መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መሳፍንት 21

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያን ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች በምጽጳ “ከእኛ ማንም ሰው ሴት ልጁን በጋብቻ ለብንያማውያን መዳር የለበትም” በማለት ቃል ገብተው ነበር፡፡
2ከዚያም ሕዝቡ ወደ ቤቴል ሄዱና በዚያ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ምሽቱ ድረስ ተቀመጡ፣ ድምፃቸውንም ከፍ በማድረግ አምርረው አለቀሱ፡፡
3እነርሱም እንዲህ ሲሉ ጮኹ፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህ በእስራኤል ለምን ሆነ? ዛሬ ከእኛ አንዱ ነገድ መታጣቱ ለምንድን ነው?”
4በሚቀጥለውም ቀን ሕዝቡ በጠዋት ተነሡና በዚያ መሠዊያ ሠሩ፣ የሚቃጠልና የሰላም መሥዋዕትንም አቀረቡ፡፡
5የእስራኤልም ሕዝብ እንዲህ አሉ፣ “ከእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ያልመጣ የትኛው ነው?” በምጽጳ ወደ እግዚአብሔር ፊት ስላልመጣ ማንም ሰው በጣም ወሳኝ የሆነ ቃል ኪዳን አድርገው ነበርና፡፡ እነርሱም እንዲህ አሉ፣ “እርሱ ፈጽሞ ሊገደል ይገባዋል፡፡”
6የእስራኤልም ሕዝብ ስለ ወንድማቸው ስለ ብንያም አዘኑ፡፡ አነርሱም እንዲህ አሉ፣ “ዛሬ ከእስራኤል ነገድ አንዱ ተቆርጧል፡፡
7ሴቶች ልጆቻችንን ከእነርሱ ለአንዳቸውም ቢሆን በጋብቻ ላንሰጥ ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለገባን ለተረፉት ሚስቶችን የሚሰጣቸው ማን ነው?”
8እነርሱም አሉ፣ “ከእስራኤል ነገድ በምጽጳ ወደ እግዚአብሔር ያልመጣ የትኛው ነው?” ከኢያቢስ ገለዓድ ወደ ጉባኤው አንድም ሰው አለመምጣቱን አወቁ፡፡
9ሕዝቡም በቅደም ተከተል ተሰልፈው እንዲቆጠሩ በተደረገ ጊዜ፣ እነሆ፣ ከኢያቢስ ገለዓድ ነዋሪዎች ማንም ሰው በዚያ አልነበረም፡፡
10ጉባኤውም 12, 000 ኃያላን ሰዎችን ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ልከው በዚያ ያሉትን ሰዎች ሴቶችንና ሕፃናትንም ጭምር ጥቃት እንዲያደርሱባቸውና እንዲገድሏቸው አዘዙአቸው፡፡
11“እንግዲህ የምታደርጉት ይህ ነው፡- ወንዱን በሙሉ እንዲሁም ከወንድ ጋር የተኛችውንም ሴት በሙሉ ግደሉ፡፡”
12ሰዎቹም በኢያቢስ ገለዓድ ከሚኖሩት መካከል ከወንድ ጋር ተኝተው የማያውቁ አራት መቶ ወጣት ሴቶች አገኙ፣ እነርሱንም በከነዓን ወዳለው በሴሎ ወደሚገኘው ሰፈር ወሰዷቸው፡፡
13ጉባኤውም በሙሉ መልክት ላኩ፣ በሬሞን ዓለት ለነበሩት ለብንያም ሕዝብ የሰላም ጥሪ እንዳቀረቡላቸውም ነገሩአቸው፡፡
14ሲለዚህ በዚያን ጊዜ ብንያማውያን ተመለሱ፣ የኢያቢስ ገለዓድንም ሴቶች ሰጧቸው፡፡ ነገር ግን ለሁሉም የሚበቁ ሴቶች አልነበሩም፡፡
15ሕዝቡም በብንያም ላይ በሆነው ገር አዘኑ፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር በእስራኤል ነገዶች መካከል ስብራት አድርጓልና፡፡
16የዚያን ጊዜ የጉባኤው መሪዎች እንዲህ አሉ፣ “የብንያም ሴቶች ተገድለዋልና፣ ለተረፉት ብንያማውያን ሚስቶችን እንዴት እናግኝላቸው?”
17እንዲህም አሉ፣ “ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዳይጠፋ ከብንያም አሁን በሕይወት ላሉት ሰዎች ርስት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
18ከሴቶች ልጆቻችን ሚስቶች ልንሰጣቸው አንችልም፡፡ የእስራኤል ሕዝብ፣ ‘ለብንያም ሚስት የሚሰጥ ርጉም ይሁን’ የሚል ቃል ኪዳን ገብተው ነበርና፡፡”
19ስለዚህ እንዲህ አሉ፣ “በቤቴል በሰሜን በኩል፣ ከቤቴልም ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በምሥራቅ በኩል፣ በለቦና በደቡብ በኩል ባለችው በሴሎ በየዓመቱ የእግዚአብሔር በዓል እንዳለ ታውቃላችሁ፡፡”
20እነርሱም ለብንያም ሰዎች እንዲህ ብለው አዘዙአቸው፣ “ሂዱና በምስጢር ተሸሸጉ፣ በወይኑ ስፍራም ተደበቁ፡፡
21የሴሎ ልጃገረዶች ለመጨፈር የሚወጡበትን ጊዜ ተመለክቱ፣ የዚያን ጊዜ ከወይኑ ስፍራ ፈጥናችሁ ውጡና እያንዳንዳችሁ ከሴሎ ልጃገረዶች ለየራሳችሁ ሚስት ውሰዱ፣ ከዚያም ወደ ብንያም ምድር ተመለሱ፡፡
22አባቶቻቸው ወይም ወንድሞቻቸው ሊጣሉን በመጡ ጊዜ፣ እንዲህ እንላቸዋለን፣ ‘ምህረት አድርጉልን! ባልና ሚስት ሆነው ይጽኑ ምክንያቱም በጦርነቱ ጊዜ እኛ ለያንዳንዳቸው ሚስት አላገኘንላቸውም፡፡ እናተ ደግሞ ሴቶች ልጆቻችሁን ለእነርሱ ስላልሰጣችሁ፣ ቃል ኪዳኑን በተመለከተ በደለኞች አይደላችሁም፡፡’”
23የብንያምም ሕዝብ እንዲሁ አደረጉ፣ በቍጥራቸው መጠን የሚያስፈልጋቸውን ያህል ሚስቶች ይጨፍሩ ከነበሩት ልጃገረዶች ወሰዱ፣ ሚስትም ይሆኗቸው ዘንድ ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ እነርሱም ወደ ርስታቸው ስፍራ ተመልሰው ሄዱ፤ ከተሞችንም እንደገና ሠሩ፣ በውስጣቸውም ኖሩ፡፡
24በዚያን ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ያን ስፍራ ለቀቁና ወደ ቤታቸው ሄዱ፣ እያንዳንዱም ወደ ነገዱና ወደ ወገኑ ሄደ፣ እያንዳንዱም ወደ ርስቱ ተመለሰ፡፡
25በዚያም ዘመን በእስራኤል ውስጥ ንጉሥ አልነበረም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በዓይኖቹ ፊት መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።