መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 14

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለ ድርቅ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፣
2"ይሁዳ ታልቅስ፣ ደጆችዋም ይውደቊ። ስለ ምድራቸው እያለቀሱ ናቸው፤ ለኢየሩሳሌም የሚያለቅሱት ከፍ ብሎአል።
3ኃያላኖቻቸውም አገልጋዮቻቸውን ለውኃ ሰደዱ። ወደ ጕድጓድ ሲመጡ ውኃ ሊያገኙ አልቻሉም። ሁሉም ሳይሳካላቸው ተመለሱ፤ አፍረውና ተዋርደው ራሳቸውን ተከናነቡ።
4ከዚህ የተነሣ በምድሪቱ ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ሆነ። አራሾች አፈሩ ራሳቸውንም ተከናነቡ።
5ዋላ በምድረ በዳ ወልዳ ሣር ባለመኖሩ ግልገልዋን ተወች።
6የሜዳ አህዮችም በወና ኮረብታ ላይ ቆመው እንደ ቀበሮ ወደ ነፋስ አለከለኩ። ልምላሜ የለምና ዓይኖቻቸው ፈዘዙ።
7ኃጢአታችን ቢመሰክርብንም፣ እግዚአብሔር ስለ ስምህ ሥራ። ያልታመንንባቸው ተግባራቶቻችን ጨምረዋልና፣ በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናል።
8የእስራኤል ተስፋ ሆይ፣ በጭንቀት ጊዜ የምታድነው አምላክ ወደ ማደሪያ ዘወር እንደሚል መንገደኛ በምድሪቱ ላይ ለምን እንደ እንግዳ ትሆናለህ?
9ግራ እንደተጋባ ሰው፣ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኃያል ለምን ትሆናለህ? አንተ ግን፣ በመካከላችን ነህ፣ እግዚአብሔር ሆይ እኛም በስምህ ተጠርተናል። አትተወን።
10እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፣ "መቅበዝበዝን ወድደዋልና፣ እግራቸውንም እንዲህ ከማድረግ አልከለከሉም፤" ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አላለውም። አሁን በደላቸውን ያስባል ኃጢአታቸውንም ይቀጣል።
11እግዚአብሔርም፣ "ለዚህ ሕዝብ መልካም እንዲሆንላቸው አትጸልይላቸው።
12ቢጾሙ ጸሎታቸውን አልሰማም፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም። በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ አለኝ።
13ከዚያም፣ "ኦ፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ወዮ! እነሆ! ነቢያት ለሕዝቡ፣ 'በዚህ ስፍራ በእውነት ሰላምን እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፣ ራብም አያገኛችሁም ይሉአቸዋል" እያሉ ናቸው።
14እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፣ "ነቢያቱ በስሜ የውሸት ትንቢት ይናገራሉ። አልላክኋቸውም፣ አላዘዝኋቸውም፣ አልተናገርኳቸውምም። ነገር ግን፣ የውሸት ራእይና ጥቅም የለሽ የሆነ ከንቱ ምዋርትን፣ የልባቸውንም ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።"
15ስለዚህ እግዚአብሔር፣ "በዚህች አገር ሰይፍና ራብ አይሆንም ስለሚሉ፣ ነገር ግን በስሜ ትንቢት ስለሚናገሩ ስላልላክኋቸው ነቢያት እንዲህ ይላል፦ እነዚህ ነብያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ።
16ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይበተናሉ፤ ክፋታቸውንም አፈስስባቸዋለሁ እነርሱንና ሚስቶቻቸውን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም።
17ይህንን ቃል ንገራቸው፦ 'ዐይኖቼ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባ ያፍስሱ። ድንግሊቱ የሕዝቤ ልጅ በታላቅ ስብራትና እጅግ ክፉ በሆነ ቍስል ተሰብራለችና ።
18ወደ ሜዳ ብወጣና ባይ! በሰይፍ የሞቱ አሉ። ወደ ከተማም ብገባ፣ ያኔም በራብ የታመሙ አሉ። ነቢዩና ካህኑም ወደማያውቋት አገር ሄደዋል።"
19በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ጽዮንንስ ጠልተሃታልን? ፈውስ በማይኖረን ጊዜ ስለ ምን መታኸን? ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፣ መልካምም አልተገኘም፤ ፈውስን በተስፋ ተጠባበቅን፣ ተመልከቱ፣ ያለው ግን ድንጋጤ ብቻ ነው።
20እግዚአብሔር ሆይ፣ በአንተ ላይ ኃጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን።
21አትጣለን! ስለ ስምህ፣ የክብርህንም ዙፋን አታስነውር። ከእኛ ጋር ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስብ እንጂ አታፍርስ።
22በውኑ በአሕዛብ ጣዖታት መካከል የጸደይን ዝናብ ከሰማይ ያዘንብ ዘንድ የሚችል ይገኛልን? ይህንን የምታደርግ አምላካችን እግዚአብሔር አንተ አይደለህምን? እነዚህን ሁሉ አድርገሃልና ስለዚህ አንተን ተስፋ እናደርጋለን።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።