1ከዚያም ጌዴዎን የተባለው ይሩበኣልና ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ በጠዋት ተነሡ፣ በሐሮድ ምንጭ አጠገብም ሰፈሩ፡፡ የምድያምም ሰፈር ከእነርሱ ወደ ሰሜን በኩል በሞሬ ኮረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ፡፡
2እግዚአብሔርም ጌዴዎንን እንዲህ አለው፣ “ምድያማውያንን እንድታሸንፍ የሚያደርጉህ እጅግ በጣም ብዙ ወታደሮች አሉኝ፡፡ ‘የራሳችን ኃይል አዳነን’ ብለው እስራኤል እንዳይታበዩብኝ እርግጠኛ ሁን፡፡
3ስለዚህም አሁን፣ በሕዝቡ ጆሮዎች እንዲህ ብለህ ተናገር፣ “ማንም የፈራ ቢኖር፣ ማንም የደነገጠ ቢኖር፣ የገለዓድን ተራራ ትቶ ይመለስ፡፡” ስለዚህ 22, 000 ሰዎች ተመለሱ፣ 10, 000 ሰዎችም ቀሩ፡፡
4እግዚአብሔርም ጌዴዎንን እንዲህ አለው፣ “ሕዝቡ አሁንም ገና ብዙ ነው፡፡ ሕዝቡን ወደ ውኃ ውሰዳቸው፣ በዚያም ቁጥራቸውን ጥቂት አደርግልሃለሁ፡፡ እኔ ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሄዳል’ ካልሁህ እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ነገር ግን እኔ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሄድም’ ካልሁህ እርሱ ከአንተ ጋር አይሄድም፡፡”
5ስለዚህ ጌዴዎን ሕዝቡን ወደ ውኃ ወሰዳቸው፣ እግዚአብሔርም ጌዴዎንን እንዲህ አለው፣ “ውሻ እንደሚጠጣ ውኃ የሚጠጣውን ሁሉ፣ ውኃ ለመጠጣት በጕልበታቸው ከሚንበረከኩት ሰዎች መካከል ለይ፡፡”
6ሦስት መቶ ሰዎች ውኃ እንደ ውሻ ጠጡ፡፡ የቀሩት ሰዎች ግን ውኃ ለጠጡ በጉልበታቸው ተንበረከኩ፡፡
7እግዚአብሔርም ጌዴዎንን እንዲህ አለው፣ “ውኃን እንደ ውሻ በጠጡት በሦስት መቶ ሰዎች ከምድያማውያን አድንሃለሁ፣ በእነርሱም ላይ ድል እሰጥሃለሁ፡፡ ሌሎቹ ሰዎች በሙሉ ወደ ስፍራቸው ይመለሱ፡፡”
8ስለዚህ የተመረጡት ሰዎች ስንቃቸውንና ቀንደ መለከታቸውን ወሰዱ፡፡ ጌዴዎን የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ፣ እያንዳንዱን ሰው ወደ ድንኳናቸው ሰደዳቸው፣ ነገር ግን ሦስቱን መቶ ሰዎች በእርሱ ዘንድ አቆያቸው፡፡ የምድያምም ሰፈር ከእርሱ በታች በሸለቆው ውስጥ ነበረ፡፡
9በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ለእርሱ እንዲህ አለው፣ “ተነስ! ሰፈራቸውን ምታ፣ በእነርሱ ላይ እኔ ድል እሰጥሃለሁና፡፡
10ነገር ግን አንተ ወደ ለመውረድ ከፈራህ፣ ከአገልጋይህ ከፉራ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፣
11የሚናገሩትንም አድምጥ፣ ከዚያም በኋላ ሰፈሩን ለመውጋት ድፍረት ታገኛለህ፡፡” ስለዚህ ጌዴዎን ከአገልጋዩ ከፉራ ጋር በሰፈሩ ወደ ነበሩት ጠባቂዎች ወረዱ፡፡
12ብዛታቸውም እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና የምሥራቅም ሰዎች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፡፡ የግመሎቻቸውም ብዛት መቁጠር አይቻልም ነበር፤ ቁጥራቸው በባህር ዳርቻ ካለው አሸዋ ይልቅ የሚበልጥ ነበር፡፡
13ጌዴዎን በዚያ በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ሕልምን ለጓደኛው ሲነግረው ነበር፡፡ ሰውየውም እንዲህ አለ፣ “ተመልከት! ሕልም አለምሁ፣ አንዲት ክብ የገብስ ቂጣ ወደ ምድያም ሰፈር ተንከባልላ ስትወርድ አየሁ፡፡ ወደ ድንኳኑም ደረሰች፣ እስኪወድቅ ድረስም በጣም መታችው ከዚህ የተነሳ ወደቀ፣ ደግሞም ተገለበጠ፣ ስለዚህም ድንኳኑ ተጋደመ፡፡”
