1የእግዚአብሔር መልዓክም ከጌልጌላ ወደ ቦኪም ወጣ፣ እንዲህም አለ፣ “ከግብጽ አወጣኋችሁ፣ ለአባቶቻችሁ ወደማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፡፡ እንዲህም አልሁ፣ ‘ከእናንተ ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን አላፈርስም፡፡
2በዚህ ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አትግቡ፡፡ መሰዊያቸውን ማፍረስ አለባችሁ፡፡’ እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፡፡ ይህ ያደረጋችሁት ምንድን ነው?
3አሁንም እላለሁ፣ ‘ከነዓናውያንን ከእናንተ ፊት አላወጣም፣ ነገር ግን እነርሱ የጎን እሾህ ይሆኑባችኋል፣ ጣዖቶቻቸውም ለእናንተ ወጥመድ ይሆናሉ፡፡’”
4የእግዚአብሔር መልዓክም እነዚህን ቃሎች ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ጮሁ አለቀሱም፡፡
5ያንንም ቦታ ቦኪም ብለው ጠሩት፡፡ በዚያም ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረቡ፡፡
6ኢያሱም ሰዎችን ወደ መንገዳቸው በላካቸው ጊዜ፣ የእስራኤል ሕዝብ ምድሩን ለመውሰድና የራሳቸው ለማድረግ ለእንዳንዳቸው ወደተመደበላቸው ቦታ ሄዱ፡፡
7ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን፣ የእግዚአብሔርን ታላቅ ስራንና ለእስራኤል ምን እንዳደረገም ያዩ ከእርሱ በኋላም በኖሩ ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አገለገለ፡፡
8የእግዚአብሔር አገልጋይ፣ የነዌ ልጅ ኢያሱ፣ በመቶ አስር ዓመቱ ሞተ፡፡
9እነርሱም በኤፍሬም ኮረብታማው አገር በሰሜናዊው ገአስ ተራራ በምድሪቱ ድንበር በተዘጋጀለት ቦታ በተምናሔሬስ ቀበሩት፡፡
10ያ ሁሉ ትውልድም ወደ አባቶቻቸው ተሰበሰቡ፡፡ ከእነርሱም በኃላ እግዚአብሔርንና እርሱ ለእስራኤል ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሳ፡፡
11የእስራኤል ሕዝብም በእግዚአብሔር ዓይን ክፉ የሆነውን ነገር አደረጉ፣ የበኣል አማልክትንም አመለኩ፡፡
12ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፡፡ ሌሎች አማልክትን፣ በዙርያቸው የነበሩ ሕዝቦች አማልክትን ተከተሉ፣ ለእነርሱም ሰገዱ፡፡ እግዚአብሔርንም አስቆጡት ምከንያቱም
13እግዚአብሔርን ትተዋልና፣ በኣልንና አስታሮትንም አምልከዋልና፡፡
14የእግዚአብሔርም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፣ ንብረታቸውን ለሰረቋቸው ወራሪዎች አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ራሳቸውን ከጠላታቸው መከላከል እንዳይችሉ፣ በዙርያቸው በጠላቶቻቸው ብርታት ተይዘው እንደ ነበሩት ባርያዎች አሳልፎ ሸጣቸው፡፡
15እስራኤል ለውጊያ በምትሄዱበት ስፍራ ሁሉ፣ ለእነርሱ እንደማለላቸው ይሸነፉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በእነርሱ ላይ ይከፋ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ እነርሱም በጣም ተጨነቁ፡፡
16ያን ጊዜ ንብረታቸውን ከሚሰርቋቸው ሰዎች ኃይል ያድናቸው ዘንድ እግዚአብሔር መሳፍንትን አስነሳላቸው፡፡
17ይሁን እንጂ እነርሱ መሳፍንቶቻቸውን ሊሰሟቸው አልቻሉም፡፡ ለእግዚአብሔር አልታመኑም፣ ራሳቸውንም እንደ አመንዝራዎች ለሌሎች አማልክት ሰጡ፣ አመለኳቸውም፡፡ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይከተሉ ከነበሩት ከአባቶቻቸው መንገድ ወዲያውኑ ዘወር አሉ፣ እነርሱ ራሳቸው እንደ አባቶቻቸው አላደረጉም፡፡
18እግዚአብሔር ለእነርሱ መሳፍንትን ባስነሳላቸው ጊዜ፣ መሳፍንቱ በኖሩበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔር መሳፍንቱን ረዳቸው፣ ከጠላቶቻቸውም ጉልበት ሁሉ አዳናቸው፡፡ በጨቆኗቸውና መከራ ባሳዩአቸው ሰዎች ምክንያት ወደ እርሱ በጮኹ ጊዜ እግዚአብሔር ለእነርሱ አዘነላቸው፡፡
19ነገር ግን መስፍኑ በሞተ ጊዜ፣ ተመልሰው አባቶቻው ያደርጉ ከነበረውም እጅግ የከፋ ነገር አደረጉ፡፡ ሌሎች አማልክትን በመከተል እነርሱን ያገለግሉና ያመልኩ ነበር፡፡ ክፉ ድርጊታቸውንና እልኸኛ መንገዳቸውንም ለመተው ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡
20የእግዚአብሔርም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፣ እንዲህም አለ፣ “ይህ ሕዝብ ለአባቶቻቸው የገባሁትን ቃል ኪዳኔን ስላፈረሱ፣ ድምጼንም ስላልሰሙ
21ከአሁን በኋላ ኢያሱ ሲሞት ሳያወጣቸው የተዋቸውን አሕዛብ ከፊታቸው አላወጣቸውም፡፡
22ይህን የማደርገው እስራኤል አባቶቻቸው እንዳደረጉት የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁና በዚያም ይሄዱ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እፈትናቸው ዘንድ ነው፡፡”
23እግዚአብሔርም እነዚያን አሕዛብ የተዋቸው፣ በፍጥነትም ያላስወጣቸው፣ ኢያሱም እንዲያሸንፋቸው ያልፈቀደለት ለዚህ ነው፡፡