መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መሳፍንት 20

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የዚያን ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወጡ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፣ የገለዓድ አገር ሰዎችንም ጨምሮ፣ በእግዚአብሔር ፊት በምጽጳ ተሰበሰቡ፡፡
2የሕዝቡም ሁሉ መሪዎች፣ የእስራኤል ነገዶች ሁሉ፣ እግረኞች ሆነው በሰይፍ የሚዋጉ 400, 000 ሰዎች በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ውስጥ ስፍራቸውን ያዙ፡፡
3በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ እስከ ምጽጳ ድረስ እንደ ሄዱ የብንያም ሕዝብ ሰሙ፡፡ የእስራኤልም ሕዝብ እንዲህ አሉ፣ “ይህ ክፉ ነገር እንዴት እንደ ተደረገ ንገሩን?”
4ሌዋዊውም፣ የተገደለችው ሴት ባል፣ እንዲህ ብሎ መለሰ፣ “እኔና ቁባቴ ሌሊቱን በዚያ ለማሳለፍ የብንያም ግዛት ወደሆነችው ወደ ጊብዓ መጣን፡፡
5በዚያ ሌሊት የጊብዓ ሰዎች በእኔ ላይ ተነሱ፣ ሊገድሉኝም አስበው ቤቱን ከበቡት፡፡ ቁባቴንም ያዙና ከእርስዋ ጋር ተኙ፣ እርስዋም ሞተች፡፡
6እኔም ቁባቴን ወሰድሁና ሰውነቷን ቆራረኋጥኋት፣ ቁርጥራጩንም በእስራኤል ርስት ወደሚገኝ ወደ እያንዳንዱ ክልል ላክሁት፣ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱን ክፋትና መአት በእስራኤል ላይ ፈጽመዋልና፡፡
7አሁንም፣ እናንተ እስራኤላውያን ሁላችሁም ተነጋገሩ፣ ምክራችሁንም ስጡ፣ ለዚህ ነገርም ፍርዳችሁን ስጡ!”
8ሕዝቡም ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በአንድ ላይ ተነሱ፣ እንዲህም አሉ፣ “ከእኛ ዘንድ ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ አይሄድም፣ ማንም ሰው ወደ ቤቱ አይመለስም!
9ነገር ግን አሁንም በጊብዓ ላይ ማድረግ ያለብን ነገር ይህ ነው፡- ዕጣው እንደሚመራን እንወጋታለን፡፡
10ከእስራኤል ነገዶች በሙሉ ለሕዝቡ ስንቅ እንዲይዙ ከመቶው አስር ሰው፣ ከሺህ መቶ ሰው፣ ከአስር ሺህ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን፣ ይህም ሕዝቡ ወደ ብንያም ጊብዓ በሚመጣበት ጊዜ እነርሱ በእስራኤል ላይ ለፈጸሙት ክፋት ይቀጧቸው ዘንድ ነው፡፡”
11ስለዚህም የእስራኤል ወታደሮች በሙሉ በአንድ ዓላማ በመስማማት በከተማይቱ ላይ ለመዝመት ተሰበሰቡ፡፡
12የእስራኤልም ነገዶች ወደ ብንያም ነገድ ሁሉ እንዲህ ብለው ሰዎችን ላኩ፣ “በእናንተ መካከል የተደረገው ይህ ክፉ ነገር ምንድር ነው?
13ስለዚህ እንድንገድላቸውና ይህንን ክፋት ከእስራኤል ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ በጊብዓ ውስጥ ያሉትን እነዚህን ክፉ ሰዎች አውጥታችሁ ስጡን፡፡” ነገር ግን ብንያማውያን የወንድሞቻቸውን የእስራኤልን ሕዝብ ቃል አልሰሙም፡፡
14የዚያን ጊዜ የብንያም ሕዝብ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ለመዋጋት ዝግጅት ያደርጉ ዘንድ ከየከተማው ወጥተው ወደ ጊብዓ ተሰበሰቡ፡፡
15የብንያም ሕዝብ ከየከተማው በአንድ ላይ ለመዋጋት መጡ፣ በዚያም ቀን በሰይፍ ስለት ለመዋጋት የሰለጠኑ 26, 000 ወታደሮች ነበሩ፤ ከዚህ በተጨማሪ ከጊብዓ ነዋሪዎች ሰባት መቶ የተመረጡ ሰዎች ተቈጠሩ፡፡
16ከእነዚህ ወታደሮች መካከል ሰባት መቶ የተመረጡ ግራኝ ሰዎች ነበሩ፤ እያንዳንዳቸውም ድንጋይ ወንጭፈው አንዲት ጠጕርስ እንኳ አይስቱም፡፡
