መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መሳፍንት 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከኢያሱ ሞት በኋላ፣ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው ጠየቁ፡- “ከነዓናውያንን ለመዋጋት ወደላይ ስንሄድ ማን ይመራናል?”
2እግዚአብሔርም አላቸው፡- “ይሁዳ ይመራችኋል፡፡ ተመልከቱ፣ ምድሪቱን ለእነርሱ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፡፡”
3የይሁዳም ሰዎች ለወንድሞቻቸው ለስምዖን ሰዎች እንዲህ አሏቸው፡- “ከነዓናውያንን አብረን እንወጋቸው ዘንድ ከእኛ ጋር ለእኛ ወደተሰጠው ክልል ኑ፡፡ እኛም እንዲሁ ለእናንተ ወደተሰጠው ክልል እንመጣለን፡፡” ስለዚህም የስምዖን ነገድ ከእነርሱ ጋር ሄዱ፡፡
4የይሁዳ ሰዎችም ወደ ላይ ወጡ፣ እግዚአብሔርም በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ላይ ድልን ሰጣቸው፡፡ በቤዜቅም ከእነርሱ አስር ሺህ ሰዎችን ገደሉ፡፡
5አዶኒ ቤዜቅን በቤዜቅ አገኙት፣ ከእርሱም ጋር ተዋግተው ከነዓናውያንና ፌርዛውያንን አሸነፉ፡፡
6አዶኒ ቤዜቅ ግን ሸሸ፣ ተከታትለውም አገኙትና ያዙት፣ የእጁንና የእግሩን አውራጣቶች ቆረጡ፡፡
7አዶኒ ቤዜቅም እንዲህ አለ፡- “የእግርና የእጅ አውራ ጣቶቻቸው የተቆረጠባቸው ሰባ ነገስታት ከእኔ ማዕድ ስር መብላቸውን ሰበሰቡ፡፡ እኔ እንዳደረግሁት፣ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አደረገብኝ፡፡” እርሱንም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፣ በዚያም ሞተ፡፡
8የይሁዳ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ከተማ ጋር ተዋግተው ተቆጣጠሯት፡፡ በሰይፍ ስለት ወጓት፣ ከተማዋንም አቃጠሏት፡፡
9ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሰዎች በኮረብታማው አገር ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያንን ለመዋጋት፣ወደ ኔጌብና ወደ ምዕራቡ ኮረብታ ግርጌ ወረዱ፡፡
10ይሁዳም በኬብሮን (የኬብሮን ስም ቀድሞ ቂርያት አርባቅ ትባል ነበር) የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ሄደ፣ ሴሲን፣ አክመንና ቴላሚንም ድል አደረጉ፡፡
11ከዚያም የይሁዳ ሰዎች ወደ ዴብር (የዴብር ስም ቀድሞ ቅርያት ሤፍር ተብላ ትጠራ ነበር) ሄዱ፡፡
12ካሌብም አለ፣ “ቅርያት ሤፍርን የሚዋጋና የሚቆጣጠራትን ሰው፣ ሴት ልጄን ዓክሳን ሚስት ትሆነው ዘንድ እሰጠዋለሁ፡፡”
13የካሌብ ታናሽ ወንድም የቄናዝ ልጅ ጎቶንያልም ዴብርን ተቆጣጠረ፣ ስለዚህ ካሌብ ሴት ልጁን ዓክሳን ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው፡፡
14ዓክሳም ወዲያውኑ ወደ ጎቶንያል መጣች፣ ለእርሱም አባቷ እርሻ እንዲሰጣት እንዲለምነው ጠየቀችው፡፡ ከአሕያዋም በወረደች ጊዜ፣ ካሌብ እንዲህ ብሎ ጠየቃት፣ “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?”
