መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መሳፍንት 18

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያን ዘመን በእስራኤል ውስጥ ንጉሥ አልነበረም፡፡ የዳን ነገድ ተወላጆች የሚቀመጡበትን ርስት ይፈልጉ ነበር፣ እስከዚያ ቀን ድረስ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልተቀበሉም ነበርና፡፡
2የዳን ሰዎች ከአጠቃላይ ወገናቸው በሙሉ ከጾርዓ ጀምሮ እስከ ኤሽታኦል ድረስ በጦርነት ልምድ ያላቸውን አምስት ሰዎች በእግራቸው ሄደው ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲያዩ ላኩ፡፡ ለእነርሱም እንዲህ አሉአቸው፣ “ሂዱና ምድሪቱን ሰልሉ፡፡” እነርሱም ወደ ኮረብታማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጡና ሌሊቱን በዚያ አሳለፉ፡፡
3በሚካ ቤት አጠገብ በነበሩ ጊዜ፣ የአንድ ወጣት ሌዋዊ ንግግር አወቁ፡፡ ስለዚህ አስቆሙትና እንዲህ ብለው ጠየቁት፣ “ወደዚህ ማን አመጣህ? በዚህ ስፍራ ምን ታደርጋለህ? ለምን ወደዚህ መጣህ?”
4እርሱም እንዲህ አላቸው፣ “ሚካ ለእኔ ያደረገው ነገር ይህ ነው፡- የእርሱ ካህን እንድሆን ቀጠረኝ፡፡”
5እነርሱም እንዲህ አሉት፣ “የምንሄድበት መንገድ መቃናቱን ወይም አለመቃናቱን እናውቅ ዘንድ፣ እባክህ፣ የእግዚአብሔርን ምክር ጠይቅልን፡፡”
6ካህኑም ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፣ “በሰላም ሂዱ፡፡ ልትሄዱ በሚገባችሁ መንገድ እግዚአብሔር ይመራችኋል፡፡”
7የዚያን ጊዜ አምስቱ ሰዎች ሄዱና ወደ ላይሽ መጡ፣ ሲዶናውያን በጸጥታ ያለስጋት ይኖሩ እንደነበረ ሁሉ፣ በዚያም ተዘልለው ይኖሩ የነበሩትን ሕዝብ አዩ፡፡ በምድሪቱም በየትኛውም መልኩ የገዛቸው፣ ወይም ያስቸገራቸው አልነበረም፡፡ ከሲዶናውያን በጣም ርቀው ይኖሩ ነበር፣ ከማንኛውም ሕዝብ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡
8በጾርዓና በኤሽታኦል ውስጥ ወደነበሩት ወንድሞቻቸው ተመለሱ፡፡ ዘመዶቻቸውም እንዲህ ብለው ጠየቁአቸው፣ “ምን ወሬ ይዛችኋል?”
9እነርሱም እንዲህ አሉ፣ “ኑ! እንውጋቸው! ምድሪቱን አይተናታል፣ በጣም ጥሩ ናት፡፡ እናንተ ዝም ትላላችሁን? ምድሪቱን ከመውጋትና ከመውረስ አትዘግዩ፡፡
10በሄዳችሁ ጊዜ፣ ያለ ስጋት እንደሚኖሩ ወደሚያስቡ ሕዝብ ትደርሳላችሁ፣ ምድሪቱም ሰፊ ናት! እግዚአብሔርም ለእናንተ ሰጥቶአችኋል፣ በምድር ካለው ነገር ሁሉ አንዳች የማይጎድልባት ስፍራ ናት፡፡
11ከዳን ወገን የሆኑና የጦር መሳርያ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሥተው ሄዱ፡፡
12እነርሱም ሄዱና በይሁዳ ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የዚያ ስፍራ ስም የዳን ሰፈር ብለው የሚጠሩት ለዚህ ነው፤ እርሱም ከቂርያትይዓሪም በምዕራብ በኩል ነው፡፡
13እነርሱም ከዚያ ተነስተው ወደ ኮረብታማው የኤፍሬም አገር አልፈው ሄዱ፣ ወደ ሚካም ቤት መጡ፡፡
14ከዚያም የላይሽን አገር ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ለዘመዶቻቸው እንዲህ አሉአቸው፣ “በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድና ተራፊም፣ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል እንዳሉ ታውቃላችሁን? ምን እንደምታደርጉ አሁን ወስኑ፡፡”
15ስለዚህ ከዚያ ዘወር አሉና ወጣቱ ሌዋዊ ይኖርበት ወደነበረው ወደ ሚካ ቤት መጡ፤ ሰላምታም አቀረቡለት፡፡
16በዚያን ጊዜ የጦር መሳርያ የታጠቁት ስድስት መቶ ዳናውያን በበሩ መግቢያ ቆሙ፡፡
17ካህኑ የጦር መሳርያ ከታጠቁት ከስድስት መቶ ሰዎች ጋር በበሩ አካባቢ ቆሞ በነበረበት ጊዜ፣ ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወደዚያ ሄዱና የተቀረጸውን ምስል፣ ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል ወሰዱ፡፡
18እነዚህ ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል፣ ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በወሰዱ ጊዜ፣ ካህኑ ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፣ “ምን ታደርጋላችሁ?”
