1የይሩበኣል ልጅ አቤሜሌክ ወደ እናቱ ዘመዶች ወደ ሴኬም ሄደና ለእነርሱና ለእናቱ ቤተሰብ ጎሳ በሙሉ እንዲህ አላቸው፣
2“በሴኬም የሚገኙ መሪዎች በሙሉ ይሰሙ ዘንድ ይህን ተናገሩ፣ ‘ለእናንተ የሚሻለው የትኛው ነው? የይሩበኣል ሰባ ልጆች ሁሉ ቢገዙአችሁ ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ?’ እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ የሥጋችሁ ቍራጭ እንደ ሆንሁ አስቡ፡፡”
3የእናቱም ዘመዶች ስለ እርሱ ለሴኬም መሪዎች ተናገሩ፣ እነርሱም አቤሜሌክን ለመከተል ተስማሙ፣ “እርሱ ወንድማችን ነው” ብለዋልና፡፡
4እነርሱም ከበኣልብሪትም ቤት ሰባ ብር ሰጡት፣ አቤሜሌክም እርሱን የተከተሉትን ስርዓት አልበኞችንና ወሮበሎችን ለመቅጠር ተጠቀበመት፡፡
5እርሱም ወደ አባቱ ቤት ወደ ዖፍራ ሄደ፣ የይሩበኣልን ልጆች ሰባ ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ አረዳቸው፡፡ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለነበር እርሱ ብቻ ተረፈ፡፡
6የሴኬምና የቤትሚሎ መሪዎች ሁሉ በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፣ እነርሱም ሄደው በሴኬም በዓምዱ አጠገብ ባለው በበሉጥ ዛፍ ስር አቤሜሌክን አነገሡት፡፡
7ለኢዮአታም ይህን ነገር በነገሩት ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ራስ ላይ ሄደና ቆመ፡፡ ድምፁንም ከፍ አድርጎ ጮኸና እንዲህ አላቸው፣ “እናንተ የሴኬም መሪዎች፣ እግዚአብሔርም እናንተን ይሰማ ዘንድ፣ እኔን ስሙኝ፡፡
8አንድ ጊዜ ዛፎች በእነርሱ ላይ የሚያነግሱት ለመቀባት ሄዱ፡፡ እነርሱም ለወይራ ዛፍ ‘በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት፡፡
9የወይራ ዛፍ ግን ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፣ ‘እግዚአብሔርና ሰዎችን ለማክበር የሚጠቅመውን ቅባቴን ትቼ ተመልሼ በሌሎች ዛፎች ላይ ለመወዛወዝ ልሂድን?’
10ዛፎቹም ለበለስ ዛፍ እንዲህ አሉት፣ ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ፡፡’
11ነገር ግን የበለሱ ዛፍ፣ ጣፋጭነቴንና መልካሙን ፍሬዬን ትቼ ተመልሼ በሌሎች ዛፎች ላይ ለመወዛወዝ ልሂድን?’ አላቸው፡፡
12ዛፎችም ለወይኑ፣ ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት፡፡
13ወይኑም፣ እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን አዲስ የወይን ጠጄን ትቼ ተመልሼ በዛፎች ላይ ለመወዛወዝ ልሂድን? አላቸው፡፡
14ከዚያም ዛፎች ሁሉ የእሾህ ቁጥቋጦን፣ ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት፡፡
15የእሾህ ቁጥቋጦውም ዛፎቹን፣ ‘በእውነት እኔን በእናንተ ላይ እንድነግስ ልትቀቡኝ የምትፈልጉ ከሆነ፣ ኑና በጥላዬ ስር ተጠለሉ፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን እሳት ከእሾህ ቁጥቋጦ ይውጣና የሊባኖስንም ዝግባ ያቃጥል’ አላቸው፡፡
16አሁን እንግዲህ፣ አቤሜሌክን ባነገሳችሁት ጊዜ በእውነትና በቅንነት አድርጋችሁ ከሆነ፣ ለይሩበኣልና ለቤቱም በጎነት አስባችሁ አድርጋችሁ ከሆነ፣ እንዳደረገውም መጠን ለእርሱ የተገባውን ቀጥታችሁት ከሆነ
17አባቴ ስለ እናንተ ተዋግቶ እንደነበር፣ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት፣ ከምድያምም እጅ እናንተን እንዳዳናችሁ አሰባችሁ ማለት ነው
18ነገር ግን ዛሬ እናንተ በአባቴ ቤት ላይ ተነሥታችኋል፣ በአንድ ድንጋይ ላይ ልጆቹን፣ ሰባ ሰዎችን፣ አረዳችኋቸው፡፡ ከዚያም የሴት አገልጋዩን ልጅ አቤሜሌክን ዘመዳችሁ ስለ ሆነ በሴኬም መሪዎች ላይ እንዲነግስ አደረጋችሁት፡፡
19ያንጊዜ ለይሩበኣልና ለቤቱ በእውነትና በቅንነትን አድርጋችሁ ከሆነ፣ እንግዲያው እናንተ በአቤሜሌክ ደስ ሊላችሁ ይገባል፣ እርሱም በእናንተ ደስ ይበለው፡፡
