1ከአቤሜሌክ በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነውና በኮረብታማውም በኤፍሬም አገር ባለችው በሳምር ይኖር የነበረው የዱዲ ልጅ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፡፡
2እርሱም በእስራኤል ላይ ሀያ ሦስት ዓመት ፈረደ፡፡ እርሱም ሞተ፣ በሳምርም ተቀበረ፡፡
3ከእርሱም በኋላ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፡፡ በእስራኤልም ላይ ሀያ ሁለት ዓመት ፈረደ፡፡
4በሠላሳ አህያዎች የሚጋልቡ ሠላሳ ልጆች ነበሩት፣ እነርሱም በገለዓድ ምድር ያሉ እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች ተብለው የሚጠሩ ሠላሳ ከተሞች ነበሩአቸው፡፡
5ኢያዕርም ሞተ፣ በቃሞንም ተቀበረ፡፡
6የእስራኤል ሕዝብ ከዚህ በፊት ከሰሩት በላይ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስራ ጨምረው ሠሩ፣ በኣልን፣ አስታሮትን፣ እንደዚሁም የሶርያን አማልክት፣ የሲዶናን አማልክት፣ የሞዓብን አማልክት፣ የአሞንን ሕዝብ አማልክት፣ የፍልስጥኤማውያንን አማልክት አመለኩ፡፡እግዚአብሔርን ተዉ፣ እርሱንም አላመለኩትም፡፡
7የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፣ እርሱም ፍልስጥኤማውያንና አሞናውያን ያሸንፉአቸው ዘንድ ለእነርሱ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡
8እነርሱም በዚያን ዓመት የእስራኤልን ሕዝብ አደቀቋቸው፣ አስጨነቋቸው፣ ለአሥራ ስምንት ዓመት በዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን ምድር በገለዓድ ውስጥ የነበሩትን የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ አስጨነቋቸው፡፡
9የአሞንም ሰዎች ከይሁዳ፣ ከብንያምና ከኤፍሬም ቤት ጋር ለመዋጋት ዮርዳኖስን ተሻገሩ፣ ከዚህ የተነሳ እስራኤል እጅግ በጣም ተጨነቁ፡፡
10የዚያን ጊዜ የእስራኤልም ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ጮሁ፣ እንዲህ በማለት፣ “በአንተ ላይ በድለናል፣ ምክንያቱም አምላካችንን ትተን የበኣል አማልክትን አምልከናልና፡፡”
11እግዚአብሔርም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ አላቸው፣ “ከግብፃውያን፣ ከአሞራውያንም፣ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጤማውያንና
12ከሲዶናውያን አላዳንኋችሁምን? አማሌቃውያንና ማዖናውያን አስጨነቋችሁ፤ ወደ እኔም ጮኻችሁ፣ እኔም ከእነርሱ ኃይል አዳንኋችሁ፡፡
13ይሁን እንጂ እናንተ እንደገና ተዋችሁኝና ሌሎችን አማልክት አመለካችሁ፡፡ ስለዚህ፣ እኔም ከእንግዲህ ወዲህ አላድናችሁም፡፡
14ሂዱና ወደምታመልኳቸው አማልክት ጩኹ፡፡ በመከራችሁ ጊዜ እነርሱ ያድኑአችሁ፡፡
15የእስራኤልም ሕዝብ እግዚአብሔርን እንዲህ አሉት፣ “እኛ ኃጢአትን ሠርተናል፡፡ ለአንተ ደስ የሚያሰኝህን ማንኛውንም ነገር በእኛ ላይ አድርግብን፡፡ እባክህ፣ የዛሬን ብቻ አድነን፡፡”
16እነርሱም በመካከላቸው ካሉት ባዕዳን አማልክት ዘወር አሉ፣ እግዚአብሔርንም አመለኩ፡፡እርሱም የእስራኤልን ጕስቍልና ሊታገሰው የማይቻለው ሆነ፡፡
17ከዚያም አሞናውያን በአንድ ላይ ተሰበሰቡና በገለዓድ ሰፈሩ፡፡ እስራኤላውያንም በአንድ ላይ ተሰበሰቡና ሰፈራቸውን በምጽጳ ላይ አደረጉ፡፡
18የገለዓድ ሕዝብ መሪዎችም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፣ “አሞናውያንን ለመዋጋት የሚጀምር ሰው ማን ነው? እርሱ በገለዓድ በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ መሪ ይሆናል፡፡”