መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መሳፍንት 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ናዖድም ከሞተ በኋላ፣ የእስራኤል ሕዝብ ክፉ ነገሮችን በመስራት እንደገና እግዚአብሔርን አልታዘዙም፣ እርሱም ምን እንዳደረጉ ተመለከተ፡፡
2እግዚአብሔርም በሐጾር ሆኖ ይገዛ በነበረው፣ በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ የሠራዊቱም አለቃ ሲሣራ ተብሎ ይጠራ ነበር፣ እርሱም የአሕዛብ በሆነችው በአሪሶት ኖረ፡፡
3የእስራኤልም ሕዝብ ለእርዳታ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፣ ምክንያቱም ሲሳራ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩት፣ እርሱም የእስራኤልን ሕዝብ ለሀያ ዓመት በኃይል አስጨንቆ ገዛቸው፡፡
4በዚያ ጊዜ ነቢይቱ የለፊዶት ሚስት ዲቦራ፣ በእስራኤል ላይ ዋነኛ ፈራጅ ነበረች፡፡
5እርስዋም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዘንባባ ዛፍ ስር ትቀመጥ ነበር፣ የእስራኤልም ሕዝብ ለክርክራቸው መፍትሔ ለማግኘት ወደ እርስዋ ይመጡ ነበር፡፡
6እርስዋም በንፍታሌም ውስጥ ካለው ከቃዴስ የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን ጠራች፡፡ እንዲህም አለችው፣ “የእስራኤል አምላክ፣ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይልሃል፣ ‘ወደ ታቦር ተራራ ሂድ፣ ከንፍታሌምና ከዛብሎን አሥር ሺህ ሰዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፡፡
7እኔ የኢያቢስን ሠራዊት አዛዥ ሲሣራን በቂሶን ወንዝ አቅራቢያ ከሰረገሎቹና ከሰራዊቱ ጋር እንዲያገኝህ አስወጣዋለሁ፣ እኔም በእርሱ ላይ ድልን እሰጥሃለሁ፡፡’”
8-9ባርቅም እንዲህ አላት፣ “አንቺ ከእኔ ጋር ከሄድሽ እኔም እሄዳለሁ፣ ነገር ግን አንቺ ከእኔ ጋር ካልሄድሽ እኔም አልሄድም፡፡” እርስዋም እንዲህ አለች፣ “በእውነት ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ፣ አንተ የምትሄድበት መንገድ ወደ ክብር አያደርስህም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሲሣራን በጥንካሬዋ ድል ታደርገው ዘንድ ለሴት አሳልፎ ይሰጣልና፡፡” ከዚያም ዲቦራ ተነሥታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች፡፡
10ባርቅም የዛብሎንና የንፍታሌም ሰዎች በአንድነት ወደ ቃዴስ እንዲመጡ ጠራቸው፡፡ አሥር ሺህም ሰዎች ተከተሉት፣ ዲቦራም ከእርሱ ጋር ሄደች፡፡
11ቄናዊው ሔቤርም ከቄናውያን ራሱን ለየ፣ እነርሱም የሙሴ አማት የኦባብ ልጆች ነበሩ፣ እርሱም በቃዴስ አጠገብ በጻዕናይም በነበረው በበሉጥ ዛፍ ጥግ ድንኳኑን ተከለ፡፡
12ለሲሳራም የአቢኔኤም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ እንደወጣ በነገሩት ጊዜ፣
13ሲሣራም ሰረገሎቹን ሁሉ፣ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች፣ ከእርሱም ጋር የነበሩትን ወታደሮቹን ሁሉ፣ የአሕዛብ ከሆነችው ከአሪሶት ወደ ቂሶን ወንዝ ሰበሰባቸው፡፡
14ዲቦራም ባርቅን እንዲህ አለችው፣ “ሂድ! ዛሬ እግዚአብሔር በሲሣራ ላይ ድል እንድታደርግ በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ነውና፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ከፊትህ አልወጣምን?” ስለዚህ ባርቅ ከታቦር ተራራ አብረውት ከነበሩት አስር ሺህ ሰዎች ጋር ወረደ፡፡
15እግዚአብሔርም የሲሣራን ሰራዊት ግራ አጋባ፣ ሰረገሎቹንም ሁሉ፣ ሠራዊቱንም ሁሉ፣ የባርቅም ሰዎች የሲሳራን ሰዎች አጠቋቸው፣ ሲሳራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ፡፡
16ባርቅ ግን ሰረገሎችንና ሠራዊቱን እስከ አሪሶት ድረስ አባረራቸው፣ የሲሣራም ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ተገደሉ፣ አንድ ሰው እንኳ አልቀረም፡፡
17ሲሳራ ግን በእግሩ ወደ ቄናዊው ሔቤር ሚስት፣ ወደ ኢያዔል ድንኳን ሸሸ፣ ምክንያቱም በሐሶር ንጉስ በኢያቢስና፣ በቄናዊው በሔቤር ቤት መካከል ሰላም ስለነበር ነው፡፡
18ኢያዔልም ሲሣራን ለመገናኘት ወጣች እንዲህም አለችው፣ “ግባ፣ ጌታዬ ሆይ፤ ወደ እኔ ግባ አትፍራም፡፡” እርሱም ወደ እርስዋ ወደ ድንኳንዋ ገባ፣ በብርድ ልብስም ሸፈነችው፡፡
19እርሱም እንዲህ አላት፣ “ጠምቶኛልና፣ እባክሽ የምጠጣው ጥቂት ውኃ ስጭኝ፡፡” እርስዋም ከቆዳ የተሰራ የወተቱን ማስቀመጫ ከፍታ የሚጠጣ ሰጠችው፣ ከዚያም እንደገና ሸፈነችው፡፡
20እርሱም አላት፣ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፡፡ ሰውም ቢመጣና ‘በዚህ ሰው አለን?’ ብሎ ቢጠይቅሽ ‘የለም’ በይ፡፡”
21ከዚያም የሔቤር ሚስት ኢያዔል የድንኳን ካስማ ወሰደች በእጅዋም መዶሻ ያዘች በቀስታ ወደ እርሱ ሄደች፣ እርሱም በከባድ እንቅልፍ ላይ ነበር፣ እርስዋም ካስማውን በጆሮ ግንዱ ላይ ሰካችው፣ ካስማውም ሰውነቱን ወግቶ አለፈና ወደ መሬት ጠለቀ፡፡ እርሱም ሞተ፡፡
22ባርቅም ሲሣራን ሲያባርር፣ ኢያዔል ልታገኘው ወጣችና እንዲህ አለችው፣ “ና፣ የምትፈልገውንም ሰው አሳይሃለሁ፡፡” እርሱም ወደ ውስጥ ከእርስዋ ጋር ገባ፣ እነሆም በዚያ ሲሣራ ሞቶ ተጋድሞ ነበር፣ ካስማውም በጆሮ ግንዱ ውስጥ ተሰክቶ አገኘው፡፡”
23ስለዚህ በዚያ ቀን እግዚአብሔር የከነዓንን ንገሥ ኢያቢስን በእስራኤል ሕዝብ ፊት አሸነፈው፡፡
24የእስራኤል ሕዝብ ጉልበት የከነዓን ንጉሥ ኢያቢስን እስከሚያጠፉ ድረስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መጣ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።