20ነገር ግን እንዲህ ባይሆን፣ ከአቤሜሌክ እሳት ይውጣና የሴኬምንም ሰዎችና የቤትሚሎን ቤት ያቃጥል፡፡ ከሴኬምም ሰዎችና ከቤትሚሎ እሳት ይውጣና አቤሜሌክን ያቃጥል፡፡
21ኢዮአታምም ሸሽቶ አመለጠ፣ ከዚያም ወደ ብኤር ሄደ፡፡ እርሱም በዚያ ተቀመጠ ምክንያቱም ከአቤሜሌክ ከወንድሙ በጣም ሩቅ ነበረ፡፡
22አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ለሦስት ዓመት ገዛ፡፡
23እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም መሪዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፡፡ የሴኬም መሪዎችም በአቤሜሌክ ላይ የነበራቸውን እምነት ጥለው ከዱት፡፡
24እግዚአብሔር ይህንን ያደረገው በሰባዎቹ የይሩበኣል ልጆች ላይ የተደረገውን ዓመፅ ለመበቀል ነው፣ ወንድማቸው አቤሜሌክም እነርሱን በመግደሉ ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ ነው፤ የሴኬም ሰዎችም እርሱ ወንድሞቹን እንዲገድላቸው ስለተባበሩት ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡
25ስለዚህ የሴኬም መሪዎች በኮረብቶች ራስ ላይ እርሱን አድፍጠው የሚጠብቁ ሰዎች መደቡ፣ እነርሱም በዚያ መንገድ በአጠገባቸው ያለፉትን ሰዎች በሙሉ ዘረፉ፡፡ ይህም ወሬ ለአቤሜሌክ ደረሰው፡፡
26የአቤድም ልጅ ገዓል ከዘመዶቹ ጋር መጣና ወደ ሴኬም ሄዱ፡፡ የሴኬም መሪዎች በእርሱ ተማመኑበት፡፡
27እነርሱም ወደ እርሻው ወጥተው ሄዱና ከወይን አትክልት ቦታ ወይን ለቅመው ጨመቁት፡፡ በአምላካቸው ቤት የደስታ በዓል አደረጉ፣ በሉም ጠጡም፣ አቤሜሌክንም ሰደቡ፡፡
28የአቤድም ልጅ ገዓል እንዲህ አለ፣ “እናገለግለው ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ማን ነው? እርሱ የይሩብኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የእርሱ ሹም አይደለምን? ለኤሞር ሰዎች፣ ለሴኬም አባት አገልግሉ! ለምን እርሱን እናገለግላለን?
29ይህ ሕዝብ በእኔ አዛዥነት ስር ቢሆን እመኝ ነበር! የዚያን ጊዜ አቤሜሌክን አስወግደው ነበር፡፡ ለአቤሜሌክም ‘ሠራዊትህን ሁሉ ጥራ’ እለው ነበር፡፡”
30የከተማይቱ ሹም፣ ዜቡል የአቤድን ልጅ የገዓልን ቃል በሰማ ጊዜ ቁጣው ነደደ፡፡
31ወደ አቤሜሌክም ያታልለው ዘንድ እንዲህ ብሎ መልክተኞች ላከ፣ “ተመልከት፣ የአቤድ ልጅ ገዓልና ዘመዶቹ ወደ ሴኬም እየመጡ ነው፣ ከተማይቱን በአንተ ላይ እንድትሸፍት አነሳስተዋል፡፡
32አሁንም አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ወታደሮች በሌሊት ተነሡ፣ ሜዳውም ላይ አድፍጡ፡፡
33ከዚያም በጠዋት ፀሐይ በወጣች ጊዜ ማልደህ ተነሣና በከተማይቱ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽምባት፡፡ እርሱና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ በአንተ ላይ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ላይ ልታደርግ የምትችለውን ማንኛውንም ነገር አድርግባቸው፡፡”
34ስለዚህ አቤሜሌክ በሌሊት ተነሳ፣ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በሙሉ፣ በአራት ወገን ተከፋፍለው በሴኬም ላይ አደፈጡ፡፡
35የአቤድ ልጅ ገዓል ወጥቶ በከተማይቱ በር መግቢያ ቆመ፡፡ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎችም ከተደበቁበት ስፍራ ወጥተው መጡ፡፡
36ገዓልም ሰዎቹን ባየ ጊዜ ዜቡልን፣ “ተመልከት፣ ሰዎች ከኮረብቶች ራስ ወርደው እየመጡ ነው!” አለው፡፡ ዜቡልም እንዲህ አለው፣ “አንተ የምታየው ሰዎች የሚመስለውን የኮረብቶች ጥላ ነው፡፡”
37ገዓልም እንደገና እንዲህ ሲል ተናገረ፣ “ተመልከት፣ በምድር መካከል ሰዎች ወርደው እየመጡ ነው፣ አንድም ወገን በቃላተኞች የበሉጥ ዛፍ መንገድ እየመጣ ነው፡፡
