1በዚያም ዘመን፣ በእስራኤል ውስጥ ንጉሥ ባልነበረበት ጊዜ፣ በኮረብታማው የኤፍሬም አገር እጅግ በጣም ሩቅ በሆነ አካባቢ ለአጭር ጊዜ የኖረ አንድ ሌዋዊ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም አንዲትን ሴት ቁባት አድርጎ ወሰዳት፡፡
2ነገር ግን ቁባቱ ለእርሱ ታማኝ አልነበረችም፤ እርሱን ተወችውና ተመልሳ ወደ አባትዋ ቤት ወደ ቤተ ልሔም ይሁዳ ሄደች፡፡ እርስዋም በዚያ አራት ወር ቆየች፡፡
3የዚያን ጊዜ ባልዋ ተነሣና ተመልሳ ወደ እርሱ እንድትመጣ ለማባበል ተከትሏት ሄደ፡፡ የእርሱ አገልጋይና ሁለት አህዮች ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ እርስዋም ወደ አባትዋ ቤት አስገባችው፡፡የልጅቱ አባት ባየው ጊዜ ደስ አለው፡፡
4የልጂቱ አባት፣ አማቱም በቤቱ ለሦስት ቀን እንዲቆይ ለመነው፡፡ እነርሱም በሉ፣ ጠጡ፣ ሌሊቱንም በዚያ አሳለፉ፡፡
5በአራተኛው ቀን ማልደው ተነሡ፣ እርሱም ለመሄድ ተዘጋጀ፣ ነገር ግን የልጂቱ አባት አማቹን እንዲህ አለው፣ “እንድትበረታ እንጀራ ብላ፣ ከዚያ መሄድ ትችላለህ፡፡”
6ስለዚህ ሁለቱም በአንድ ላይ ለመብላትና ለመጠጣት ተቀመጡ፡፡ ከዚያም የልጂቱ አባት እንዲህ አለ፣ “እባክህ ሌሊቱን ደግሞ እዚህ ለማሳለፍ ፈቃደኛ ሁን፣ መልካም ጊዜም ይሁንልህ፡፡”
7ሌዋዊው ለመሄድ በማለዳ በተነሳ ጊዜ፣ የወጣቷ ሴት አባት እንዲቆይ ለመነው፣ ከዚህ የተነሳ እቅዱን ለወጠና ሌሊቱን በዚያ አሳለፈ፡፡
8በአምስተኛው ቀን ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፣ ነገር ግን የልጂቱ አባት እንዲህ አለ፣ “ሰውነትህን አበርታ፣ እስከ ማምሻ ድረስ ቆይ አለው፡፡ ስለዚህ ሁለቱም አብረው በሉ፡፡
9ሌዋዊው፣ ቁባቱና አገልጋዮቹ ለመሄድ በተነሱ ጊዜ፣ የልጂቱ አባት አማቱ እንዲህ አለው፣ “ተመልከት፣ አሁን ቀኑ እየመሸ ነው፡፡ እባክህ ሌላ ሌሊት በዚህ ቆዩ፣ መልካም ጊዜም ይሁንልህ፡፡ ነገ በማለዳ ተነስታችሁ ወደ ቤታችሁ ተመልሳችሁ መሄድ ትችላላችሁ፡፡”
10ነገር ግን ሌዋዊው ሌሊቱን በዚያ ለማሳለፍ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ተነሳና ሄደ፡፡ ኢየሩሳሌምም ወደ ተባለችው ወደ ኢያቡስ ሄደ፡፡ ሁለት የተጫኑ አህዮች ነበሩት፣ ቁባቱም ከእርሱ ጋር ነበረች፡፡
11ወደ ኢያቡስም በቀረቡ ጊዜ መሸባቸው፣ አገልጋዩም ለጌታው እንዲህ አለው፣ “ና፣ ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ እንሂድና ሌሊቱን በዚያ እናሳልፍ፡፡”
12ጌታውም፣ “የእስራኤል ሕዝብ ወገን ወዳልሆነ ወደ እንግዳ ሕዝብ ከተማ ውስጥ አንገባም፡፡ እኛ ወደ ጊብዓ እንሄዳለን፡፡”
13ሌዋዊውም ለወጣቱ ሰው እንዲህ አለው፣ “ና፣ ከእነዚህ ስፍራዎች ወደ አንዱ እንሂድ፣ ሌሊቱንም በጊብዓ ወይም በራማ እናሳልፍ፡፡”
14ስለዚህ መንገዳቸውን ቀጠሉ፣ የብንያም ነገድ ወደምትሆነው ወደ ጊብዓ ግዛት ሲቀርቡ ፀሐይ ገባችባቸው፡፡
15እነርሱም ሌሊቱን በጊብዓ ለማሳለፍ ወደዚያ አቀኑ፡፡ እርሱም ወደ ውስጥ ገባና በከተማው አደባባይ ተቀመጠ፣ ሌሊቱን በዚያ ያሳልፉ ዘንድ ወደ ቤቱ የወሰዳቸው ማንም ሰው አልነበረምና፡፡
16ነገር ግን በዚያን ጊዜ አንድ ሽማግሌ ሰው ከእርሻ ሥራው በምሽት እየመጣ ነበር፡፡ እርሱም ከኮረብታማው ከኤፍሬም አገር ነበረ፣ እርሱም በጊብዓ በእንግድነት ተቀምጦ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያ ስፍራ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ብንያማውያን ነበሩ፡፡
17እርሱም ዓይኑን አነሳና መንገደኛውን በከተማው አደባባይ አየው፡፡ ሽማግሌውም እንዲህ አለ፣ “ወዴት ትሄዳለህ? ከወዴትስ መጣህ?”
