1እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ እግዚአብሔር ለእናንተ የተናገረውን ቃል ስሙ።
2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'የአሕዛብን መንገድ አትማሩ፣ ከሰማይ በሚሆኑት ምልክቶችም አትፍሩ፣ አሕዛብ እነዚህን ይፈራሉና።
3የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና። አንድ ሰው ዛፍን ከጫካ ይቈርጣል፤ የሠራተኛም እጅ በመጥረቢያ ይህንን ይሠራል።
4ከዚያም በብርና በወርቅ ያስጌጡታል። እንዳይወድቅም በመዶሻና በሚስማር ይቸነክሩታል።
5እነዚህ ጣዖታት ምንም ማለት ስለማይችሉ፣ በዱባ ማሳ ላይ እንደ ተቀረጸ ዓምድ ናቸው። ጨርሶ መራመድ ስለማይችሉ ሊይሸከሟቸው ይገባል። ክፉ መሥራት አይቻላቸውምና፣ ደግምም የትኛውንም መልካም ነገር ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው።
6እግዚአብሔር ሆይ እንደ አንተ ያለ የለም። አንተ ታላቅ ነህ፣ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው።
7የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፣ የማይፈራህ ማነው? በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል ወይም በታማኝ መንግሥታቸውም ሁሉ መካከል እንደ አንተ ያለ ስለሌለ፣ አንተ ይህ ይገባሃል።
8እነርሱ ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው፣ ደንዝዘዋል፣ ደንቍረውማል፤ እንጨት ብቻ እንጂ ምንም ላልሆኑ ጣዖቶቻቸው ደቀመዛሙርት ናቸው።
9ከጠርሴስ አንጥረኛ የቀጠቀጠውን ብር፣ ከአፌዝም ወርቅ ያመጣሉ። ልብሳቸውም ሰማያዊና ቀይ ግምጃ ነው። ብልሃተኞች ሰዎቻቸው እነዚህን ሁሉ ነገሮች ይሠራሉ።
10እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው። እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው። ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፣ አሕዛብም ቊጣውን መቋቋም አይችሉም።
11እናንተም "ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ" ትሏቸዋላችሁ።
12ምድርን በኃይሉ የፈጠረው፣ ደረቊን ምድር በጥበቡ የመሠረተው ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።
13ድምፁ በሰማይ የውኾችን ድምፅ ይፈጥራል፣ ከምድርም ጠርዝ ደመናትን ከፍ ያደርጋል። ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፣ ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።
14እያንዳንዱ ሰው እውቀት አጥቶ አላዋቂ ሆኗል። እያንዳንዱ አንጥረኛ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፣ ሕይወትም የለባቸውምና በቀረጸው ጣዖት አፍሮአል።
15እነርሱ ጥቅም የለሽ፣ የቀልደኞች ሥራ ናቸው፤ በሚቀጡበት ጊዜ ይጠፋሉ።
16የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፣ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና። እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስሙ ነው።
17በከበባ ውስጥ የምትኖሩ እናንተ ሕዝቦች፣ ዕቃችሁን ሰብስቡና ምድሪቱን ትታችሁ ውጡ።
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ "ተመልከቱ፣ በዚህ ጊዜ በምድሪቱ የሚኖሩትን ልወረውራቸው ነው። አስጨንቃቸዋለሁ፣ እንደዚያም ሆኖ ያገኙታል።
19ስለ ተሰበረው አጥንቴ ወዮልኝ! ቍስሌም መርቅዟል። ስለዚህ እኔ፣ "በእውነት ይህ የመከራ ጩኸቴ ነው ልሸከመውም ይገባኛል" አልሁ።
20ድንኳኔ ተበዘበዘ፣ አውታሬም ሁሉ ለሁለት ተቈረጠ። ልጆቼም ከእኔ ወሰዷቸው፣ ስለዚህ ከእንግዲህ የሉም። ድንኳኔንም ከእንግዲህ ወዲህ የሚዘረጋ መጋረጃዎችንም የሚያነሣ የለም።
21እረኞች ደንቆሮዎች ሆነዋል። እግዚአብሔርን አልፈለጉትምና። ስኬት አልሆነላቸውም፤ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል።
22የወሬን ድምፅ ስሙ፣ "ተመልከቱ! እየመጣ ነው! የይሁዳን ከተሞች ባድማና የቀበሮ ማደሪያ ያደርጋቸው ዘንድ ከሰሜን ጽኑ የምድር ነውጥ መጥቶአል።"
23እግዚአብሔር ሆይ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይመጣ አውቃለሁ። የሚራመድ የትኛውም ሰው የገዛ አካሄዱን አያቀናም።
24እግዚአብሔር ሆይ እንዳታጠፋኝ በቊጣህ ሳይሆን በፍትህ ቅጣኝ።
25በማያውቁህ አሕዛብ፣ ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ መዓትህን አፍስስ። ያዕቆብን በልተውታልና፣ ፈጽመው ሊያጠፉት ውጠውታልና ማደሪያውንም አፍርሰዋልና።