1በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ ይህንን መዝሙር ዘመሩ፡-
2“በእስራኤል ውስጥ መሪዎች የመሪነት ስፍራውን ሲይዙ፣ ሕዝቡም በደስታና በፈቃዳቸው ለጦርነት ሲወጡ፣ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን!
3ስሙ፣ እናንተ ነገሥታት! አድምጡ፣ እናንተም መኳንንት! እኔ፣ እኔ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ምስጋናን እዘምራለሁ፡፡
4እግዚአብሔር ሆይ፣ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፣ ከኤዶምያስም በተነሳህ ጊዜ፣ ምድር ተናወጠች፣ ሰማያት ደግሞ ተንቀጠቀጡ፤ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠባጠቡ፡፡
5ተራሮች በእግዚአብሔር ፊት ተንቀጠቀጡ፤ ሲና ተራራም እንኳ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ተንቀጠቀጠ፡፡
6በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፣ በኢያዔል ዘመን፣ መንገዶች ተተዉ፣ መንገደኞችም በጠመዝማዛ መንገድ ብቻ ይጠቀሙ ነበር፡፡
7እኔ ዲቦራ አለቃ እስከሆንሁበት ጊዜ ድረስ፣ ለእስራኤል እናት ሆኜ አለቅነትን እስከወሰድሁበት ጊዜ ድረስ፣ በእስራኤል ውስጥ ገበሬዎች አልነበሩም፡፡
8አዲስ አማልክትን መረጡ፣ በከተማዋ ደጆች ጦርነት ነበረ፤ በእስራኤል ውስጥ በአርባ ሺህ መካከል ጋሻ ወይም ጦር አልታየም፡፡
9ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ሄደ፣ በሕዝቡ መካከል ራሳቸውን በደስታ ስለ ሰጡትም እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
10እናንተ በነጫጭ አህዮች ላይ ትንሽ የምንጣፍ ኮርቻ ላይ ተቀምጣችሁ የምትጓዙ፣ በመንገድም የምትሄዱ እናንተ ስለዚህ ነገር አስቡ፡፡
11በማጠጫው ስፍራ መካከል ሆነው በጎችን የሚከፋፍሉትን ሰዎች ድምጽ ስሙ፡፡ የእግዚአብሔርን የጽድቅ ድርጊትና ተዋጊዎቹ በእስራኤል ውስጥ የሰሩትን የጽድቅ ተግባር በዚያ እንደገና እየተናገሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ ከተማው በሮች ወረዱ፡፡
12ንቂ፣ ንቂ፣ ዲቦራ ሆይ! ንቂ፣ ንቂ፣ መዝሙርን ዘምሪ! ባርቅ ሆይ፣ ተነሣ፣ የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፣ ምርኮኞችህን ማርከህ ውሰድ፡፡
13የዚያን ጊዜ የተረፉት ወደ ኃያላኑ መጡ፣ ከተዋጊዎቹም መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ እኔ መጡ፡፡
14መሰረታቸው ከአማሌቅ ወገን የሆኑ ከኤፍሬም መጡ፤ የብንያም ሕዝብም ተከተሉህ፡፡ ከማኪርም አዛዦች ወረዱ፣ የስልጣን በትር የያዙ ከዛብሎን ወረዱ፡፡
15የይሳኮርም መሳፍንት ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤ ይሳኮርም ከባርቅ ጋር በትዕዛዙ መሰረት ከኋላው እየተከተለ ወደ ሸለቆው ሄደ፡፡ በሮቤል ጎሳ መካከል ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ፡፡
16የበጎች እረኞች ለመንጎቻቸው በፉጨት ሲጫወቱ እያዳመጥህ በእሳት ማንደጃ መካከል ለምን ተቀመጥህ? በሮቤል ጎሳ መካከል ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ፡፡
17ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤ ዳን ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ? አሴርም በባሕሩ ዳርቻ ቀረ፣ በወንዞቹም ዳርቻ ኖረ፡፡
18ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት አሳልፎ የሚሰጥ ሕዝብ ነው፣ ንፍታሌምም በውጊያ ሜዳ ላይ ነው፡፡
19ነገሥታት መጡ ተዋጉም፣ የዚያን ጊዜ የከነዓን ነገስታትም በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ ተዋጉ፡፡ ምንም የብር ምርኮ አልወሰዱም፡፡
20ከሰማይ ከዋክብት ተዋጉ፣ በሰማያት ላይ በአካሄዳቸውም ሲሣራን ተዋጉት፡፡
21ከዱሮ ጀምሮ የታወቀው፣ የቂሶን ወንዝም፣ ጠርጎ ወሰዳቸው፡፡ ነፍሴ ሆይ ገስግሺ፣ በርቺ!
22የፈረሶች የግልብያ ኮቴዎች ድምጽ፣ የኃያላኑ ግልቢያ ድምጽም፡፡
23የእግዚአብሔር መልአክ “ሜሮዝን እርገሙ!” ይላል፡፡ ‘ነዋሪዎቿን ፈጽማችሁ እርገሙ! ምክንያቱም እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡም፣ ከኃያላን ጦረኞች ጋር በተደረገው ውጊያ እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና፡፡'
24የቄናዊው የሔቤር ሚስት፣ ኢያዔል፣ ከሴቶች ሁሉ ይልቅ የተባረከች ናት፣ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ሁሉ ይልቅ የተባረከች ናት፡፡
25ሰውየው ውኃ ለመናት፣ እርስዋም ወተት ሰጠችው፤ ለመሳፍንት በሚሆን በተከበረ ሳህን ቅቤ አመጣችለት፡፡
26እጅዋን ወደ ድንኳን ካስማ፣ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፣ ራሱንም ቀጠቀጠች፡፡ ጆሮ ግንዱን በወጋችው ጊዜ ጭንቅላቱንም ፈረከሰችው፡፡
27በእግሮችዋ መካከል ተደፋ፣ ወደቀ ተኛም፡፡ በእግሮችዋ አጠገብ ተሰብሮ ወደቀ፡፡ የተደፋበት ስፍራ በክፉ ሁኔታ የሞተበት ነው፡፡
28ከመስኮት ሆና ወደ ውጭ ተመለከተች፣ የሲሣራ እናት በርብራብ በኩል በኃዘን ወደ ውጭ ጮኸች፣ ‘ወደዚህ ለመምጣት ሰረገላው ረዥም ጊዜ ለምን ወሰደበት? ለምንስ ሰረገላዎቹን የሚጎትቱት የፈረሶቹ ኮቴዎች ዘገየ?’
29ብልሃተኞች ልዕልቶቿም መለሱላት፣ ለራስዋም ተመሳሳይ መልስ መለሰች፡-
30ምርኮውን አግኝተው ተካፍለው የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ልጃገረድ፤ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ቀለም ያለው ልብስ፣ የተጠለፈ ባለቀለም ጨርቅ ምርኮ፣ ለማረኩ ሰዎች ለአንገታቸው የሚሆን በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ባለቀለም ጨርቆች ምርኮን አላገኙምን?’
31ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ! ነገር ግን እርሱን የሚወዱት በኃይል እንደሚወጣ ጸሐይ ይሁኑ፡፡” ምድሪቱም ለአርባ ዓመት ያህል ዐረፈች፡፡