መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መሳፍንት 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የኤፍሬም ሰዎች ለጌዴዎን እንዲህ አሉት፣ “ይህ በእኛ ላይ ያደረግኸው ምንድር ነው? ምድያምን ለመዋጋት በሄድህ ጊዜ እኛን አልጠራኸንም?” ከእርሱም ጋር በኃይል ተጣሉ።
2እርሱም እንዲህ አላቸው፣ “ከእናንተ ጋር ሲነጻጸር አሁን እኔ ያደረግት ምንድን ነው? ከኤፍሬም የወይን ቃርሚያ ይልቅ የአቢዔዝር ሙሉ የወይን መከር አይሻልምን?
3እግዚአብሔር በምድያም መሪዎች በሔሬብና በዜብ ላይ ድልን ሰጥቶአችኋል! ከእናንተ ጋር ሲነጻጸር እኑ ምን ፈጸምሁ?” ይህን በተናገረ ጊዜ ቍጣቸው በረደ።
4ጌዴዎን ከእርሱ ጋር ከነበሩት ከሦስቱ መቶ ሰዎች ጋር ወደ ዮርዳኖስ መጣና ተሻገረ፡፡ እጅግ በጣም ደክመው ነበር፣ ይሁን እንጂ ያሳድዱ ነበር።
5እርሱም ለሱኮት ሰዎች እንዲህ አላቸው፣ “ደክመዋልና እባካችሁ ለተከተሉኝ ሰዎች እንጀራ ስጡአቸው፣ እኔም የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን እያሳደድሁ ነው፡፡”
6የሱኮትም መሪዎች እንዲህ አሉ፣ “ዛብሄልንና ስልማናን በጉልበትህ አሸነፍኃቸውን?” እኛ ለሠራዊትህ እንጀራ ለምን እንደምንሰጥ አናውቅም?
7ጌዴዎንም እንዲህ አለ፣ “እግዚአብሔር በዛብሄልና በስልማና ላይ ድል በሰጠኝ ጊዜ፣ እኔ በምድረ በዳ እሾህና በኵርንችት ሥጋችሁን እቦጫጭቀዋለሁ፡፡”
8ከዚያም ወደ ጵኒኤል ወጣና በተመሳሳይ መንገድ በዚያ ለሚገኙ ሰዎች ተናገራቸው፣ ነገር ግን የጵንኤልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች እንደ መለሱ መለሱለት።
9እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች ደግሞ እንዲህ አላቸው፣ “በሰላም በተመለስሁ ጊዜ፣ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ፡፡
10ዛብሄልና ስልማናም ከሠራዊቶቻቸው ጋር፣ ከምሥራቅም ሰዎች ሠራዊት ሁሉ የቀሩ 15, 000 ያህል ሰዎች በቀርቀር ነበሩ፡፡ በሰይፍ ለመዋጋት ስልጠና የወሰዱ መቶ ሀያ ሺህ ሰዎች ወድቀው ነበርና፡፡
11ጌዴዎንም ዘላኖች ባሉበት መንገድ በኖባህና በዮግብሃ አልፎ ወደ ጠላት ሰፈር ሄደ፡፡ እርሱም የጠላትን ሰራዊት አሸነፈ፣ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት አደጋ ይገጥመናል ብለው አላሰቡም ነበርና፡፡
12ዛብሄልና ስልማናም ሸሹ፣ ጌዴዎንም ባሳደዳቸው ጊዜ ሁለቱንም የምድያም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ያዛቸው፣ ሠራዊታቸውንም ሁሉ ድንጋጤ ላይ ጣላቸው፡፡
13የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎንም በሔሬስ ዳገት በኩል በማለፍ ከጦርነት ተመለሰ፡፡
14እርሱም ከሱኮት ሰዎች አንድ ወጣት ይዞ ጠየቀውና ከእርሱ ምክር ፈለገ፡፡ ወጣቱም የሱኮትን መሪዎችና ሽማግሌዎች ሰባ ሰባት ሰዎች እነማን እንደሆኑ ገለጸለት።
15ጌዴዎንም ወደ ሱኮት ሰዎች መጣና እንዲህ አላቸው፣ “‘ዛብሄልንና ስልማናን በጉልበትህ አሸነፍኃቸውን? እኛ ለሠራዊትህ እንጀራ መስጠት እንዳለብን አናውቅም?’ ብላችሁ ያላገጣችሁብኝ ዛብሄልና ስልማና ተመልከቱአቸው፡፡”
16ጌዴዎንም የከተማይቱን ሽማግሌዎች ያዛቸው፣ የሱኮትንም ሰዎች በምድረ በዳ እሾህና በኵርንችት ገረፋቸው፡፡
17የጵኒኤልንም ግንብ አፈረሰ፣ የዚያችን ከተማ ሰዎችን ገደለ፡፡
18ጌዴዎንም ለዛብሄልና ለስልማና እንዲህ አላቸው፣ “በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች ምን ዓይነት ሰዎች ነበሩ?” እነርሱም፣ “እንደ አንተ ያሉ ነበሩ፡፡ እያንዳንዳቸው የንጉሥ ልጅ ይመስላሉ” አሉት፡፡