19እነርሱም እንዲህ አሉት፣ “ዝም በል! እጅህን በአፍህ ላይ ጫንና ከእኛ ጋር ና፣ ለእኛም አባትና ካህን ሁንልን፡፡ ለአንተስ ለአንድ ሰው ቤት ካህን መሆን ወይስ በእስራኤል ውስጥ ላለው ነገድና ወገን ሁሉ ካህን መሆን ይሻልሃል?”
20የካህኑም ልብ ደስ አለው፡፡ ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና የተቀረጸውንም ምስል ወሰደና ከሕዝቡ ጋር ሄደ፡፡
21ስለዚህ እነርሱ ዞሩና ሄዱ፡፡ ሕፃናቶችን፣ ከብቶችንና ንብረታቸውን በፊታቸው አስቀደሙ፡፡
22ከሚካም ቤት ጥቂት በራቁ ጊዜ፣ በሚካ ቤት አጠገብ በነበሩት ቤቶች ውስጥ የነበሩ ሰዎች ተጠራርተው ተሰበሰቡ፣ የዳን ሰዎችንም ተከትለው ደረሱባቸው፡፡
23ወደ ዳንም ሰዎች ጮኹ፣ ዘወር ብለው ለሚካም እንዲህ አሉት፣ “ተሰብስባችሁ በአንድ ላይ የመጣችሁት ለምንድን ነው?”
24እርሱም፣ “የሠራኋቸውን አማልክቴን ሰረቃችሁ፣ ካህኔንም ይዛችሁ ሄዳችሁ፡፡ ሌላ ምን የቀረኝ ነገር አለ? ‘ያስጨነቀህ ምንድን ነው?’ ብላችሁ እንዴት ልትጠይቁኝ ትችላላችሁ፡፡”
25የዳን ሰዎችም እንዲህ አሉት፣ “ምንም ዓይነት ንግግር ስትናገር እንድንሰማ አታድርገን፣ አለዚያ አንዳንድ የተቈጡ ሰዎች ይጎዱሃል፣ አንተና ቤተሰቦችህም ትሞታላችሁ፡፡”
26የዚያን ጊዜ የዳን ሰዎች መንገዳቸውን ሄዱ፡፡ ሚካ ከእርሱ ይልቅ እነርሱ እጅግ በጣም የበረቱ እንደሆኑ ባየ ጊዜ፣ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
27የዳን ሰዎችም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ካህኑን ወሰዱና ወደ ላይሽ መጡ፣ በሰላምና ያለ ስጋት ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ መጥተው በሰይፍ ስለት ገደሉአቸው፣ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት፡፡
28እነርሱን የሚያድን አንድም ሰው አልነበረም ምክንያቱም ከተማይቱ ከሲዶና በጣም ራቅ ያለች ነበረች፣ እነርሱም ከሌሎች ሰዎች ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡ እርስዋም በቤትሮዖብ አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ ነበረች፡፡ የዳን ሰዎችም ከተማይቱን እንደገና ሠሩና ተቀመጡባት፡፡
29ከተማይቱንም ከእስራኤል ወንዶች ልጆች አንዱ በሆነው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ የከተማይቱ ስም ላይሽ ነበረ፡፡
30የዳን ሰዎችም ለራሳቸው የተቀረጸ ምስል አቆሙ፣ የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ ዮናታን፣ እርሱና ወንዶች ልጆቹ ምድሪቱ እስከምትያዝበት ቀን ድረስ ለዳን ሰዎች ካህናት ነበሩ፡፡
31ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ በነበረበት ጊዜ ሁሉ፣ ሚካ የሰራውን የተቀረጸ ምስል አመለኩ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።