1የእስራኤልም ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ሥራ ሠሩ፤ እርሱም በምድያም ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ ለሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡
2የምድያምም ኃይል በእስራኤል ላይ በረታ፡፡ ከምድያምም የተነሣ የእስራኤል ሕዝብ በኮረብታዎች ላይ ጕድጓድ፣ ዋሻና ምሽግም ለራሳቸው መሸሸጊያ አበጁ።
3እንዲህም ሆነ፣ እስራኤል ዘር በዘሩ ጊዜ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ከምሥራቅም የመጡ ሰዎች እስራኤላውያንን ያጠቁ ነበር፡፡
4ሰራዊታቸውን በምድሪቱ ላይ ያሰፍሩና እስከ ጋዛ ድረስ ያለውን ሰብል ያጠፉ ነበር፡፡ በእስራኤልም ምንም መብል፣ በጎች፣ ከብቶችና አህያዎች አይተዉም ነበር፡፡
5እነርሱ እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው ሲመጡ እንደ አንበጣ መንጋ ሆነው ይመጡ ነበር፤ እነርሱንና ግመሎቻቸውንም መቁጠር አይቻልም ነበር፡፡ ምድሪቱንም ያጠፉ ዘንድ ይወርሩአት ነበር፡፡
6ምድያም እስራኤልን ክፉኛ ከማዳከማቸው የተነሣ የእስራኤል ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡
7የእስራኤል ሕዝብ በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፣
8እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፡፡ ነቢዩም እንዲህ አለ፡- “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ‘እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ ከባርነትም ቤት አወጣኋችሁ፡፡
9ከግብፃውያንም እጅ እንደዚሁም ይጨቁኑአችሁ ከነበሩ ኃይላት ሁሉ አዳንኋችሁ፡፡ ከፊታችሁም አሳድጄ አወጣኋቸው፣ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ፡፡
10ለእናንተንም እንዲህ አልኋችሁ፣ “እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን፣ የአሞራያውያንን አማልክት እንዳታመልኩ አዘዝኋችሁ፡፡ ነገር ግን እናንተ ድምጼን አልታዘዛችሁም፡፡
11የእግዚአብሔርም መልአክ መጣና በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው ከበሉጥ ዛፍ በታች ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር፡፡
12የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጠለትና እንዲህ አለው፣ “አንተ ብርቱ ተዋጊ ሰው፣ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው!”
13ጌዴዎንም ለእርሱ እንዲህ አለው፣ “ጌታዬ ሆይ፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ይህ ነገር ሁሉ ለምን በእኛ ላይ ደረሰብን? አባቶቻችንስ የነገሩን እርሱ የሰራቸው አስደናቂ ነገሮች ወዴት አሉ፣ እንዲህ ብለው የነገሩን፣ ‘እግዚአብሔር ከግብፅ አላወጣንምን?’ አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፣ ለምድያማውያንም ብርታት አሳልፎ ሰጥቶናል፡፡
14እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ተመለከተና እንዲህ አለው፣ “በዚህ ባለህ ብርታት ሂድ፡፡ እስራኤልንም ከምድያም ኃይል አድን፤ እነሆ እኔ አልላክሁህምን?”
15ጌዴዎንም እንዲህ አለው፣ “ጌታ ሆይ፣ እባክህ፣ እኔ እስራኤልን እንዴት ማዳን እችላለሁ? ተመልከት፣ የእኔ ቤተሰብ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ ደካማ ነው፣ እኔም በአባቴ ቤት ውስጥ የመጨረሻ ነኝ፡፡
16እግዚአብሔርም፣ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፣ አንተም የምድያምን ሰራዊት በሙሉ ታሸንፋለህ” አለው፡፡
17ጌዴዎንም እንዲህ አለው፣ “በእኔ ደስተኛ ከሆንህ፣ የምትናገረኝ አንተ እንደሆንህ እርግጠኛ እሆን ዘንድ ምልከትን ስጠኝ፡፡
18ወደ አንተ እስክመጣና መስዋእቴን አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ ከዚህ አትሂድ፡፡” እግዚአብሔርም “እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ” አለ፡፡
19ጌዴዎን ሄደ የፍየሉንም ጠቦት አረደ፣ የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት ወስዶ ያልቦካ ቂጣ አዘጋጀ፡፡ ሥጋውን በቅርጫት አኖረ፣ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አኖረ፣ ሁሉንም ይዞ በበሉጥ ዛፍ በታች አቀረበለት፡፡
20የእግዚአብሔርም መልአክ እንዲህ አለው፣ “ሥጋውንና ያልቦካውን ቂጣ ውሰድና በዚህ ድንጋይ ላይ አኑረው፣ መረቁንም በላዩ ላይ አፍስሰው፡፡” ጌዴዎንም እንዲሁ አደረገ፡፡
21የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ የያዘውን የበትሩን ጫፍ ወደዚያ ዘረጋ፡፡ በበትሩም ሥጋውንና ያልቦካውን ቂጣ ነካው፤ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥቶ ሥጋውንና ያልቦካውን ቂጣ በላ፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ ሄደ፣ ጌዴዎንም ሊያየው አልቻለም፡፡
22ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አወቀ፡፡ ጌዴዎንም፣ “አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፣ ወዮልኝ! የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና” አለ፡፡
23እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፣ “ሰላም ለአንተ ይሁን! አትፍራ፣ አትሞትም፡፡”
24ስለዚህ ጌዴዎን በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፡፡ ስሙንም፣ እግዚአብሔር ሰላም ብሎ ጠራው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በአቢዔዝራውያን ጎሳ በምትሆነው በዖፍራ አለ፡፡
25እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት እንዲህ አለው፣ “የአባትህን በሬ፣ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውንም በሬ ውሰድ፣ የአባትህ የሆነውን የበኣል መሠዊያ አፍርስና በአጠገቡ ያለውን አሼራን ሰባብረው፡፡
26በዚህ መሸሸጊያ ስፍራ ጫፍ ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ፣ በትክክለኛው መንገድም ስራው፡፡ ከአሼራ ሰባብረህ በጣልኸው እንጨት ሁለተኛውን በሬ የሚቃጠል መስዋእት አድርገህ አቅርበው፡፡”
27ስለዚህ ጌዴዎን ከባሪያዎቹ አሥር ሰዎችን ወሰደና እግዚአብሔር እንደነገረው አደረገ፡፡ ነገር ግን በቀን ለማድረግ የአባቱን ቤተ ሰቦችና የከተማውንም ሰዎች እጅግ በጣም ስለፈራ፣ በሌሊት አደረገው፡፡
28በማለዳ የከተማው ሰዎች በተነሱ ጊዜ፣ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ ነበር፣ በአጠገቡ የነበረውም አሼራ ተሰባብሮ ነበር፣ ሁለተኛውም በሬ አዲስ በተሰራው መሠዊያ ላይ ተሠውቶ ነበር፡፡
29የከተማውም ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ተባባሉ፡፡ ከሌሎች ጋር ሲነጋገሩና መልስ ሲፈልጉ ሳሉ፣ “ይህን ያደረገው የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ነው” አሉ፡፡
30የዚያን ጊዜ የከተማው ሰዎች ኢዮአስን እንዲህ አሉት፣ “የበኣልን መሠዊያ አፍርሶአልና፣ በአጠገቡ የነበረውንም አሼራ ሰባብሮታልና እንዲሞት ልጅህን አውጣ፡፡”
31ኢዮአስም ለተቃወሙት በሙሉ እንዲህ አላቸው፣ “ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? እርሱን ታድኑታላችሁን? ለእርሱ የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ጠዋት ይገደል፡፡ በኣል አምላክ ከሆነ፣ መሠዊያውን ሲያፈርሱበት ራሱን ይከላከል፡፡
32ስለዚህም በዚያ ቀን ጌዴዎን “ይሩበኣል” የሚል ስም ተሰጠው፣ ምክንያቱም እርሱ “በኣል ራሱን ይከላከል” ብሏልና፣ ጌዴዎን መሠዊያውን አፍርሶአልና፡፡
33ምድያማውያንና አማሌቃውያን ሁሉ፣ የምሥራቅም ሰዎች አንድ ላይ ተሰበሰቡ፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግረው በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ ሰፈሩ፡፡
34ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ጌዴዎንን ሊረዳው በእርሱ ላይ ወረደ፡፡ ጌዴዎንም ቀንደ መለከት ነፋ፣ የአቢዔዝር ጎሳ ሰዎች ይከተሉት ዘንድ ጠራቸው፡፡
35እርሱም ወደ ምናሴ ነገድ ሁሉ መልክተኞችን ሰደደ፣ እነርሱም ደግሞ እንዲከተሉት ተጠርተው ነበር፡፡ መልክተኞችንም ወደ አሴር፣ ዛብሎንና ንፍታሌምም ላከ፣ እነርሱም እርሱን ሊየገኙት ሄዱ፡፡
36ጌዴዎንም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፣ “እንደ ተናገርኸው እስራኤልን ለማዳን እኔን የምትጠቀምብኝ ከሆነ
37ተመልከት፣ በአውድማው ላይ የበግ ጠጕር ባዘቶ አኖራለሁ፡፡ በጠጕሩ ብቻ ላይ ጠል ቢሆንና በምድሩም ሁሉ ደረቅ ቢሆን፣ የዚያን ጊዜ እንደተናገርኸው አንተ እስራኤልን ለማዳን እንደምትጠቀምብኝ አውቃለሁ፡፡”
38እንዲሁም ሆነ፣ ጌዴዎን በነጋው ማልዶ ተነሣ፣ ጠጕሩንም በአንድ ላይ ጨመቀው፣ ከጠጕሩም የተጨመቀው ጠል አንድ ቆሬ ለመሙላት በቂ ሆነ፡፡
39ጌዴዎንም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፣ “አትቈጣኝ፣ አንድ ጊዜ እንደገና እናገራለሁ፡፡ እባክህ፣ የጠጉሩ ባዘቶ በመጠቀም አንድ ተጨማሪ ሙከራ እንዳደርግ ፍቀድልኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ጠጕሩ ብቻ ደረቅ ይሁን፣ በምድሩና በዙርያውም ሁሉ ላይ ደግሞ ጠል ይሁን፡፡”
40እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት የጠየቀውን አደረገ፡፡ ጠጕሩ ደረቅ ነበረ፣ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ነበረ፡፡