38የዚያን ጊዜ ዜቡል እንዲህ አለው፣ “‘እናገለግለው ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው?’ ብለህ የተናገርሃቸው እነዚያ የትዕቢት ቃላቶችህ አሁን የት አሉ? እነዚህ ሰዎች አንተ የናቅሃቸው አይደሉምን? አሁን ውጣና ከእነርሱ ጋር ተዋጋ፡፡”
39ገዓል ወጣና የሴኬም ሰዎችን ይመራ ነበር፣ ከአቤሜሌክም ጋር ተዋጋ፡፡
40አቤሜሌክም አሳደደው፣ ገዓልም በፊቱ ሸሸ፡፡ ብዙዎቹም በከተማይቱ በር መግቢያ ፊት ለፊት በከባድ ሁኔታ ቆስለው ወደቁ፡፡
41አቤሜሌክም በአሩማ ተቀመጠ፡፡ ዜቡልም ገዓልንና ዘመዶቹን ከሴኬም እንዲወጡ አስገደዳቸው፡፡
42በሚቀጥለው ቀን የሴኬም ሕዝብ ወደ እርሻ ሄዱ፣ ይህም ወሬ ለአቤሜሌክ ደረሰው፡፡
43ሕዝቡንም ወሰደ፣ በሦስት ወገንም ከፈላቸውና በእርሻዎቹ ውስጥ አደፈጡ፡፡ እርሱም ተመለከተ፣ ሕዝቡ ከከተማ ወጥተው ሲመጡ አየ፡፡ እርሱም ተዋጋቸውና ገደላቸው፡፡
44አቤሜሌክና ከእርሱም ጋር የነበሩት ወገኖች ተዋጉና የከተማይቱን በር መግቢያ ዘጉ፡፡ ሌሎቹ ሁለት ወገኖች ደግሞ በእርሻው ውስጥ የነበሩትን ሁሉ ወጓቸውና ገደሉአቸው፡፡
45አቤሜሌክም ቀኑን ሙሉ ከከተማይቱ ጋር ተዋጋ፡፡ ከተማይቱንም ተቆጣጠረና በውስጧ የነበሩትን ሕዝብ ገደላቸው፡፡ የከተማይቱንም ቅጥር አፈራረሰው፣ በላይዋም ጨው በተነባት፡፡
46የሴኬም ግንብ መሪዎች በሙሉ ይህንን ወሬ በሰሙ ጊዜ፣ ወደ ኤልብሪት ቤት ምሽግ ውስጥ ገቡ፡፡
47አቤሜሌክም መሪዎቹ በሙሉ በሴኬም ግንብ ውስጥ በአንድ ላይ እንደተሰበሰቡ ተነገረው፡፡
48አቤሜሌክ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጣ፣ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ፡፡አቤሜሌክም በእጁ መጥረቢያ ወሰደና የዛፉን ቅርንጫፎች ቆረጠ፡፡ እርሱም አንሥቶ በትከሻው ላይ አደረገውና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፣ “እኔ ሳደርግ ያያችሁትን፣ ፈጥናችሁ እኔ እንዳደረግሁ አድርጉ፡፡”
49ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው የዛፉን ቅርንጫፎች ቈረጠና አቤሜሌክን ተከተሉት፡፡ እነርሱም ቅርንጫፎቹን በምሽጉ ላይ ከመሩአቸው፣ በላዩም ላይ እሳት አቀጣጠሉበት፣ ከዚህ የተነሳ የሴኬም ግንብ ሰዎች ሁሉ፣ አንድ ሺህ የሚያህሉ ወንድና ሴት ሞቱ፡፡
50ከዚያ በኋላ አቤሜሌክ ወደ ቴቤስ ሄደ፣ ቴቤስንም ከበባትና ተቆጣጠራት፡፡
51ነገር ግን በከተማይቱ ጠንካራ ግንብ ነበረ፣ የከተማይቱም ሰዎች ሁሉ፣ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ የከተማይቱም መሪዎች ሁሉ ወደዚያ ሸሹና በውስጥ ሆነው ደጁን ዘጉት፡፡ ከዚያም እስከ ግንቡ ሰገነት ድረስ ወደ ላይ ወጡ፡፡
52አቤሜሌክም ወደ ግንቡ መጣና ተዋጋ፣ በእሳትም ሊያቃጥለው ወደ ግንቡ በር አጠገብ መጣ፡፡
53ነገር ግን አንዲት ሴት በአቤሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ ጣለችበት፣ መጁም ጭንቅላቱን ሰባበረው፡፡
54ከዚያም እርሱ በአስቸኳይ ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ፣ “አንድም ሰው እኔን ‘ሴት ገደለችው’ እንዳይል ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ” አለው፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ሰው ወጋውና ሞተ፡፡
55የእስራኤልም ሰዎች አቤሜሌክ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
56እግዚአብሔርም ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ላይ ያደረገውን ክፋት ተበቀለው፡፡
57እግዚአብሔርም የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰባቸው፣ የይሩበኣልም ልጅ የኢዮአታም እርግማን በእነርሱ ላይ መጣባቸው፡፡