁ፣ በፊቴም ቆመህ ታገለግለኛለህ። የተዋረደውንም ከከበረው ብትለይ፣ እንደ አፌ ትሆናለህ። ሕዝቡ ወደ አንተ ይመለሳሉ፣ አንተ ራስህ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም።
20ለዚህም ሕዝብ የማይጣስ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፣ ይዋጉሃል። ነገር ግን እኔ ላድንህ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም ይላል እግዚአብሔር።
21ከክፉ ሰዎችም እጅ እታደግሃለሁ፣ ከጨካኞችም ቡጢ እቤዥሃለሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።