18ሌዋዊውም እንዲህ አለው፣ “እኛ ከቤተ ልሔም ይሁዳ በጣም ሩቅ ወደሆነው ወደ ኮረብታማው ወደ ኤፍሬም አገር እንሄዳለን፣ እኔም የመጣሁት ከዚያ ነው፡፡ ወደ ቤተ ልሔም ይሁዳ ሄጄ ነበር፣ አሁን ወደ እግዚአብሔር ቤት እየሄድሁ ነው፣ ነገር ግን ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ማንም ሰው የለም፡፡
19ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፣ ለእኔና እዚህ ላለችው ለሴት አገልጋይህ፣ ከአገልጋዮችህም ጋር ላለው ለዚህ ወጣት ሰው እንጀራና የወይን ጠጅ አለን፡፡ አንዳችም አላጣንም፡፡”
20ሽማግሌውም ሰላምታ አቀረበላቸው፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን! የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ እኔ እሰጣችኋለሁ፡፡ በአደባባይ ግን ሌሊቱን አትደሩ” አለው፡፡
21ስለዚህም ሰውየው ሌዋዊውን ወደ ቤቱ ወሰደው፣ ለአህዮቹም ገፈራ ሰጣቸው፡፡ እግራቸውን ታጠቡ፣ በሉም ጠጡም፡፡
22እነርሱም መልካም ጊዜ ነበራቸው፣ ክፉ የሆኑ የከተማይቱ ሰዎች ያደሩበትን ቤት ከበቡ፣ በሩንም ይደበድቡ ነበር፡፡ የቤቱ ባለቤት ለሆነው ለሽማግሌው እንዲህ አሉት፣ “ከእርሱ ጋር መተኛት እንድንችል ወደ ቤትህ የገባውን ሰው አምጣው፡፡”
23ሰውየውም፣ የቤቱ ባለቤት፣ ወደ እነርሱ ሄደና እንዲህ አላቸው፣ “አይሆንም፣ ወንድሞቼ ሆይ፣ ይህን ክፉ ነገር እባካችሁ አታድርጉ! ይህ ሰው ወደ ቤቴ የገባ እንግዳ ስለሆነ፣ ይህን ክፉ ነገር አትሥሩ፡፡
24ተመልከቱ፣ ድንግል ልጄና የእርሱም ቁባት እዚህ አሉ፡፡ አሁን ሄጄ ላምጣቸው፡፡ አስነውሩአቸው፣ የፈለጋችሁትንም አድርጉባቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰው ላይ እንደዚህ ያለ ክፉ ነገር አታድርጉበት!”
25ነገር ግን ሰዎቹ እርሱን አልሰሙትም፣ ስለዚህ ሰውዮው ቁባቱን ያዛትና ወደ ውጭ አወጣላቸው፡፡ እነርሱም ያዟትና ከእርሷ ጋር ተኙ፣ ሌሊቱን በሙሉ አመነዘሩባት፣ ጎህም ሲቀድ ለቀቁአት፡፡
26ሴቲቱም በማለዳ መጣችና ጌታዋ ባለበት በሰውዮው ቤት በር ወደቀች፣ ጸሐይ እስኪወጣ ድረስ እዚያው ተዘረረች፡፡
27ጌታዋም በማለዳ ተነሣና የቤቱን በር ከፈተ፣ መንገዱንም ለመሄድ ወጣ፡፡ እርሱም ቁባቱ እጅዋን በመድረኩ ላይ ዘርግታ በበሩ ተዘርራ አያት፡፡
28ሌዋዊውም እንዲህ አላት፣ “ተነሺ፡፡ እንሂድ፡፡” ነገር ግን ምንም መልስ አልነበረም፡፡ እርሱም በአህያው ላይ ጫናት፣ ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
29ሌዋዊውም ወደ ቤቱ በመጣ ጊዜ፣ ቢላዋ ወሰደ፣ ቁባቱንም ይዞ ቆራረጣት፣ ብልት በብልት ለአሥራ ሁለት ቈራርጦ ቁራጮቹን ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ላከው፡፡
30ይህንን ያየ ሁሉ እንዲህ አለ፣ “የእስራኤል ሕዝብ ከግብፅ ምድር ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልተደረገም ወይም አልታየም፡፡ ስለ ነገሩ አስቡበት! ምክር ስጡን! ምን ማድረግ እንዳለብን ንገሩን!”