14ሌላኛውም ሰው እንዲህ አለ፣ “ይህ ነገር ከእስራኤል ሰው ከኢዮአስ ልጅ ከጌዴዎን ሰይፍ በቀር ሌላ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በምድያምና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ ድል ሰጥቶታል፡፡”
15ጌዴዎን የሕልሙን ዝርዝርና ትርጓሜውን በሰማ ጊዜ በጸሎት ተደፍቶ ሰገደ፡፡ እርሱም ወደ እስራኤል ሰፈር ሄደና እንዲህ አለ፣ “ተነሱ! እግዚአብሔር በምድያም ሠራዊት ላይ ድል ሰጥተአችኋል፡፡”
16እርሱም ሦስቱን መቶ ሰዎች በሦስት ቡድን ከፈላቸው፣ ለሁሉም ሰዎች ቀንደ መለከትና ባዶ ማሰሮ፣ በማሰሮውም ውስጥ ችቦ ሰጣቸው፡፡
17እርሱም እንዲህ አላቸው፣ “እኔን ተመልከቱ፣ የማደርገውንም አድርጉ፡፡ አስተውሉ! ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በመጣሁ ጊዜ፣ እኔ የማደርገውን እናንተም ታደርጋላችሁ፡፡
18እኔና ከእኔም ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከት ስንነፋ፣ እናንተ ደግሞ በሰፈሩ በሁሉም አቅጣጫ ቀንደ መለከታችሁን ንፉና “ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን” ብላችሁ ጩኹ፡፡
19ስለዚህ ጌዴዎንና ከእርሱ ጋር የነበሩት መቶ ሰዎች የመካከለኛው የጥበቃ ሰዓት በተጀመረ ጊዜ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፡፡ ምድያማውያን የጥበቃ ሰዎችን በሚቀይሩበት ጊዜ፣ ቀንደ መለከቶቹን ነፉ፣ በእጃቸውም የነበሩትንም ማሰሮች ሰባበሩ፡፡
20ሦስቱም ቡድኖች ቀንደ መለከቶቹን ነፉ፣ ማሰሮችንም ሰበሩ፡፡ በግራ እጃቸው ችቦችን ያዙ፣ በቀኝ እጃቸው ደግሞ ቀንደ መለከቶችን ይዘው ለመንፋት ተዘጋጁ፡፡ እነርሱም “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” ብለው ጮኹ፡፡
21ሁሉም ሰው በሰፈሩ ዙሪያ በየቦታው ቆመ፣ የምድያማውያን ሠራዊት ሁሉ ሮጡ፡፡ እነርሱም ጮኹና ሸሹ፡፡
22ሦስት መቶውንም ቀንደ መለከቶች በነፉ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የእያንዳንዱን ምድያማዊ ሰው ሰይፍ በጓደኛውና በራሳቸው ሰራዊት ሁሉ ላይ አዘጋጀ፡፡ ሠራዊቱም በጽሬራ በኩል እስከ ቤትሺጣ፣ በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልምሖላ ዳርቻ ድረስ ሸሸ፡፡
23የእስራኤል ሰዎች ከንፍታሌም፣ ከአሴርና ከምናሴም ሁሉ ተሰብስበው ምድያምን ከኋላ እየተከተሉ አሳደዱ፡፡
24ጌዴዎን መልክተኞችን በኤፍሬም ወዳለው ኮረብታማ አገር ሁሉ በመስደድ እንዲህ አለ፣ “ምድያምን ለመዋጋት ውረዱና እነርሱን ለማስቆም የዮርዳኖስን ወንዝ እስከ ቤትባራም ድረስ ተቆጣጠሩ፡፡” ስለዚህ የኤፍሬም ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ ተሰብስበው እስከ ቤትባራና ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ውኃውን ተቆጣጠሩ፡፡
25የምድያምን ሁለቱን መሪዎች ሔሬብንና ዜብን ያዙ፡፡ ሔሬብንም በሔሬብ ዓለት ገደሉት፣ ዜብንም በዜብ ወይን መጥመቂያ ላይ ገደሉት፡፡ ምድያማውያንንም አሳደዱ፣ የሔሬብንና የዜብንም ራስ ይዘው በዮርዳኖስ ማዶ ወደነበረው ወደ ጌዴዎን አመጡ፡፡