17የእስራኤል ወታደሮች፣ ከብንያም ወገን የሆኑትን ሳይጨምር፣ በሰይፍ ስለት ለመዋጋት የሰለጠኑ አራት መቶ ሺህ ሰዎች ተቆጠሩ፡፡ እነዚህ በሙሉ የጦር ሰዎች ነበሩ፡፡
18የእስራኤልም ሕዝብ ተነሱ፣ ወደ ቤቴል ወጡ፣ ከእግዚአብሔርም ምክር ጠየቁ፡፡ እንዲህም ብለው ጠየቁ፣ “የብንያምን ልጆች ለመውጋት ለእኛ መጀመርያ ማን ይውጣልን?” እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፣ “ይሁዳ በመጀመርያ ይዋጋል፡፡”
19የእስራኤልም ሕዝብ በማለዳ ተነሱና በጊብዓ ፊት ለውጊያ ተዘጋጁ፡፡
20የእስራኤልም ወታደሮች ከብንያም ጋር ለመዋጋት ወጡ፡፡ እነርሱም በጊብዓ ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት ቦታ ቦታቸውን ይዘው ተሰለፉ፡፡
21የብንያም ወታደሮች ከጊብዓ ወጥተው መጡ፣ በዚያም ቀን ከእስራኤላውያን ሰራዊት 22, 000 ሰዎች ገደሉ፡፡
22ነገር ግን የእስራኤል ወታደሮች ራሳቸውን አበረቱ፣ በመጀመርያው ቀን ተሰልፈው በነበረበት ስፍራ ላይ እንደገና ቦታ ቦታቸውን በመያዝ የውጊያውን መስመር አዘጋጁ፡፡
23የእስራኤልም ሕዝብ ወደ ላይ ወጡና እስከ ማታ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሱ፡፡ከእግዚአብሔርም ምሪትን ፈለጉ እንዲህም ብለው ጠየቁ፣ “ከወንድሞቻችን ከብንያም ሕዝብ ጋር ለመዋጋት እንደገና ወደዚያ መቅረብ ይገባናልን?” እግዚአብሔርም “በእነርሱ ላይ ውጡና ግጠሟቸው” አለ፡፡
24ስለዚህም በሁለተኛው ቀን የእስራኤል ወታደሮች የብንያምን ወታደሮች ለመዋጋት ሄዱ፡፡
25በሁለተኛው ቀን የብንያም ወታደሮች ከጊብዓ እነርሱን ሊወጉ ወጡና ከእስራኤል ወታደሮች 18, 000 ሰዎች ገደሉ፡፡ እነዚህም ሰዎች ሁሉ በሰይፍ ለመዋጋት የሰለጠኑ ነበሩ፡፡
26የዚያን ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች ሁሉ፣ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡና አለቀሱ፣ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፣ እነርሱም በዚያ ቀን እስከ ምሽት ድረስ ጾሙ፣ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የሰላም መሥዋዕት አቀረቡ፡፡
27የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ጠየቁ፣ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በዚያ ነበረ፣
28በእነዚህ ጊዜያቶች የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በታቦቱ ፊት ያገለግል ነበር፣ “ከወንድሞቻችን ከብንያም ሕዝብ ጋር አንድ ጊዜ ለመዋጋት እንደገና እንሂድ ወይስ እንቅር?” እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፣ “ጥቃት ፈጽሙባቸው፣ ነገ እነርሱን እንድታሸንፉ እረዳችኋለሁና፡፡”
29ስለዚህ እስራኤል በጊብዓ ዙሪያ በምስጢራዊ ስፍራዎች የተደበቁ ሰዎች አኖሩ፡፡
30የእስራኤል ወታደሮች ከብንያም ወታደሮች ጋር ለሦስተኛ ቀን ተዋጉ፣ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት በጊብዓ ላይ የውጊያ መስመራቸውን ዘርግተው ተሰለፉ፡፡
31የብንያምም ሕዝብ ሄዱና ሕዝቡን ተዋጉ፣ ከከተማይቱም እንዲወጡ ተደረጉ፡፡ ከሕዝቡም አንዳንዶቹን መግደል ጀመሩ፡፡ ከእስራኤልም ወገን የሞቱ ሠላሳ የሚያህሉ ሰዎች በእርሻዎቹና በመንገዶቹ ነበሩ፣ ከመንገዶቹ አንዱ ወደ ቤቴል የሚወስድ ነው፣ ሌላኛው ደግሞ ወደ ጊብዓ የሚወስድ ነው፡፡
32የዚን ጊዜ የብንያምም ሕዝብ እንዲህ አሉ፣ “እንደ በፊቱ ተሸንፈዋል፣ ከእኛ እየሸሹ ነው፡፡” ነገር ግን የእስራኤል ወታደሮች እንዲህ አሉ፣ “እንሽሽ፣ ከከተማይቱ እንዲወጡና ወደ መንገዶቹ እንዲሄዱ እናድርጋቸው፡፡”
