1በኮረብታማውም በኤፍሬም አገር አንድ ሰው ነበር፣ ስሙም ሚካ ይባላል፡፡
2ለእናቱም እንዲህ አላት፣ “ከአንቺ ዘንድ ተወስዶ የነበረው 1, 100 ብር፣ የእርግማን ንግግር የተናገርሽበትና እኔም የሰማሁት እነሆ እዚህ አለ! ብሩ በእኔ ዘንድ አለ፡፡ እኔ ሰርቄዋለሁ!” እናቱም እንዲህ አለች፣ “ልጄ ሆይ፣ እግዚአብሔር ይባርክህ!”
3እርሱም 1, 100 ብር ለእናቱ መለሰላት፣ እናቱም እንዲህ አለችው፣ “ስለ ልጄ የተቀረጸ የእንጨት ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል ለማድረግ ይህን ብር ለእግዚአብሔር ለይቼዋለሁ፡፡ ስለዚህ አሁን፣ ለአንተ መልሼዋለሁ፡፡”
4ለእናቱም ገንዘቡን በመለሰላት ጊዜ፣ እናቱ ሁለቱን መቶ ብር ወሰደችና የተቀረጸ የእንጨት ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አድርጎ ለሰራው ለብረት ሰራተኛ ሰጠችው፡፡ ያም በሚካ ቤት ተቀመጠ፡፡
5ሚካ የተባለውም ሰው የጣዖታት አምልኮ ቤት ነበረውና አንድ ኤፉድና ተራፊም ሰራ፣ ከልጆቹም አንዱ ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው አደረገ፡፡
6በዚያን ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፣ ሰውም ሁሉ በዓይኖቹ ፊት ትክክል መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር፡፡
7አሁን በቤተ ልሔም ይሁዳ ከይሁዳ ወገን የሆነ አንድ ሌዋዊ ወጣት ሰው ነበረ፡፡ እርሱም ተግባሩን ለመፈጸም በዚያም ይቀመጥ ነበር፡፡
8ይህ ሰው የሚቀመጥበትን ስፍራ ለመፈለግ ቤተ ልሔም ይሁዳን ለቅቆ ሄደ፡፡ ሲጓዝም ወደ ኮረብታማው የኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጣ፡፡
9ሚካም ለእርሱ እንዲህ አለው፣ “ከወዴት መጣህ?” እርሱም እንዲህ አለው፣ “እኔ ከቤተ ልሔም ይሁዳ የመጣሁ ሌዋዊ ነኝ፣ የምኖርበትን ስፍራ ለማግኘት እየተጓዝሁ ነው፡፡”
10ሚካም እንዲህ አለው፣ “ከእኔ ጋር ተቀመጥ፣ ለእኔም አማካሪና ካህን ሁነኝ፡፡ እኔም በየዓመቱ አሥር ብር፣ እንደዚሁም ልብሶችንና ምግብህን እሰጥሃለሁ፡፡” ስለዚህ ሌዋዊው ወደ ቤቱ ገባ፡፡
11ሌዋዊውም ከሰውዮው ጋር ለመቀመጥ ፈቃደኛ ሆነ፣ ወጣቱም ሰው ለሚካ ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት፡፡
12ሚካም ሌዋዊውን ለተቀደሰ ሃላፊነት ቀደሰው፣ ወጣቱም ሰው ካህኑ ሆነለት፣ በሚካም ቤት ነበረ፡፡
13ከዚያም ሚካ እንዲህ አለ፣ “አሁን እግዚአብሔር ለእኔ መልካም እንደሚሰራልኝ አውቄአለሁ፣ ምክንያቱም ይህ ሌዋዊ ካህን ሆኖልኛል፡፡”