19ጌዴዎንም “እነርሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፡፡ በሕይወት እንዲኖሩ አድናችኋቸው ቢሆን ኖሮ፣ ሕያው እግዚአብሔርን፣ እኔ አልገድላችሁም ነበር” አለ፡፡
20ለበኵር ልጁ ለዬቴር እንዲህ አለው፣ “ተነሳና ግደላቸው!” ነገር ግን ወጣቱ ልጅ ስለፈራ ሰይፉን አልመዘዘም፣ ምክንያቱም ገና ወጣት ልጅ ነበረና፡፡
21የዚያን ጊዜ ዛብሄልና ስልማና እንዲህ አሉ፣ “አንተ ተነሳና ግደለን! የሰው ኃይሉ እንደ ሰውነቱ ነውና፡፡” ጌዴዎንም ተነሥቶ ዛብሄልንና ስልማናን ገደላቸው፡፡ በግመሎቻቸውም አንገት ላይ የነበሩትን ጌጦች ወሰደ፡፡
22የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን “አንተ ግዛን፣ አንተ፣ የአንተ ልጅና የልጅ ልጆችህ ግዙን፣ ምክንያቱም አንተ ከምድያም ብርታት አድነኸናልና፡፡”
23ጌዴዎንም ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፣ “እኔ በእናንተ ላይ አልገዛም፣ ልጄም በእናንተ ላይ አይገዛም፣ እግዚአብሔር ይገዛችኋል አላቸው፡፡
24ጌዴዎን ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፣ “አንድ የምጠይቃችሁ ነገር አለኝ፡- እያንዳንዳችሁ ከምርኮአችሁ ጕትቻችሁን እንድትሰጡኝ እለምናችኋለሁ፡፡” (ምድያማውያን የወርቅ ጕትቻ ነበራቸው ምክንያቱም እነርሱ እስማኤላውያንም ነበሩና፡፡)
25እነርሱም፣ “ለአንተ ልንሰጥህ ደስተኞች ነን” አሉት፡፡ እነርሱም ልብስ አነጠፉና ሁሉም ሰው የምርኮውን ጕትቻ በዚያ ላይ ጣለ፡፡
26እርሱ የጠየቀው የወርቅ ጕትቻ ክብደት 1, 700 ሰቅል ወርቅ ነበር፡፡ ይህም ምርኮ ከጌጣ ጌጦቹ ሌላ የአንገት ጌጥ፣ የምድያምም ነገሥታት ከሚለብሱት ሐምራዊ ልብስ፣ እንደዚሁም በግመሎቻቸውም አንገት ከነበሩት ጌጦች ሌላ ነበረ፡፡
27ጌዴዎንም ከጉትቻዎቹ ባገኘው ወርቅ ኤፉድ ሠራና በከተማው፣ በዖፍራ አኖረው፣ እስራኤልም ሁሉ እርሱን በማምለክ አመነዘረበት፡፡ ለጌዴዎንና በቤቱም ላሉት ወጥመድ ሆነባቸው፡፡
28ስለዚህም ምድያም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ተዋረደ፣ ራሳቸውንም እንደገና አላነሡም፡፡ በጌዴዎንም ዘመን ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም ሆነች።
29የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄደና በራሱ ቤት ተቀመጠ።
30ጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ሰባ ወንዶች ልጆች ነበሩት፡፡
31በሴኬም የነበረችው ቁባቱም ወንድ ልጅ ወለደችለት፣ ጌዴዎንም ስሙን አቤሜሌክ ብሎ ጠራው፡፡
32የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን በመልካም የሽምግልና ዕድሜ ሞተ፣ በአቢዔዝራውያን ጎሳ በሆነው በዖፍራ በነበረው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ፡፡
33ጌዴዎን ከሞተ በኋላ ብዙ ሳይቆይ እንዲህ ሆነ፣ የእስራኤል ሕዝብ እንደገና ተመለሱ፣ የበኣልን አማልክት በማምለክ አመነዘሩ፡፡ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ፡፡
34የእስራኤልም ሕዝብ በተለያዩ አቅጣጫዎች ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ኃይል ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፡፡
35እነርሱም ለእስራኤል ስላደረገው በጎ ነገር አስበው ለይሩበኣል (የጌዴዎን ሌላኛው ስም ነው) ውለታ ለመመለስ ቃል ኪዳናቸውን አልጠበቁም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።