መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 13

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፣ "ሂድ፣ ከተልባ እግር የተሠራ የውስጥ ሱሪ ግዛና ወገብህን ታጠቅ፤ ነገር ግን አስቀድመህ በውኃ ውስጥ አትንከረው።
2ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳለው የውስጥ ሱሪን ገዛሁና ወገቤን ታጠቅሁበት።
3ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እኔ መጣና እንዲህ አለኝ፣
4በወገብህ ያለውን የገዛሃውን መታጠቂያ ወስደህ ተነሥና ወደ ኤፍራጥስ ሂድ። በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽገው" አለኝ።
5እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ ሄድሁና በኤፍራጥስ ሸሸግሁት።
6ከብዙ ቀንም በኋላ፣ እግዚአብሔር፣ "ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ። በዚያም እንድትሸሽገው ያዘዝሁህን የውስጥ ሱሪ ከዚያ ውሰድ" አለኝ።
7እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄድሁ ቆፈርሁም፣ ከሸሸግሁበትም ስፍራ የውስጥ ሱሪውን ወሰድሁ። ነገር ግን እነሆ! የውስጥ ሱሪው ተበላሽቶ ነበር፣ ለምንም የማይጠቅም ሆኖ ነበር።
8ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ በድጋሚ መጣና እንዲህ አለኝ፣
9"እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንዲሁ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ታላቅ እብሪት አጠፋለሁ።
10ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ የሚሉ፣ በልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፣ ያመልኩአቸውና ይሰግዱላቸው ዘንድ ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንዳማይረባ እንደሆነው እንደዚ የውስጥ ሱሪ ይሆናሉ።
11የውስጥ ሱሪው በሰው ወገብ ላይ እንደሚጣበቅ፣ እንዲሁ ሕዝብና ስም ምስጋናና ክብር ይሆኑልኝ ዘንድ የእስራኤልን ቤት ሁሉ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ ይላል እግዚአብሔር። ነገር ግን አልሰሙኝም።
12ስለዚህ ይህንን ቃል ለእነርሱ ልትናገር ይገባል፣ 'የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል።' እነርሱም 'ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንዲሞላ በውኑ እኛ አናውቅምን?' ይሉሃል።
13ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከቱ፣ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፣ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት፣ ካህናቱን፣ ነቢያቱንና በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ።'
14ሰውንም በሰው ላይ፣ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ፣ እቀጠቅጣለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራም፣ አላዝንላቸውም፣ አልምርም።"
15ስሙ፣ አድምጡም። እግዚአብሔር ተናግሮአልና እብሪተኞች አትሁኑ።
16ሳትጨልም እግራችሁም በጨለመችው ተራራ ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨለማ ሳይለውጠው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ።
17ይህን ባትሰሙ፣ ስለ ትዕቢታችሁ ብቻዬን አለቅሳለሁ። የእግዚአብሔርም መንጋ ተማርኮአልና ዓይኔ ታነባለች፣ እንባንም ታፈስሳለች።
18ለንጉሡና ንግሥቲት ለሆነችው እናት፣ 'የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ራሳችሁን አዋርዳችሁ ተቀመጡ' በል።
19የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፣ የሚከፍታቸውም የለም። ይሁዳ ሁሉ ተማርኮአል፣ ፈጽሞ ተማርኮአል።
20ዓይናችሁን አንሥታችሁ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቱ፤ ለአንቺ የሰጠው መንጋ፣ ለአንቺ የተዋበው መንጋሽ ወዴት አለ?
21ወዳጆችሽ እንዲሆኑ ያስተማርሻቸውን እግዚአብሔር በራስሽ ላይ አለቆች ባደረጋቸው ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አንቺንም የሚይዝሽ የምጥ ስቃይ ጅማሬ አይደለምን?
22በልብሽም፣ 'እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን ደረሰብኝ?' ብትዪ፣ የቀሚስሽ ዘርፍ ተገልጦ የተገፈፍሽው ከብዙ ኃጢአትሽ የተነሣ ነው።
23የኩሽ ሕዝቦች የቆዳ ቀለማቸውን፣ ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? ከሆነ፣ በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ መልካምን ማድረግ ትችላላችሁ።
24ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ።
25ረስተሽኛልና፣ በሐሰትም ታምነሻልና የሰጠኹሽ፣ የደነገግሁልሽም እድል ፈንታ ይህ ነው፣ ይላል እግዚአብሔር።
26ስለዚህም የቀሚስሽን ዘርፍ እኔ ራሴ በፊትሽ እገልጣለሁ፣ የእፍረት አካልሽም ይታያል።
27አስጸያፊ ሥራሽን፣ ምንዝርናሽን፣ ማሽካካትሽን፣ የግልሙትናሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ በሜዳም የሆኑትን እነዚህን አስፀያፊ ነገሮች እንዲታዩብሽ አደርጋለሁ! ወዮልሽ፣ ኢየሩሳሌም! አልነፃሽም። ይህስ እስከ መቼ ይቀጥላል?"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።