33የእስራኤልም ወታደሮች በሙሉ ከስፍራቸው ተነሱና በበኣልታማር ለውጊያ ራሳቸውን አዘጋጅተው ተሰለፉ፡፡ በምስጢራዊ ስፍራ ተደብቀው የነበሩት የእስራኤል ወታደሮችም ከነበሩበት ስፍራ ከጊብዓ ወጥተው ሮጡ፡፡
34ከእስራኤልም ሁሉ 10, 000 የተመረጡ ሰዎች በጊብዓ ላይ መጡ፣ ጦርነቱም በርትቶ ነበር፣ ነገር ግን ብንያማውያን ጥፋት ወደ እነርሱ ቀርቦ እንደነበር አላወቁም፡፡
35እግዚአብሔርም ብንያምን በእስራኤል ፊት ድል አደረገ፡፡ በዚያም ቀን የእስራኤል ወታደሮች 25, 100 የብንያም ሰዎችን ገደሉ፡፡ የሞቱት ሰዎች በሙሉ በሰይፍ ለመዋጋት ስልጠና የወሰዱ ነበሩ፡፡
36ስለዚህ የብንያም ወታደሮች እንደ ተሸነፉ አዩ፡፡ የእስራኤልም ሰዎች ለብንያም ስፍራ ለቀቁላቸው፣ ምክንያቱም ከጊብዓ ውጭ በድብቅ ስፍራዎች ባስቀመጡአቸው ሰዎች ላይ ተማምነው ነበርና፡፡
37የዚያን ጊዜ ተደብቀው የነበሩት ሰዎች ተነሱና ፈጥነው ወደ ጊብዓ ሮጡ፣ በከተማይቱም ውስጥ የሚኖረውን ሰው በሙሉ በሰይፋቸው ገደሉ፡፡
38በእስራኤል ወታደሮችና በምስጢር በተደበቁት ሰዎች መካከል ከከተማው የታላቅ ጢስ ደመና በምልክትነት እንዲያስነሡ ስምምነት ተደርጎ ነበር፡፡
39የእስራኤልም ወታደሮች በውጊያው ጊዜ ከጦርነቱ ርቀው እንዲያፈገፍጉ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ ብንያማውያን ማጥቃት ጀመሩ ሠላሳ የእስራኤልንም ሰዎች ገደሉ፣ እነርሱም እንዲህ አሉ፣ “እንደ መጀመርያው የጦርነት ጊዜ በእኛ ፊት መሸነፋቸው እርግጠኛ ነው፡፡”
40ነገር ግን የጢሱ ዓምድ ከከተማው ወደ ላይ መውጣት በጀመረ ጊዜ፣ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ሲመለከቱ ጢሱ ከከተማዋ በሙሉ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፡፡
41የዚያን ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች ዞረው አጠቋቸው፡፡ የብንያም ሰዎችም ደነገጡ፣ በእነርሱ ላይ ጥፋት እንደመጣባቸው አይተዋልና፡፡
42ስለዚህ ከእስራኤል ወታደሮች ተመልሰው ወደ ምድረ በዳው መንገድ ሸሹ፡፡ ነገር ግን ውጊያው ተከታትሎ ደረሰባቸው፡፡ የእስራኤልም ወታደሮች ከከተማዎቹ ወጡና በቆሙበት ስፍራ ገደሉአቸው፡፡
43እነርሱም ብንያማውያንን ከበቡና ተከትለዋቸው ሄዱ፤ በመኑሔም አሸነፉአቸው፣ ከጊብዓ በስተ ምሥራቅ በኩል እስካለው ስፍራ ድረስ አሳደዱአቸው፡፡
44ከብንያም ነገድም 18, 000 ወታደሮች ሞቱ፣ እነዚህ ሰዎች በሙሉ በጦርነት ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ፡፡
45እነርሱም ተመልሰው በምድረ በዳ ወዳለው ወደ ሬሞን ዓለት ሸሹ፡፡ እስራኤላውያንም ከእነርሱ ተጨማሪ አምስት ሺህ ሰዎችን በየመንገዱ ገደሉ፡፡ እነርሱም ተከታተሉአቸው፣ ወደ ጊድአምም በቅርብ እየተከታተሉአቸው ተጨማሪ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደሉ፡፡
46በዚያ ቀን የሞቱት የቢኒያም ወታደሮች በሙሉ 25, 000 በሰይፍ ለመዋጋት ልዩ ስልጠና የወሰዱ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህ በሙሉ በጦርነት ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ፡፡
47ነገር ግን ስድስት መቶ ሰዎች ተመልሰው በምድረ በዳ ወዳለው ወደ ሬሞን ዓለት ሸሹ፡፡ ለአራት ወራት ያህል በሬሞን ዓለት ተቀመጡ፡፡
48የእስራኤልም ወታደሮች በብንያም ሕዝብ ላይ እንደገና ተመለሱ፣ ሞላውን ከተማ፣ ከብቶችንና ያገኙትንም ሁሉ አጠቁ ደግሞም ገደሉ፡፡ በመንገዳቸው ያገኙትን ማንኛውንም ከተማ ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።