15እርሷም እንዲህ አለችው፣ “በረከትን ስጠኝ፡፡ በኔጌብ ምድር ያለውን መሬት ሰጥተኸኛልና፣ የውሃ ምንጭንም ስጠኝ፡፡” ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጭ ሰጣት፡፡
16የቄናዊው የሙሴ አማት ዘሮችም ከባለ ዘንባባዋ ከተማ ለቀው ከይሁዳ ሰዎች ጋር በኔጌብ ወዳለችው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ከይሁዳ ሰዎች ጋር በዓራድ አጠገብ ለመኖር ሄዱ፡፡
17የይሁዳ ሰዎችም ከወንድሞቻቸው ከስምዖን ሰዎች ጋር ሄዱና በጽፋት ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያንን ወጓቸው፣ፈጽሞም አጠፏት፡፡ የከተማይቱም ስም ሔርማ ይባል ነበር፡፡
18በተጨማሪ የይሁዳ ሰዎች ጋዛንና በዙርያዋ ያለውን አገር፣ አስቀሎናንና በዙርያዋ ያለውን አገር እንደዚሁም አቃሮንንና በዙርያዋ ያለውን አገር ሁሉ ተቆጣጠሩ፡፡
19እግዚአብሔርም ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፣ የኮረብታማውንም አገር ተቆጣጠሩ፣ ነገር ግን በረባዳው ምድር የሚኖሩትን ሰዎች ማስወጣት አልቻሉም ነበር ምክንያቱም ነዋሪዎቹ የብረት ሰረገሎች ነበሯቸው፡፡
20ሙሴም እንደተናገረ ኬብሮንን ለካሌብ ሰጡት፣ እርሱም የዔናቅን ሶስት ልጆች ከዚያ አስወጣቸው፡፡
21ነገር ግን የቢንያም ሰዎች በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ኢያቡሳውያንን አላስወጧቸውም፡፡ ስለዚህ ኢያቡሳውያን እስከዛሬ ድረስ ከቢንያም ሰዎች ጋር በኢየሩሳሌም ይኖራሉ፡፡
22የዮሴፍ ወገንም ቤቴልን ለመውጋት ተዘጋጁ፣ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበር፡፡
23ቀድሞ ሎዛ ተብላ ትጠራ የነበረችውን ቤቴልን ለመሰለል ሰዎችን ላኩ፡፡
24ሰላዮቹም ከከተማው አንድ ሰው ሲወጣ አዩ፣ እንዲህም አሉት፣ “ወደ ከተማው እንዴት መግባት እንደምንችል እባክህ አሳየን፣ ለአንተም ቸርነት እናደርግልሃለን፡፡”
25እርሱም ወደ ከተማው መግቢያውን መንገድ አሳያቸው፡፡ እነርሱም በሰይፍ ስለት ከተማውን ወጉ፣ ያንን ሰውና ቤተሰቦቹንም እንዲያመልጡ አደረጓቻው፡፡
26ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ሐገር ሄደና ከተማ ገነባ ስሙንም ሎዛ አለው፣ የዚያ ቦታ ስምም እስከዛሬ ሎዛ ነው፡፡
27የምናሴ ሰዎች በቤትሳንና በመንደሮቿ፣ በታዕናክና በመንደሮቿ፣ በዶርና በመንደሮቿ፣ በይብለዓምና በመንደሮቿ፣ በመጊዶና በመንደሮቿ ይኖሩ የነበሩትን ሰዎች አላስወጡአቸውም፣ ምክንቱም ከነዓናውያን በዚያ ለመቀመጥ ወስነው ስለነበር ነው፡፡
28እስራኤልም በበረታ ጊዜ፣ ከነዓናውያንን የጉልበት ስራ እየሰሩ እንዲያገለግሉአቸው አስገደዷቸው፣ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አላስወጧቸውም፡፡
29ኤፍሬም በጌዝር ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያን አላስወጣቸውም፣ ስለዚህ ከነዓናውያን በእነርሱ መካከል በጌዝር መኖር ቀጠሉ፡፡
30ዛብሎንም በቂድሮን የሚኖሩትን ሰዎች ወይም በነህሎል ይኖሩ የነበሩትንም ሰዎች አላስወጣቸውም፣ ስለዚህ ከነዓናውያን በእነርሱ መካከል መኖር ቀጠሉ፣ ነገር ግን ዛብሎን ከነዓናውያን የጉልበት ስራ እየሰሩ እንዲያገለግሉአቸው ያስገድዳቸው ነበር፡፡
31አሴር በዓኮ፣ በሲዶን፣ በአሕላብ፣ በአክዚብ፣ በሒልባን፣ በአፌቅ፣ በረአብም የሚኖሩትን ሰዎች አላስወጣቸውም፡፡
32ስለዚህ የአሴር ነገድ በምድሪቱ በሚኖሩት በከነዓናውያን መካከል ኖሩ፣ ምክንያቱም አላስወጧቸውም ነበር፡፡
33የንፍታሌም ነገድ በቤት ሳሚስና በቤት ዓናት ይኖሩ የነበሩትን ሰዎችን አላስወጧቸውም፡፡ ስለዚህ የንፍታሌም ነገድ በምድራቸው ይኖሩ በነበሩ በነዓናውያን ሰዎች መካከል አብረው ኖሩ፡፡ ይሁን እንጂ የቤት ሳሚስና የቤት ዓናት ነዋሪዎች ለንፍታሌም ሰዎች የጉልበት ስራ እንዲሰሩ ይገደዱ ነበር፡፡
34አሞራውያንም የዳን ነገድ በኮረብታማው አገር እንዲኖሩ አስገደዷቸው፣ ወደ ሜዳማ ስፍራ ወርደው እንዲኖሩ አልፈቀዱላቸውም ነበር፡፡
35ስለዚህ አሞራውያን በሔሬስ ተራራ፣ በኤሎን፣ በሸዓልቢምም ኖሩ፣ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት ወታደራዊ ኃይል በእነርሱ ላይ በረቱባቸው፣ ከዚህ የተነሳ ከባድ የጉልበት ስራ እየሰሩ
36የአሞራውያንም ድንበር በሴላ ካለው ከአቅረቢም ኮረብታ ጀምሮ እስከ ኮረብታማው አገር ድረስ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።