1እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ሳያስወጣ ያስቀራቸው እስራኤልን ይልቁንም ደግሞ በከነዓን በተደረጉት ጦርነቶች ያልተዋጉትን በእስራኤል የሚገኙትን እያንዳንዱ ሰው ይፈትን ዘንድ ነው፡፡
2(ይህንን ያደረገው ውጊያ የማያውቁትን አዲሱ የእስራኤል ትውልድ ውጊያን ለማስተማር ነው) ፡-
3አምስቱ የፍልስጤማውያን ነገስታት፣ ከነዓናውያንም ሁሉ፣ ሲዶናውያን እና ከበዓልኤርሞንየም ተራራ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራዎች ይኖሩ የነበሩትም ኤውያውያን ነበሩ፡፡
4እነዚህ ሕዝቦች ሳይወጡ እንዲቀሩ የተደረጉት እግዚአብሔር እስራኤልን መፈተኛ እንዲሆኑ ነው፣ እነርሱ ለአባቶቻቸው በሙሴ በኩል የሰጣቸውን ሕግ ይታዘዙና አይታዘዙ እንደሆነ ለማረጋገጥ ነው፡፡
5ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ በከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዛውያን ከኤውያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋር አብረው ኖሩ፡፡
6ሴት ልጆቻቸውንም ሚስት እንዲሆኗቸው ወሰዷቸው፣ የራሳቸውን ሴት ልጆችም ለወንድ ልጆቻቸው ሰጧቸው፣ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ፡፡
7የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ዓይን ጸያፍ የነበረውን ነገር ፈጸሙ፣ አምላካቸው እግዚአብሔርንም ረሱ፡፡ የኣልንና የአስታሮትን አማልክት አመለኩ፡፡
8ስለዚህም የእግዚአብሔር ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፣ ለመስጶጣምያ ንጉስ ለኩሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ የእስራኤል ሕዝብም ኩሰርሰቴን ለስምንት አመታት አገለገሉ፡፡
9የእስራኤል ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር በጮሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ለመርዳት የሚመጣና ካሉበት ሁኔታም የሚያድናቸው ሰው አስነሳ፡- ይህም ሰው የካሌብ ታናሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ነበር፡፡
10የእግዚአብሔር መንፈስም አበረታው፣ እስራኤላውያን ላይም ይፈርድ ነበር፣ ወደ ውጊያም ይወጣ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በመስጶጣምያ ንጉስ በኩሰርሰቴ ላይ ድልን ሰጠው፡፡ ኩሰርሰቴንም ያሸነፈው የጎቶንያል እጅ ነበር፡፡
11ምድሪም ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች፡፡ የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያልም ሞተ፡፡
12የእስራኤልም ሕዝብ ክፉ ነገሮችን በማድረግ ደግመው እግዚአብሔርን ሳይታዘዙ ቀሩ፣ እርሱም ምን እንዳደረጉ ተመለከተ፡፡ ስለዚህ እስራኤል ክፉ ነገሮችን ስላደረጉና፣ እግዚአብሔርም ስላያቸው የሞኣብ ንጉስ ኤግሎም እስራኤልን ለመውጋት በመጣ ጊዜ እግዚአብሔር ብርታትን ሰጠው፡፡
13ኤግሎምም ከአሞንና ከአማሌቃውያን ጋር ተባበረ፣ እነርሱም ሄዱ እስራኤልንም አሸነፉ፣ ከዚያም የዘንባባ ከተማን ተቆጣጠሩ፡፡
14የእስራኤልም ሕዝብ የሞኣብን ንጉስ ኤግሎምን ለአስራ ስምንት አመታት አገለገሉ፡፡
15ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር በጮሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የሚረዳቸውን ሰው አስነሳ፣ ይህም ግራኝ የነበረው ብንያማዊው የጌራን ልጅ ናኦድ ነው፡፡ የእስራኤልም ሕዝብ እርሱን ወደ ሞኣብ ንጉስ ወደ ኤግሎም የሚከፍሉትን ግብር አስይዘው ላኩት፡፡
16ናኦድ በሁለት በኩል የተሳለ ርዝመቱ አንድ ክንድ የሆነ ሰይፍን ሰራ፤ ከልብሱም በታች በቀኝ ጭኑ አሰረው፡፡
17ግብሩንም ለሞኣብ ንጉስ ለኤግሎም ሰጠው፡፡ (ኤግሎም በዚያን ጊዜ እጅግ ወፍራም ሰው ነበር፡፡)
18ናኦድም የግብሩን ክፍያ ካቀረበ በኋላ፣ ግብሩን ተሸክመው ገብተው ከነበሩ ሰዎች ጋር ወጣ፡፡
19ይሁን እንጂ ናኦድ በጌልጌላ አጠገብ የተቀረጹ ምስሎች ተሰርተውበት ወደነበረው ስፍራ ሲደርስ ተመልሶ ሄደና እንዲህ አለ፡- “ንጉስ ሆይ፣ ለአንተ የሚስጥር መልዕክት አለኝ፡፡” ኤግሎምም እንዲህ አለ፡- “ጸጥታ!” ስለዚህም አገልጋዮቹ ሁሉ ክፍሉን ትተው ወጡ፡፡
20ናኦድም ወደ እርሱ መጣ፡፡ ንጉሱም ቀዝቃዛ በሆነው ሰገነት ላይ ብቻውን ተቀምጦ ነበር፡፡ናኦድም እንዲህ አለ፣ “ለአንተ ከእግዚአብሔር የመጣ መልዕክት አለኝ፡፡” ንጉሱም ከመቀመጫው ተነሳ፡፡
21ናኦድም ግራ እጁን ዘረጋና ሰይፉን ከቀኝ ጭኑ አወጣ፣ ሰይፉንም በንጉሱ ሰውነት ውስጥ ሰካው፡፡
22የሰይፉም እጀታ ከስለቱ ጋር ወደ ሰውነቱ ገባ፣ ጫፉም በጀርባው ወጣ፣ ሞራም ስለቱን ሸፈነው፣ ናኦድም ሰይፉን ከንጉሱ ሰውነት አላወጣውም፡፡
23ከዚያም ናዖድ ወደ በረንዳው ወጣና የሰገነቱን በር በንጉሱ ላይ ዘግቶ ቈለፈው፡፡
24ናዖድም ከሄደ በኋላ፣ የንጉሱ ባሪያዎች መጡ፤ የሰገነቱም ደጅ ተቈልፎ አዩ፣ ስለዚህ እንዲህ ሲሉ አሰቡ፣ “ምናልባት በቀዝቃዛው ሰገነት ውስጥ እየተጸዳዳ ይሆናል፡፡”
25ንጉሱ የሰገነቱን በር ሳይከፍት በቆየም ጊዜ ስራቸውን ችላ እንዳሉ እስኪሰማቸው ድረስ ስጋት እያደረባቸው ጠበቁ፡፡ ስለዚህ ቁልፉን ወሰዱና በሮቹን ከፈቱ፣ እነሆም ጌታቸው ተጋድሞ፣ በወለሉም ላይ ወድቆ፣ ሞቶም አገኙት፡፡
26ባርያዎቹ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እያሰቡ ሲጠባበቁ፣ ናዖድ አመለጠ፣ የጣኦታት ምስል በተቀረጸበት ስፍራ በኩል አለፈ፣ ወደ ቤይሮታም አመለጠ፡፡
27በደረሰም ጊዜ፣ በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ቀንደ መለከት ነፋ፡፡ ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ ከእርሱ ጋር ከኮረብታማው አገር ወረዱ፣ እርሱም ይመራቸው ነበር፡፡
28እርሱም እንዲህ አላቸው፣ “ተከተሉኝ፣ እግዚአብሔር ጠላቶቻችሁን፣ ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና፡፡” እነርሱም ተከትለውት ወረዱና የዮርዳኖስን መሻገርያ ከሞዓባውያን ቀምተው ያዙ፣ እነርሱም ማንም ሰው ወንዙን እንዳይሻገር ከለከሉ፡፡
29በዚያን ጊዜም ከሞዓብ አሥር ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን ገደሉ፣ የተገደሉትም ሁሉ ጠንካራና ኃይለኛ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድም እንኳ አላመለጠም፡፡
30በዚያም ቀን ሞዓብ በእስራኤል ብርታት ድል ሆነች፡፡ ምድሪቱም ለሰማንያ ዓመት ዐረፈች፡፡
31ከናኦድ በኋላ የተነሳው መስፍን ስድስት መቶ የፍልስጥኤም ሰዎችን በበሬ መንጃ የገደለው የዓናት ልጅ ሰሜጋር ነበር፡፡ እርሱም ደግሞ እስራኤልን ከአደጋ አዳነ፡፡